ዘርፈ ብዙ ጥቅማቸው ተመራጭ አድርጓቸዋል
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 26 2009መልዓከፀሐይ የሚጠቀመው እንደብጤዎቹ ለመያዝ የሚያሳሱ የእጅ ስልኮች ሳይሆን ከቁመቱ ዘለግ ከክብደቱ ደርጀት ያለ ተንቀሳቃሽ ስልክ ነው፡፡ ስልኩ እንደ ቅንጦዎቹ ስልኮች ሁነኛ የንግድ ምልክት የለውም፡፡ አጽህሮተ ቃል እና ቁጥሮችን የደባለቀ መለያ ከስክሪኑ ታች ያስቀመጠ ነው፡፡ ሁለት ሲም ካርድ ይቀበላል፡፡ መደበኛ የእጅ ስልክ አገልግሎቶች የሚባሉትን የድምጽና የጽሁፍ ልውውጥ ማካሄድ ያስችላል፡፡ ስልኩን ከገዛው አንድ ዓመት ከስድስት ወር እንዳለፈው የሚናገረው መልዓከፀሐይ እኒህን አገልግሎቶች ያለምንም ችግር እያገኘበት በመሆኑ ደስተኛ ነው፡፡ ይህን ስልክ ምርጫው ያደረገበትን ምክንያቶች እንዲህ ይዘረዝራል፡፡
“ብዙ ቀን ቻርጅ ሳታደርገው ይሰራል፡፡ ረጅም ጊዜ የሚቆይ ነው፤ ወድቆ ይነሳል፡፡ ባትሪ አለው፡፡ ኔትወርኩም አሪፍ ነው፡፡ ካለንበት ሁኔታ አንጻር ትርጉም ይሰጣል፡፡ የስልክ ኔትወርክ ችግር አለ፡፡ አንዳንድ አካባቢዎች ኔትወርኩ በጣም የሳሳ ነው፡፡ መብራትም በተደጋጋሚ ይቋረጣል፡፡ በሁለቱም ምክንያት በአስተማማኝ ሁኔታ ሰዎችን ማግኘት እንድትችል ስለሚያደርግ ነው” ይላል የስልኩን ጠንካራ ጎኖች ሲዘረዝር፡፡
እንደ አዲስ አበባ ባለ ከተማ ለሚኖር የመልዓከፀሐይ አይነት ወጣት የእጅ ስልክ ማለት ተራ መገልገያ ብቻ አይደለም፡፡ የኑሮ ደረጃ መለኪያም እንጂ፡፡ ወጣቱ ይህን አስተሳሰብ ተሻግሮ ስልክን በጠቀሜታው ብቻ እንደሚመዝን ይናገራል፡፡ ቅንጡ ስልክ ይዞ “ወዲያው ባትሪው የሚያልቅ ከሆነ፣ ጥሩ ኢንተርኔት በሌለበት አፕልኬሽን መጠቀም ካዳገተ፣ ኢትዮጵያዊ ይዘት ያላቸው መረጃ አቅራቢዎች ማግኘት ካስቸገረ” የጊዜውን ምርጥ ስልክ መያዝ ጠቀሜታው አይታየኝም ባይ ነው፡፡
እርሱን ጨምሮ በርካቶች “ፊቸር ስልክ” ተብለው ወደሚታወቁት እና መሰረታዊ የስልክ አግልግሎት ብቻ ወደሚሰጡ የእጅ ስልኮች ፊታቸውን ያዞሩት ፍላጎቶቻቸውን ስለሚያሟሉላቸው እንደሆነ ይከራከራል፡፡
“አብዛኛው ሰው እየተከተለ ካለው፣ በዘመኑ ሰዎች ጥሩ ነው ብለው እያደረጉ ካሉት ነገር [ይልቅ] የቀን ውሏችን ውስጥ ያለ መሰረታዊ ፍላጎት የበለጠ ሃይል እንዳለው ነው የሚያሳየው፡፡ መሰረታዊ ፍላጎቱ ምንድነው? ከሰው ጋር መገናኘት መቻል፣ ሁሌ ከሰው ላለመራቅ፣ ላለመጥፋት እና ስራዎችን ማከናወን መቻል ያለውን ፋሽን ወይም ሰዎች የሚያደርጉትን ነገር ከመከተል የበለጠጠንካራ የማሳመን ኃይል አለው፡፡ እና እዚህ ጋር እንደዚያ ነው እየሆነ ያለው” ሲል ይሟገታል፡፡
መልዓከፀሐይ ስልኩ በእርሱ ጓደኞች እጅ በብዛት ባይታይም የኮንስትራክሽን ስራ ላይ ባሉ ግለሰቦች እና ብዙ ጊዜያቸውን መንገድ ላይ በሚያሳልፉ ሰዎች ዘንድ በብዛት እንደተመለከተ ያስረዳል፡፡ ለዚህ ምልከታው አንዱ ማሳያ ከመዲናይቱ አዲስ አበባ በስተምስራቅ በ515 ኪሎሜትር ርቀት ላይ የሚኖረው አብዱ መሐመድ ነው፡፡
አብዱ ስራው ሹፍርና ነው፡፡ ከሚኖርበት ድሬዳዋ እየተነሳ ለቀናት ባስ ሲልም ለሳምንታት ይጓዛል፡፡ አብዛኛው ጉዞው ደግሞ መንገድ እንኳ በቅጡ ያልተዘረጋባቸው የገጠር አካባቢዎች ነው፡፡ በእነዚያ አካባቢዎች የመብራት ኃይልም ሆነ ሌሎች የመሰረተ ልማት አቅርቦቶች ብርቅ ናቸው፡፡ ለቀናት በእንዲህ አይነት ቦታ ላይ መቆየት ግድ በሚለው ስራው ምክንያት አብዱ መቸገሩ አልቀረም፡፡ ቶሎ ባትሪ የሚጨርሰውን የዘመናዊ ስልኩን ነገር በመኪናው ላይ በተገጠመ ቻርጀር ሊያስታግስ ቢሞክርም የኔትወርክ ለማግኘት ያለውን ችግር ግን መፍታት አቅቶት ቆይቷል፡፡
ለጠረፍ አካባቢዎች ባላት ቅርበት ምክንያት አዳዲስ የቴክኖሎጂ እና ኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን ለማግኘት ፈጣን ነች በምትባለው ድሬዳዋ መኖሩ ጠቅሞታል፡፡ የዛሬ ዓመት ግድም በድሬዳዋ አቅራቢያ ወደምትገኘው የሶማሌ ክልሏ ዶሎ ኦዶ በተጓዘ ጊዜ አንዴ ቻርጅ ከተደረገ እስከ 15 ቀናት ድረስ የባትሪ ቆይታ ስላለው ስልክ ይሰማል፡፡ ካለው ቅንጡ ስልክ በተደራቢነትም ቢሆን ለመግዛት አይኑን አላሸም፡፡ ስልኩ በተለይ በገጠር ያለውን ጠቀሜታ እንዲህ ይገልጻል፡፡
“አንዳንድ ቦታዎች መብራት ያልደረሱባቸው ቦታዎች ስላሉ እነዚያ ቦታ ላይ በእሱ ነው የምንጠቀመው፡፡ ራሱን የቻለ አምፖል ስላለው አምፖሉን ሰክተን በእርሱ እንጠቀማለን፡፡ መብራት ሲጠፋ በእሱ አምፖል እየሰካህ እንደ መብራት ትጠቀመዋለህ፡፡ ሙሉ ለሙሉ ክፍት ከሆነ እስከ ሶስት ቤት ሊያበራ ይችላል፡፡ እሱን አምፖል የማትጠቀም ከሆነ 15 ቀን [ከዚያ] በላይም ልትጠቀም ትችላለህ፡፡ ማታ ሙሉ የምታበራው ከሆነ ግን አራት ወይም አምስት ቀናት ልትጠቀመው ትችላለህ፡፡ ሁለተኛ ነገር ደግሞ ብዙውን ጊዜ ጫካ ነው የምንውለው፡፡ በዚያ ኔትወርክ ስቦ ያገኝልናል፡፡ ሌሎች ቅንጡ ስልኮች ኔትወርክ እንደእርሱ አይስቡም፡፡ የመስክ ስራ ላይ በጣም ጠቃሚ ስልክ ነው” ይላል ስለ ስልኩ ትሩፋቶች ሲያስረዳ፡፡
ስልኩ ከሹፌሮች ሌላ በምግባረ ሰናይ ድርጅቶች ውስጥ በሚሰሩ ሰዎች ዘንድም ተወዳጅነት እንዳለው አብዱ ያስረዳል፡፡ የእርሱን ዓይነት ሰዎች ራስ ምታት ማቃለሉን ሲመለከት “ለእኛ ሀገር የተሰራ ነው የሚመስለው” እንዲል አድርጎታል፡፡ ሆኖም እርሱ የገዛው በሶማሊያ በኩል የገባውን ውጭ ሰራሽ ስልክ ነው፡፡ እንደ እርሱ ሁሉ መልዓከፀሐይም በሞያሌ መስመር በኬንያ በኩል የመጣውን ስልክ ሲዳሞ ላይ እንዳስገዛ ይናገራል፡፡
ስልኩ በተለያየ ሀገራት ተመርቶ በተለያየ መንገድ ወደ ኢትዮጵያ ቢገባም በእጅ ስልክ ተጠቃሚዎች ዘንድ ተወዳጅነትን ለማትረፍ አጭር ጊዜ ብቻ እንደፈጀበት ተገልጋዮቹ እና በተንቀሳቃሽ ስልክ ንግድ የተሰማሩ ግለሰቦች ይመሰክራሉ፡፡ አብዛኞቹ ተጠቃሚዎቹም ከከተሞች ውጭ ያሉ ነዋሪዎች እንደሆኑ ይናገራሉ፡፡ አሊ ሁሴን በሰሜን ኢትዮጵያ ደሴ ከተማ የተንቀሳቃሽ ስልክ እና ተዛማጅ ዕቃዎች መሸጫ ሱቅ አለው፡፡ ስለ እንደዚህ ዓይነት ስልኮች ተወዳጅነት እንዲህ ያብራራል፡፡
“በተለይ ገጠር አካባቢ ላይ የሚኖሩ ግለሰቦች በደንብ ይፈልጉታል፡፡ ከሌላው የተሻለ ሽያጭ [አለው]፡፡ እርሱ ይሻላል፡፡ ለምን ቢባል? የተሻለ አገልግሎት አለው፡፡ በዚህ ሰዓት የተሻለ ደንበኛ ያለው እርሱ ነው ግን ጥራቱ መጀመሪያ ላይ እንደነበረው አይደለም፡፡ ቢሆንም ግን በፊት በነበረው ተቀባይነት አሁንም የተሻለ የሚሸጠው እርሱ ነው፡፡ ሰው ይፈልገዋል” ይላል አሊ፡፡
እንደዚህ ስልኮች በገበያው ላይ ሰፊ ተቀባይነት አንዲያገኙ ካደረጋቸው ምክንያቶች አንዱ ዋጋቸው ከቅንጡ ስልኮች ጋር ሲነጻጸር ርካሽ መሆኑ ነው፡፡ የድሬዳዋው አብዲ ዋጋው ወደድ ያለውን፣ የተሻሻለ የተባለውን እና የስልክ ስክሪኑ በእጅ የሚነካውን ሲገዛ አንድ ሺህ ብር አውጥቷል፡፡ የአዲስ አበባው መልዓከፀሐይ በበኩሉ ስልኩ ገና እንዳሁኑ ሳይታወቅ በ700 ብር ብቻ ነበር የገዛው፡፡ በመጠን እና ሞዴል የተለያዩ እንዲህ አይነት ስልኮች በወቅቱ የገበያ ዋጋ ከ400 እስከ 600 ብር እንደሚሸጡ የደሴው አሊ ያስረዳል፡፡
የእጅ ስልኮቹን ይበልጥ ተመራጭ የሚያደርጋቸው የባትሪ ኃይላቸው ነው፡፡ ትንሹ የሚባለው 2‚800 ዋት ጉልበት ያለው ሲሆን እስከ 10‚000 ዋት ድረስ ኃይል ያላቸው እንዳሉም አሊ ይናገራል፡፡ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እያጋጠመው ያለው የስልኮቹ የጥራት መዋዠቅም ከባትሪያቸው ኃይል መድከም ጋር የተያያዘ እንደሆነ ይገልጻል፡፡ ይህን ስልክ ገዝተው ሌሎች ስልኮችን ቻርጅ ለማድረግ እንደ ኃይል ቋት (ፓወር ባንክ) ለሚጠቀሙ የገጠር ነዋሪዎች በተለይ ይህ መልካም ዜና አይደለም፡፡
በገጠር ባሉ ነዋሪዎች ዘንድ ስልኩን ተመራጭ ያደረገው ሌላው አግልግሎቱ ሬድዮ ያለ ተቀጥላ ማዳመጫ በራሱ አንቴና ብቻ መሳቡ እና ሙዚቃን ከፍ ባለ ድምጽ ማጫወቱ ነው፡፡ ስልኩን ከአንድ ቦታ አስቀምጠው እንደ እርሻ ባሉ ስራዎች ለሚሰማሩ ተጠቃሚዎች ይህ የልብ አድርስ ሆኖላቸዋል፡፡ በጥቅሉ “ፊቸር” ተብለው የሚጠሩት እንዲህ አይነት ስልኮች ቀላል በሚባሉ እኒህን መሰል ጥቅሞቻቸው ምክንያት በአፍሪካ አሁንም ተወዳጅነታቸው ከፍተኛ እንደሆነ ጥናቶች ይጠቁማሉ፡፡
በዓለም ዓቀፍ ጉዳዮች ላይ ምርምር በሚያደርገው ፒው ሪሰርች ሴንተር አማካኝነት በጎርጎሳዊው 2015 ኬንያን ጨምሮ በሰባት ከሰሃራ በታች ባሉ ሀገራት የተደረገ አንድ ጥናት እንደሚያመለክተው ሞባይል ተጠቃሚ ከሆነው ህዝብ መካከል 65 በመቶው አሁንም እነዚህን መሰረታዊ ግልጋሎት ብቻ የሚሰጡ ስልኮችን ይጠቀማል፡፡ ብዙ ተንታኞች እንደሚስማሙት በአፍሪካ የዘመናዊ ስልኮች አብላጫውን ቦታ መያዝ የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ አይቀሬ ነው፡፡በቴሌኮምኒኬሽን እና ሚዲያ ላይ ጥናት የሚያካሂደው ኢንፎርማ ቴሌኮምስ ኤንድ ሚዲያ የተባለ የእንግሊዝ የምርምር ተቋም እንደተነበየው በጎርጎሳዊው 2012 መጨረሻ በአፍሪካ 80 ሚሊዮን ብቻ የነበረው የዘመናዊ ስልኮች ብዛት በቀጣዩ ዓመት ግማሽ ቢሊዩን ያህል ይደርሳል፡፡
በኢትዮጵያ ያለው የመሰረታዊ የእጅ ስልኮች ተወዳጅነት ማሻቀብ “ሀገሪቱ ዓለምም ሆነ አህጉሪቱ እየተጓዙበት ካለው አቅጣጫ በተቃራኒ እየሄደች ይሆን?” የሚል ስጋት ቢጤ ያጭራል፡፡ ከተንቀሳቃሽ ስልክ ጋር በተያያዙ ጉዳዮች ላይ የማማከር አገልግሎት የሚሰጠው ነብዩ ይርጋ ለዚህ ስጋት ምላሽ አለው፡፡
“የዘመናዊ ስልኮቹ ጥቅም ምንድነው? የዕለት ከዕለት ውሏችንን ብዙ የሚያቀልልን አፕልኬሽኖች በመስራትና አገልግሎቶች አቅርበህ በመሸጥ ሰው እንዲጠቀም ለማድረግ ነው፡፡ ከተማ ውስጥ ለምንኖረው፣ ለዕለት ከዕለት ኑሯችን ለምንጠቀመው ተመልሰን ወደ መሰረታዊ ስልኮች የምንመልስበት ዕድል በጣም ትንሽ ነው፡፡በኑሯችን ከዘመናዊ ስልክ ጋር ያለን ቅርበት ጨምሯል፡፡ ኢንተርኔቱ ሊቀንስ ይችላል ወይም ላይመቸን ይችላል አሊያም የምንኛገኝበት ዕድል እየጠበበ ሊመጣ ይችላል፡፡ እርሱ ይሆናል የሚቸግረን፡፡”
“ከዚህ በኋላ ያለው አመጣጥ ግን ለምሳሌ ኢትዮ-ቴሌኮም የሚወጣቸው ጨረታዎች ወይም አሁን ያሉትም ጨረታዎች ዘመናዊ ስልኮች ለሚያቀርቡ ነው፡፡ መሰረታዊ ስልኮችም ይሸጣሉ፡፡ ለሚፈልግ ሰው ማቅረብ ስለሆነ ስራህ ለሁሉም ነገር መቀበል ነው፡፡ ያው እንግዲ ምርጫው ለሰው ነው የሚተወው፡፡ እንደእኔ እንደእኔ ወደ ኋላ መመለስ የሚባለው ምርጫ ውስጥ የሚገባ አይደለም፡፡ የማደርገው ነገር አይደለም፡፡ ይጎትተናል፤ አውቃለሁ ግን ወደ እሱ የምንመለስበት ጉዳይ አይደለም” ሲል እርግጠኝነት በተላበሰ ድምጽ ያስረዳል፡፡
መልዓከፀሐይን ግን በሚይዘው ስልክ መጠን መተለቅ ምክንያት በኢትዮጵያ ተንቀሳቃሽ ስልክ በተጀመረ ወቅት ወደነበረው የስልክ ዓይነት የተመለሰ አድርገው የሚቆጥሩት አሉ፡፡የዚያን ጊዜው ስልክ ትልቅነቱን ለማጠየቅ “ዳስተር” በሚል ቅጽል ይጠራ ነበር፡፡ አሁን እርሱ የሚይዘውን ደግሞ “ዎኪ ቶኪ” ሲሉ በጸጥታ አስከባሪዎች ዘንድ የተለመደው የሬድዮ መገናኛ ስያሜ ይሰጡታል፡፡ ስልኩን የሚያዩት ሰዎች እንደሚገረሙ የሚናገረው መልዓከፀሐይ ስለትልቅነቱ ያለውን ስሜት በሳቅ ታጅቦ ያጋራል፡፡
“ትረባ ድረስ ባይደርስም እንደመነጋገሪያ ሆኖ ይቀርባል፡፡ ጥሩ በር ከፋች ነው፡፡ በዚህ ምክንያት ንግግር ይጀመራል፡፡ አስገራሚ ነው፡፡ መጠኑም እኮ ከበፊቱም ይተልቃል፡፡ እና ብዙም የሚያሳፍር ሆኖ አላገኘሁትም፡፡ እንደውም እንዳትረሳው ያደርግሃል፡፡ የሆነ ቦታ ረስተኸው ብትወጣ ‘ምን ቀለለኝ ዛሬ?’ ትላለህ፡፡ ስለዚህ እስከዛሬ ረስቼው አላውቅም፡፡”
ተስፋለም ወልደየስ
ኂሩት መለሰ