1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ሶስት የጉራጌ ዞን ወረዳዎች ዉሳኔ እና አንድምታው

ቅዳሜ፣ ነሐሴ 7 2014

በጉራጌ ዞን የሚገኙ ሦስት የወረዳ ምክር ቤቶች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል ለሁለት የሚከፍለውን የክላስተር አደረጃጀት አጸደቁ ፡፡ የመስቃን ፣ የምስራቅ መስቃን እና የማረቆ ብሄረሰብ ምክር ቤቶች የክላስተር አደረጃጀቱን ያጸደቁት ዛሬ በየወረዳቸው በጠሩት አስቸኳይ ጉባዔዎቻቸው አማካኝነት ነው ፡፡

Äthiopien | Mareko wereda council meeting
ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በጉራጌ ዞን ውስጥ የሚገኙ ሶስት ወረዳዎች የዞኑን ውሳኔ የቀለበሰ ውሳኔ አሳለፉ

This browser does not support the audio element.

በጉራጌ ዞን የሚገኙ ሦስት የወረዳ ምክር ቤቶች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል ለሁለት የሚከፍለውን የክላስተር አደረጃጀት አጸደቁ ፡፡ የመስቃን ፣ የምስራቅ መስቃን እና የማረቆ ብሄረሰብ ምክር ቤቶች የክላስተር አደረጃጀቱን ያጸደቁት ዛሬ በየወረዳቸው በጠሩት አስቸኳይ ጉባዔዎቻቸው አማካኝነት ነው ፡፡የወረዳ ምክር ቤቶቹ ውሳኔ ከትናንት በስቲያ ሀሙስ የዞን ምክር ቤት ውሳኔ ጋር የሚጣረስ ነው ያሉት አንድ የህግና የአስተዳደር ባለሙያ በበኩላቸው አካሄዱ ምናልባትም የህገ መንግሥት ትርጉም ሊያስፈልገው ይችላል ብለዋል፡፡

በጉራጌ ዞን የሚገኙ ሦስት የወረዳ ም/ቤቶች ዛሬ ቅዳሜ አስቸኳይ ጉባኤዎቻቸውን አካሄደዋል፡፡ የመስቃን ፣ የምስራቅ መስቃንና የማረቆ ብሄረሰብ ም/ቤቶች አሁን ያለውን የደቡብ ክልል በሁለት አስተዳደራዊ ክልሎች ለማደራጀት በቀረበው ሀሳብ ላይ ተወያይተዋል ፣ ውሳኔዎችንም አሳልፈዋል፡፡ በተለይም የማረቆ ወረዳ ም/ቤት ከአጎራባች ዞኖችና ወረዳዎች ጋር በአንድ የጋራ ክልል ለመሆን የቀረበውን ሀሳብ  ጉባኤተኛው በሙሉ ድምጽ ማጽደቁን የም/ቤቱ ምክትል አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ስኳሬ ኮሊሶ ለዶቼ ቬለ DW ገልፀዋል፡፡

ምስል Shewangizaw Wegayehu/DW

በዞኑ የመስቃን እና የምስራቅ መስቃን ወረዳ ም/ቤቶች በየበኩላቸው በጠሩት አስቸኳይ ጉባኤ ‹‹ ክላስተር ››  የተባለውን አወቃር የሚደግፉ ውሳኔዎችን አሳልፈዋል፡፡ የምስራቅ መስቃን ወረዳ ም/ቤት አባል አቶ በረኸዲን ከማል ‹‹ በጉባኤው የመስቃን ቤተ ጉራጌ ከአጎራባች ህዝቦች ጋር በአንድ ክልላዊ አስተዳደር ሥር መሆን አለበት የሚለውን አማራጭ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል ›› ብለዋል፡፡

የወረዳ ም/ቤቶቹ ዛሬ ያሳለፏቸው ውሳኔዎች የጉራጌ ዞን ም/ቤት ባለፈው ሀሙስ ውድቅ ካደረገው የክላስተር አደረጃጀት አጀንዳ ጋር በተቃራኒው የቆመ ነው፡፡ ጉዳዩ በዞን ም/ቤትና በወረዳ ም/ቤቶች መካከል የውሳኔ መጣረዝ አያስከትልም ወይ? ውሳኔው ከሕግ አንጻርስ እንዴት ይስተናገዳል ? በሚል ዶቼ ቬለ DW የሕግና አስተዳደር መምህርና ተመራማሪ የሆኑትን አቶ ሀሮን ደጎልን ጠይቋል፡፡ አቶ ሀሮን የዞንም ሆነ የወረዳ ም/ቤቶች በክልሉ ሕገ መንግሥት ከተሠጧቸው ስልጣኖች መካከል ቀድሞውኑ በአደረጃጀት ላይ ይወስናሉ የሚል ነገር የለም ይላሉ ፡፡ ‹‹ በደቡብ ክልል ህገ መንግሥት ላይ የዞንና የወረዳ ምክር ቤቶች አስተዳደራዊ መዋቅር ጉዳዮችን ተመልክተው ሊወስኑ ይችላሉ በሚል የተሠጣቸው ሥልጣንና ተግባር የለም ፡፡ ምክር ቤቶቹ ክልል ወይም ክላስተር ይሻለኛል ብለው የሚወስኑት በየትኛው ህግ እንደሆነ በራሱ አጠያያቂ ነው ፡፡ ውሳኔያቸው ምናልባትም የህገ መንግሥት ትርጉም ሊያስፈልገው ይችላል ›› ብለዋል ፡፡

በደቡብ ክልል የሚገኙ 10 የዞንና 6 የልዩ ወረዳ ም/ቤቶች ክልሉን ለሁለት የሚከፍለውን የክላስተር አደረጃጀት በቅርቡ ነበር ያጸደቁት ፡፡ ም/ቤቶቹ ሐምሌ 28 ቀን 2014 ዓም ውሳኔው ተፈጻሚ ይሁንልን ሲሉም  ለፌዴሬሽን ም/ቤት ማቅረባቸው ይታወሳል፡፡ ባለፈው ሐሙስ ጉባኤውን ያካሄደው የጉራጌ ዞን ም/ቤት በአንጻሩ የክላስተር አደረጀጀቱን በ40 የድጋፍና በ52 የተቃውሞ ድምፅ ውድቅ ማድረጉ  የሚታወቅ ነው፡፡ ‹‹ ክላስተር አልፈልግም ›› ያለው  የዞኑ ም/ቤት ሦስቱ የወረዳ ም/ቤቶች ዛሬ ባሳለፉት ውሳኔ ዙሪያ እስካሁን ያለው ነገር የለም፡፡

 ሸዋንግዛው ወጋየሁ 

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW