1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀጠርና የአደራዳሪነት ሚናዋ

ዓርብ፣ ሰኔ 14 2005

የቀተር የውጭ መርህ እንደ እስካሁኑ ላይቀጥል ይችላል። የቀተሩ አሚር ሼክ ሃማድ ቢን ካሊፋ ጤና በማጣታቸው ከሥልጣናቸው ሳይነሱ አይቀርም ። እንደ መጀመሪያ ደረጃ ተደርጎ የሚወሰደው የሚተካቸው ወንዱ ልጃቸው ሼክ ታሚም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱንም ቦታ እንዲይዙ ማድረግ ሳይሆን አይቀርም ። በዚህም ቀጠር አስተዋይና ታዋቂ ዲፕሎማትዋን ታጣላች ።

ምስል XtravaganT/Fotolia

በቀጠር ዋና ከተማ ዶሃ በትናትናው እለት ዩናይትድ ስቴትስና ታሊባን የሰላም ንግግር ለማካሄድ ቀጠሮ ይዘው ነበር ። ይሁንና ታሊባን ቀጠር ውስጥ ቢሮ መክፈቱ የአፍጋኒስታን መንግሥትን አስቆጥቶ በተከተለው ግርግር ምክንያት ንግግሩ ሳይካሄድ ቀርቷል ። የአሜሪካንና የታሊባን ንግግር መቼ እንደሚካሄድ ከዶሃ በኩል የሚታወቅ ነገር እንደሌለ ቢገለፅም የዋሽንግተን መንግሥት ግን የሰላም ድርድሩ በቅርቡ ይካሄዳል ተብሎ እንደሚጠበቅ አስታውቋል ። ድርድሩም እዚያው ዶሃ ይሆናል ተብሎ ነው የሚታሰበው ። ትንሽቷ ቀጠር በተደጋጋሚ ጊዜያት በዓለም ዓቀፍ አደራዳሪነት የምትጫወተው ሚና ከፍተኛ ነው ። በስፋት ከጀርመኑ የሄሰን ፌደራዊ ክፍለ ሃገር ግማሽ ያህል የምትሆነው ቀጠር ከመካከለኛው ምሥራቅ ተሰሚነት ያላት ሃገር ናት ። ከ 10 ዓመታት አንስቶ ቀጠር በየአካባቢው የሚከሰቱ ግጭቶችን ስትሸመግል ቆይታለች ።

የዶሃው አዲሱ የታሊባን ቢሮምስል Reuters

በዚህ ረገድ የየመን የሶማሊያ የሊባኖስ የዳርፉርና የቻድ ግጭቶችን ለመፍታት የተጫወተችው የሽምግልና ሚና በምሳሌነት ይጠቀሳል ። ይህ ሚናዋ እየተጠናከረ የመጣውም በብሩኪንግስ የዶሃ የጥናት ማዕከል ባልደረባ ሻዲ ሃሚድ እምነት ሃገሪቱ ፣ ከእስራኤል ከሃማስ ከቴህራን እንዲሁም ከዋሽንግተን ከታሊባንና ከአፍጋኒስታን ፕሬዝዳንት ሃሚድ ካርዛይ ጋር ለመነጋገር ዝግጁ ሆና በመገኘትዋ ነው ።«ቀጠር ለብዙ ዓመታት አዳዲስ ሃሳቦችን ያካተተ ፣ ገለልተኛ ና ልዩ የውጭ መርህ አላት ። ያ ነው ለቀተር በዓለም ውስጥ ልዩ ቦታ የሚያሰጣት ። ቀተር ግጭቶችን በገለልተኛ መንገድ ለመፍታት በ ምታደርገው ሙከራ መቀጠሏ ትርጉም አለው ። ቀተር ለዚህ ወይም ለዚያኛው የወገነች ሆና ለመታየት አትፈልግም ። እንደሚመስለኝ ይህ ቀተርን ይጠቅማል ። ይህን ማድረግም ትፈልጋለች ። ለማንም ያልወገነ ገለልተኛ አቋም መያዝ ነው የምትፈልገው ።»በአፍጋኒስታኑ የሰላም ንግግር ቀጠሮች ለማንም አልወገኑም ። ሆኖም ከአሜሪካን ጋር ወታደራዊ አጋር ናቸው ፤ ከታሊባን አንጃዎች መካከል ቢያንስ የአንዱን አመኔታ ማግኘታቸው ያስደስታቸዋል ።

ሼክ ሃማድ ቢን ያሲም አልታኒምስል Reuters

ይህ ደግሞ አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችልና ረዥም ጊዜ እንደሚወስድም ለሚገመት ንግግር ገለልተኛ ሚና መጫወት ያስችላቸዋል ። ቀጠር ገለልተኛ የውጭ መርህ ልትይዝ የመቻልዋ ምክንያት ሃብታም፣ የዓለም ዋነኛዋ ነዳጅ ዘይት አምራች ና ሻጭ ሃገር በመሆንዋ ነው ይላሉ RUSI የተባለው የዶሃ የጥናት ተቋም ባልደረባ ማይክል ስቴፈንስ «ካታር እጅግ ብዙ ገንዘብ ያላት ሃገር ናት ። በገንዘቡ ምን ማድረግ እንዳለባት በርግጥ አታውቅም ። ገንዘቡን በተለይ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችሉ መንገዶች ለማመቻቸት ልትጠቀምበት ትችላለች ። ያንንም ታደርጋለች ። በምትንቀሳቀስባቸው ሃገሮች የብዙሃኑን አመለካከት ይወክላሉ ብላ የምታስባቸውን ንቅናቄዎች ወይም የፖለቲካ ፓርቲዎች በገንዘብ ለመደገፍ ትሻለች ። »

ዋነኛው የጉዳዩ አንቀሳቃሽ የ53 ዓመቱ የቀጠር ጠቅላይ ሚኒስትርና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሼክ ሃማድ ቢን ያሲም አልታኒ ናቸው ። አልታኒ ጠንካራ ስብዕናና ተስጥኦ ያላቸው ፖለቲከኛ ና የተካኑ ዲፕሎማትም ጭምር ናቸው ። ማይክል ስቴፈንስ እንደሚሉት ቀጠሮች ድርድሮች እንዲካሄዱ የሚያደርጉባቸው መንገዶች ይለያሉ ።

« አንዳንድ ጊዜ ቀጠሮች እጅግ የከረረ ጠብ ያላቸውን አንጃዎች ያደራድራሉ ። በሮቹን ዘግተው አንድ መግባቢያ ላይ እስክትደርሱ ድረስ እዚሁ እንቀመጣለን ይላሉ ። ይህን ለማድረግ የሆነ ጥንካሬ ያስፈልጋል ። »

የሱዳን መንግሥትና ና የሱዳን የፍትህና የነፃነት ንቅናቄ ስምምነት በዶሃምስል picture-alliance/dpa

አንዳንዴ ግጭቶች ሰላማዊ መፍትሄ ሲታጣላቸው ውዝግብን በወታደራዊ ኃይል ለመፍታት ነው ጥረት የሚደረገው ። ለዚህም ሶሪያና ሊቢያ ምሳሌዎች ናቸው ። ቀጠር በውጭ መርኋ መሰረት ግጭቶችን ለማስወገድ የምታደርጋቸው ጥረቶች በሙሉ ተሳክተዋል ማለት አይቻልም ። ምንም እንኳን ቀጠር የሶሪያ ተቃዋሚ ወገኖችን በትጋት የምትደግፍ ቢሆንም በሶሪያም ይህን ነው የሚባል ውጤት አልተገኘም ። ይህ የቀተር የውጭ መርህ እንደ እስካሁኑ ላይቀጥል ይችላል ። እንደሚሰማው ከሆነ የቀተሩ አሚር ሼክ ሃማድ ቢን ካሊፋ ጤና በማጣታቸው ከሥልጣናቸው ሳይነሱ አይቀርም ። እንደ መጀመሪያ ደረጃ ተደርጎ የሚወሰደው የሚተካቸው ወንዱ ልጃቸው ሼክ ታሚም የጠቅላይ ሚኒስትርነቱንም ቦታ እንዲይዙ ማድረግ ሳይሆን አይቀርም ። በዚህም ቀጠር ታታሪና አስተዋይ ታዋቂ ዋና ዲፕሎማትዋን ታጣላች ። ሼክታሚም እንደሚተኳቸው ባለሥልጣን ፣ ተግባራቸውን ያካሂዳሉ ተብሎ የሚጠብቅ የለም ። ታሚም የ 33 ዓመት ጎልማሳ ናቸው ። እድሜ ትልቅ ሚና በሚጫወትበት በአረቡ ዓለም የሼክታሚ እድሜ ለሽምግልና ብቁ አያደርጋቸውም ።

ሂሩት መለሰ

አርያም ተክሌ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW