1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ሳይንስኢትዮጵያ

ሽመናን ያዘመነው ሀገር በቀል ቴክኖሎጂ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3 2016

ቴክኖሎጂው የተሰራው ኢንጂነር ቻላቸው ሰጠኝ በተባሉ በአዲስ አበባ የዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጅ ኢንስቲቲዩት የሚካኒካል ምህንድስና መምህር ሲሆን፤ የክር ፣የድር እና ማግ ማጠንጠኛ እንዲሁም አውቶማቲክ መሸመኛ ማሽኖችን ያጠቃልላል። ቴክኖሎጅው ጊዜ እና ጉልበትን የሚቆጥብ ሲሆን ምርታማነትንም በአስር እጥፍ የሚያሳድግ መሆኑ ተገልጿል።

የመሸመኛ ማሽን  በኤለክትሪክ የሚሰራ እና ዘመናዊ እና ባህላዊ አልባሳትን ለመስራት የሚያገለግል ነው።
ኢንጅነር ቻላቸው ሰጠኝ የሰሩት አውቶማቲክ የመሸመኛ ማሽን በኤለክትሪክ የሚሰራ እና ዘመናዊ እና ባህላዊ አልባሳትን ለመስራት የሚያገለግል ነው።ምስል Privat

ቴክኖሎጅው ባህላዊ እና ዘመናዊ አልባሳትን በቀላሉ ለማምረት ያስችላል

This browser does not support the audio element.


የሽመና ስራ በኢትዮጵያ በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ቀደምት ዘርፍ ቢሆንም አሰራሩ የዕድሜውን ያህል የተሻሻለ አይለም።ሽመና አሁንም  ድረስ ጊዜን እና ጉልበትን የሚወስድ አድካሚ ስራ ነው። የሚገኘው የምርት መጠን ቢሆን፤ ከወጣው ጉልበት እና ጊዜ ጋር የሚወዳደር አይለም።ይህንን የተገነዘቡ ኢንጂነር ቻላቸው ሰጠኝ የተባሉ በአዲስ አበባ  የዩንቨርሲቲ የቴክኖሎጅ ኢንስቲቲዩት የሚካኒካል ምህንድስና  መምህር  የሽመና ስራን የሚያዘምን ቴክኖሎጅ ሰርተዋል። 

ኢንጅነር ቻላቸው ሰጠኝ ዘመናዊ የሽመና ማሽን የሰሩ ምስል Privat

ኢንጅነር  ቻላቸው  እንደሚሉት የህብረተሰብን ችግር  የሚፈቱ   የፈጠራ ስራዎችን ማሽኖችን እና ቴክኖሎጅዎችን መስራት የልጅነት ህልማቸው ነው። ይህንን ህልማቸውን ለማሳካትም በባህርዳር ፣በአርባ ምንጭ  እና በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲዎች የሜካኒካል ምህንድስና ትምህርት ክፍልን በመቀላቀል እስከ ማስርስ ዲግሪ ትምህርታቸውን ተከታትለዋል።
የሜካኒካል ምህንድስና ትምህርትን የተማርኩት ንድፈ ሃሳብን ችግር ፈቺ ፈጠራዎችን በመስራት በተግባር ለማሳየት ነው የሚሉት ኢንጅነር ቻላቸው፤ የሽመና ስራን የሚያዘምነውን  ይህንን የፈጠራ ስራቸውን የጀመሩትም በ1997 የዩንቨርሲቲ ተማሪ በነበሩበት ወቅት ነው። «የሽመና ማሽን መስራት የጀመርኩት ተመራቂ በነበርኩበት ወቅት ነው።ሃያ ዓመት ሊሆነው ነው።እና የመመረቂያ ፕሮጄክቴ እንዲሁ መመረቂያ ብቻ ሳይሆን በተግባር ላይ መዋል የሚችል ቴክኖሎጅ፤ የህብረተሰቡን ችግር የሚፈታ ሀሳብ እንዲሆን እፈልግ ነበር።አድቫይዘሬ ነው አጋጣሚ ባህርዳር ዩንቨርሲቲ «ቴክስታይል ዲፓርትመንት» አለ።እዚያ ዲፓርትመንት ውስጥ ባህላዊ የሽመና ክፍል አላቸው።እስኪ የሽመና መሳሪያዎችን እይና ዛሬ ትሰራለህ  ብሎ ሲወስደኝ አንድ ሽማኔ በአንድ ቀሰም እያዳወረ ነበር ያገኘነው።ስለዚህ መካኒዝም ብንፈጥርለት በአንዴ ብዙ ቀሰም ማጠንጠን ይችላል ብዬ ሀሳብ አቀረብኩ።ስራ ብሎኝ በዚህ አጋጣሚ ወደ ሽመና ቴክኖሎጅዎች ገባሁ ማለት ነው።»በማለት አብራርተዋል። 

ኢንጅነር ቻላቸው ሰጠኝ፤ የክር ፣ማጠንጠኛ፣ የድር እና የማግ ማድሪያ ወይም ማዘጋጃ እንዲሁም አውቶማቲክ መሸመኛ  መሳሪያዎችን ሰርተዋልምስል Privat

ኢንጂነሩ በመጀመሪያ የሰሩት የክር ማጠንጠኛ ማሽን ሲሆን፤ ውለው አድረው ግን ከሸማ ሰሪዎች ጋር የነበራቸው የዕለት ተዕለት ግንኙነት እየተጠናከረ በመምጣቱ እና የዘርፉን ችግር በቅርበት ሆነው በማየታቸው  በ2009 ዓ/ም መሸመኛ ማሽን ለመስራት ችለዋል።በዚህ ሁኔታ ባለሙያው የተለያዩ ባህላዊና ዘመናዊ ልብሶችን ለማምረት የሚያገለግሉ በኤሌክትሪክ ኃይል የሚሰሩ የክር ፣ማጠንጠኛ፣ የድር እና የማግ ማድሪያ ወይም ማዘጋጃ እንዲሁም አውቶማቲክ መሸመኛ  መሳሪያዎችን ሰርተዋል።
ባለሙያው ስለ ፈጠራ ሥራዎቹ ጠቀሜታ ሲገልፁ፤ በተለይም ያለ ሰው ዕገዛ የሚሰራው የመሸመኛ ማሽን ጊዜና ጉልበትን በመቆጠብ ምርታማነትን በአስር እጥፍ እንደሚያሳድግ ይናራገሉ። «በባህላዊ ጨርቃጨርቅ ሴክተር ላይ ብዙ አይነት ችግሮች አሉ።«ሌቨር ኢንተንሲቭ» ነው።በጣም ሲለፋ ውሎ ትንሽ ነው የሚሰራው።በሌላ በኩል የህፃናት የጉልበት ብዝበዛ አለ።የሴቶች የስራ ጫናም አለ።ትንሽ ችግር የሚፈጥር ሴክተር ነው።የክር ማጠንጠኛ ማሽን አለ።የሽመና ማሽን አለ።የማድሪያ ማሽንም ሰርቻለሁ።እነዚህን አቀናጅቶ በሚጠቀሙበት ጊዜ፤አንደኛ አዋቂ ሰዎች ነው የሚሰሩበት በቴክኖሎጅው።የሰው ጉልበት አይጠይቅም።የሰው ጉልበት ይቆጥባል።በአግባቡ ከተጠቀሙበት ምርታማነትን በአስር እጥፍ ይጨምራል።»በማለት የቴክኖሎጅውን ጠቀሜታዎች አስረድተዋል። ቴክኖሎጅው የሴቶችን የሥራ ጫና ከመቀነሱ በተጨማሪ  የሕጻናትን የጉልበት ብዝበዛ  በማስቀረት ጊዚያቸውን ለትምህርት እንዲያውሉት በማድረግ ረገድም  ያለው ፋይዳ ቀላል አይደለም።

ባህላዊ የሽመና ስራ በአብዛኛው ህፃናትን ለጉልበት ብዝበዛ የሚዳርግ ነው ምስል Mortuza Rashed/DW

በሌላ በኩል ማሽኑ ለአሠራር ምቹ በመሆኑ የአካል ጉዳተኞችን በዘርፉ ለማሳተፍ እና  ለሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል ለመፍጠርም ያግዛል።
አዲስ አበባ ከተማ በሚገኘው ሚርካ ኢንጅነሪንግ በተባለው የግል ድርጅታቸው አማካኝነት ማሽኑን ሰርተው በመሸጥ ለተጠቃሚዎች ማድረስ መጀመራቸውን የሚናገሩት ባለሙያው፤ማሽኑን ሰርቶ መሸጥ ብቻ ሳይሆን ስለ አጠቃቀሙም ለተጠቃሚዎች ስልጠና ይሰጣሉ።በዚህም ተጠቃሚዎች ደስተኞች መሆናቸውን ይገልጻሉ።
በጎንደር ከተማ በባህላዊ አልባሳት ስራና ሽያጭ የሚተዳደሩት አቶ ሀይሉ መኮንንን ይህንን ማሽን ገዝተው ከሚጠቀሙት መካከል ናቸው። እሳቸው እንደሚሉት ከማሽኑ በርካታ ጠቀሜታዎችን አግኝተዋል። 
«ማሽኑን አይቼ ነበር ያዘዝኩት።አንደኛ የሰው ጉልበት ይቀንሳል።ምርቱም በአስር እጥፍ ከፍ ያለ ነው።ለምሳሌ እኛ ሙሉ ቀን ሰርተን 11 ሜትር አካባቢ ነበር የምናወጣው።በማሽኑ ግን ወደ መቶ ሜትር አካባቢ በቀን ማውጣት እንችላለን።በአስር እጥፍ አደገ ማለት ለኛ የተሻለ ነው።በአስር ቀን የምንሰራውን በአንድ ቀን ውስጥ ሰራነው ማለት ነው።»ካሉ በኋላ «ባለሙያ ያልሆነ ሰውም ማሽኑን ማንቀሳቀስ የሚችልበት መንገድ አለ።ለማንኛውም ሰው ሁለት ቀን ሶስት ቀን ስልጠና ሰጥቶ ያንን ማሽን አንቀሳቅሶ እንዲያመርት ማድረግ ይቻላል።»በማለት ጠቀሜታውን አብራርተዋል።

ዘመናዊ የሽመና ማሽኑ ማሽኑን ዘመናዊ እና ባህላዊ ልብሶችን በማምረት የጨርቃጨርቅ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ ያስቀራልምስል Privat

አቶ ሀይሉ እንደሚሉት ፤የውጭ ምንዛሬ ከፍለው ከውጭ ማምጣት የነበረባቸውን ማሽን በሀገር ውስጥ ማግኘታቸውም ሌላው ጠቀሜታ ነው። «አሁን ለምሳሌ እኛ የጥልፍ ማሽን ለማስመጣት ሶስት ዓመት ነው ፕሮሰሱ እያደረግን ያለነው ።ግን እስካሁን ማሽኑ አልገባልንም። በተመሳሳይ ሌላ እናምጣ ብንል ሌላ ሶስት ዓመት ነው የሚወስድብን።»በማለት አቶ ሀይሉ ገልፀዋል። ከዚህ ባሻገር ኢንጅነር ቻላቸው እንደሚገልፁት በሀገር ደረጃም ማሽኑን ከውጭ ገዝቶ ለማምጣት እንዲሁም የጨርቃጨርቅ ምርቶችን ከውጭ ለማስገባት የሚወጣውን የውጭ ምንዛሬ  ያስቀራል።«የውጥው ዓለም ቴክኖሎጅን ቀድሞ በመጀመሩ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ደርሰዋል።እነሱ እያመረቱ የስራ ዕድል ፈጥረው ምርታቸውን ወደ እኛ ይልካሉ።እኛ ደግሞ አንሰራም ምርታቸውን ነው የምንቀበለው።ይህ በሀገራችን ኢኮኖሚ ላይ ትልቅ «ዲፊሲት»የሚፈጥር ነገር  ነው።አብዛኛው ልብሶች የሚመረቱት ደግሞ በሽመና ነው» ካሉ በኃላ «ይህን ሁሉ በዓመት ብዙ  ዶላር እያወጣች ነው ሀገራችን የምትገዛው።ነገር ግን እንደዚህ ዓይነት ቴክኖሎጅዎችን በደንብ እያዘመን ያሳደግን እዚሁ ሀገራችን እያመረትን ኢትዮጵያ ውስጥ ብናሰራጨው።እነዚህን ከውጭ የሚመጡ ልብሶች እዚሁ ማምረት እንችላለን።»ብለዋል።

ባለሙያው ሚርካ ኢንጅነሪንግ በተባለው ድርጅታቸው አማካኝነት ዘመናዊ የመሸመኛ ማሽኑን ማምረት እና መሸጥ ጀምረዋልምስል Privat

በእነዚህ ስራዎችም የፈጠራ ባለሙያው ከኢትዮጵያ አዕምሯዊ ንብረት ባለስልጣን  ዕውቅና ተስጥቷቸዋል።ለዘመናት በሰው ኃይል ብቻ ይሰራ የነበረውን የሽመና ስራ በቴክኖሎጂ በመተካታቸውም ባለሙያው በተለያዩ የሀገር ውስጥ ውድድሮች ሽልማት እና እውቅና  አግኝተዋል። ይሁን እንጅ  ማሽኑን በሚፈለገው መጠን ሰርቶ ለተጠቃሚ ለማድረስ ያለው መሰናክል ቀላል አይደለም ይላሉ።የፈጠራ ባለሙያው እንደሚሉት በ2007 ዓ/ም ሚርካ የተባለ ድርጅት ከፍተው ክር የማጠንጠን ስራ ጀምረው የነበረ ቢሆንም፤ በገንዘብ እጥረት በዓመቱ ማለትም በ2008 ዓ/ም ለመዝጋት ተገደዋል።

የፈጠራ ባለሙያው ዘመናዊ የክር ማጠንጠኛ በመስራት ሚርካ በተባለ ድርጅታቸው አማካኝነት ክር የማጠንጠን ስራ ጀምረው ነበርምስል Privat

ቆይተውም በ2011 ዓ/ም ሚርካ ኢንጅነሪንግ ብለው ንግድ ፈቃድ በማውጣት  የሽመና ማሽኑን ሰርተው በተመጣጣኝ ዋጋ በመሸጥ ለተጠቃሚዎች ለማድረስ ሞክረዋል። ያም ሆኖ ማሽኑን ለማምረት የሚጠይቀው ገንዘብ፣ የመስሪያ ቦታ እና የሰው ሀይል በእሳቸው አቅም የማይቻል በመሆኑ ለሽያጭ ያቀረቡት የሚፈለገውን ያህል አይደለም።«እንደ ማሽኑ ተፈላጊነት ብዙ በማምረት በሀገሪቱ ተሰራጭቶ ጥቅም ላይ መዋል ነበረበት።»እውነት ለመናገር።ነገር ግን ከኔ የዘለለ መንግስትም የተለያዩ ድርጅቶች እና የሚመለከታቸው አካላት የሚገባቸውን ያህል አልሰሩም።ያው በአሁኑ ስዓት አምርቼ መሸጥ ጀምሪያለሁ።ነገር ግን መሄድ ያለብኝ ያህል አልሄድኩም።እንደ ፍላጎታችን መስራት እንደምንችለው አይለም።» በማለት ከገለፁ በኋላ፤ዋናው ችግር የገንዘብ ችግር መሆኑን ገልጸዋል።«ቴክኖሎጅን በብዛት እና በጥራት አምርቶ ለመሸጥ አቅም ይጠይቃል።»ብለዋል።በመሆኑም መንግስትም ሆነ ባለሀብቶች የፈጠራ ስራዎችን ትኩረት ሰጥተው እንዲደግፉ አሳስበዋል።«መንግስትም ሆነ ባለሀብቶች ቁርጠኛ መሆን አለባቸው።የፈጠራ ስራ አንድ የሀገር ሀብት ነው።ስለዚህ ቴክኖሎጅዎችን እያቀናጄንና እያሳደግን መስራት ካልቻልን እንደ ሀገር እድገታችንም ከባድ ነው።»ካሉ በኋላ፤የሌሎች ሀገሮችን ተሞክሮ በመጥቀስ «ማደግ ካለብን ገንዘብ እና የፈጠራ ስራዎች መገናኘት አለባቸው።» በማለት ገልፀዋል።«መንግስት እንደ መንግስት ከፌደራል እስከ ወረዳ ድረስ ለፈጠራ ስራ ትኩረት መስጠት እና ምርታማነትን ለሚጨምሩ እና የስራ ዕድል ለሚፈጥሩ ነገሮች ትኩረት ሰጥቶ የፈጠራ ሰዎችን ማበረታታት ያስፈልጋል።»ብለዋል። 

ሙሉ ዝግጅቱን የድምፅ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡ።

 


ፀሀይ ጫኔ
ሽዋዬ ለገሠ

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW