1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቀጣዩ ክትባት የኤች አይ ቪ ኤድስ ይሆን?

ረቡዕ፣ ሐምሌ 14 2013

የኤች አይ ቪ ኤድስ ከተከሰተ አራት አስርተ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ተመራማሪዎች የተሳካ የመከላከያ ክትባት ገና አላገኙም። የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ግን ሁለት አመት  ባልሞላ ጊዜ  ስምንት ክትባቶችን ማበልፀግ ተችሏል። ይህም ኤች አይ ቪን የሚከላከል ክትባት ለማበልፀግ  በተመራማሪዎች ዘንድ ተስፋና መነቃቃት ፈጥሯል።

Bangladesh | Welt AIDS Tag
ምስል Suvra Kanti Das/Abaca/picture alliance

ቀጣዩ ክትባት የኤች አይ ቪ ኤድስ ይሆን?

This browser does not support the audio element.

 

የኤች አይ ቪ ኤድስ ከተከሰተ አራት አስርተ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ተመራማሪዎች የተሳካ የመከላከያ ክትባት ገና አላገኙም። የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ግን ሁለት አመት  ባልሞላ ጊዜ  ስምንት ክትባቶችን ማበልፀግ ተችሏል። ይህም ከ35 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገውን ኤች አይ ቪ ን  የሚከላከል ክትባት ለማበልፀግ  በተመራማሪዎች ዘንድ ተስፋና መነቃቃት ፈጥሯል።  እንዲያ ከሆነ ቀጣዩ ክትባት የኤች አይቪ ኤድስ ይሆን?


የኤች አይ ቪ / ኤድስ ወረርሽኝ ከተከሰተ አራት አስርተ ዓመታትን ቢያስቆጥርም ተመራማሪዎች የተሳካ የመከላከያ ክትባት  ገና  አላገኙም። የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ወዲህ ግን ሁለት  አመት  ባልሞላ ጊዜ  ስምንት የኮቪድ -19  መከላከያ ክትባት ማበልፀግና ማምረት ተችሏል። ይህም በዓለም ዙሪያ  ከ35 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገውን ኤች አይ ቪ  ኤድስን መከላከል የሚያስችል ክትባት ለማበልፀግ  በዘርፉ ተመራማሪዎች ዘንድ ተስፋና መነቃቃት ፈጥሯል።እንዲያ ከሆነ ቀጣዩ ክትባት የኤች አይቪ ኤድስ ይሆን? የዛሬው የሳይንስና ቴክኖሎጅ ዝግጅት ፣ በሂደት ላይ ያሉ የኤችአይቪ ክትባቶችን ፣ በኤችአይቪ ክትባት ላይ እየታዩ ያሉ  አዳዲስ ተስፋዎችን እንዲሁም  ከኮቪድ -19 የክትባት ሂደቶች የተገኙ ተሞክሮዎችን ይቃኛል።
የኮቪድ-19 በሽታ ከተከሰተ ወዲህ ተመራማሪዎች ባለፉት 18 ወራቶች ብቻ ከ 32 በላይ  የመከላከያ ክትባቶች ወደ ሦስተኛ ደረጃ ክሊኒካዊ ሙከራዎች እንዲደርሱ አድርገዋል። ስምንት የሚሆኑት ደግሞ ማረጋገጫ አግኝተው  እንዲመረቱ ተደርጓል። ሌሎች 90 ክትባቶች ደግሞ በመጀመሪያና ሁለተኛ ደረጃ  ሙከራ ላይ  ይገኛሉ ፡፡ 
በአንፃሩ ሊቃዉንቱ ላለፉት 40 ዓመታት ባደረጉት ምርምር -ሰዎችን ከኤች አይ ቪ  ኤድስ ለመከላከል የሚያስችል አስተማማኝ እና ውጤታማ ክትባት ማግኘት አልቻሉም፡፡ ተመራማሪዎቹ  በኤች.አይ.ቪ ላይ ላለፉት 37 ዓመታት ባደረጉት ምርምር  ወደ ሦስተኛ ደረጃ ክሊኒካዊ ሙከራ መድረስ የቻሉት  ስምንት ክትባቶች ብቻ ናቸው። ፡ይህም ከኮቪድ-19 ጋር ሲነፃፀር እዚህ ግባ የሚባል አይደለም።በዚህ የተነሳ ተመራማሪዎች በዘርፉ ሲደረግ የነበረውን ጥናትና ምርምር ማጤንና መጠየቅ ጀምረዋል።
የጀርመን የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከያ ማዕከል ዋና ዳይሬክተርና በቦን ዩንቨርሲቲ የተዋህሲያን ተመራማሪ  የሆኑት ፕሮፌሰር ሄንድሪክ ሽትሪክ  የፖለቲካ ቁርጠኝነትና የገንዘብ ድጋፍ  ካለ  ምርምሩን ለማካሄድ መፍጠን  ይቻላል።ባይ ናቸው ።ይህንንም ከኮቪድ-19  የክትባት ሂደት መመልከት ችለናል  ይላሉ።
« የኮቪድ- 19  ወረርሽኝ  በፍጥነት  እና በከፍተኛ ደረጃ ልንያዝ እንደምንችል እና አዲሱን ተዋህሲ  ለመዋጋት መፍጠን እንደምንችልም አሳይቶናል። በተጨማሪም  የሳይንሱ ማህበረሰብ በአጭር ጊዜ  የክትባት ማረጋገጫ ፈቃድ ማግኘትና 30 በሚሆኑ ክትባቶች ላይ ጥሩ ሙከራ ማድረግ  እንደሚችል አሳይቶናል። በተቃራኒው  በ 30 ዓመታት ውስጥ በኤች አይ ቪ ኤድስ ላይ በስምንት  ክትባቶች ብቻ ሙከራ ተደርጓል። አስቡት  የሰውን አቅም አሰባስበን  መነሳት ከቻልን  በእውነቱ ለ«ኤች አይ ቪ  ኤድስ»ም ተመሳሳይ ነገር መስራት እንችላለን ፡፡»ብለዋል።
ሽትሪክ እንደሚሉት  ምንም እንኳን የኤችአይቪ ክትባት ምርምሮች  እስካሁን ስኬታማ ባይሆኑም ሙከራዎች የሉም ማለት  ግን አይደለም። እንደ እሳቸው  ገለፃ መቶ ሚሊዮን ዶላር ወጪ የተደረገባቸውና የ1ኛ ደረጃ ክሊኒካዊ ሙከራዎች የተካሄደባቸው ከ 400 በላይ የኤች አይ ቪ  እጩ ክትባቶች ነበሩ። 
ምንም እንኳ የኮሮና ወረርሽኝ ከተከሰተ ከጎርጎሪያኑ ከታህሳስ 2019 ዓ/ም ጀምሮ ዓለም ትኩረቱን እና ገንዘቡን ወደ ኮቪድ-19 ክትባት ፍለጋ ያዞረ ቢሆንም፤ የመከላከያ ክትባቶቹ ግኝት  መለያየት ከፖለቲካ  ቁርጠኝነትና ከገንዘብ ድጋፍ ብቻ ሳይሆን  ከሁለቱ ተዋህሲያን  የባህሪ ልዩነት  ጋር  የተያያዘ ጭምር መሆኑን ይገልፃሉ ተመራማሪው።
እንደ ተመራማሪው ኮቪድ-19 በሽታን የሚያስከትለው የኮሮና ተዋህሲ  እና «ኤች አይ ቪ »በአወቃቀራቸውም  ይሁን  በውስብስብነታቸው ሊነፃፀሩ የማይችሉ ናቸው።   
የኮሮና ተዋህሲ  የመለዋወጥ ባህሪው አነስተኛ  ሲሆን በአንፃሩ፤ የኤች አይ ቪ ተዋህሲ   በጣም ተለዋዋጭ ነው።  ያ በመሆኑ ተዋህሲው ሰውነት የኤች አይ ቪ ተዋህሲ   ውጤታማ የሆነ የበሽታ መከላከያ ምላሽ እንዳይሰጥ ያደርገዋል። ከዚህ በተጨማሪ  ውጤታማ ክትባት ለማዘጋጀት የሚደረገውን ምርምር አስቸጋሪ እንዳደረገው በደቡብ አፍሪቃ የካፕሪሳ የኤችአይቪ ኤድስ የክትባት ምርምር  ተቋም ሀላፊ  ናይግል ጋሬት ይናገራሉ።
«ይህ  በግልፅ በዓለም ዙሪያ  ሁሉንም የሚያጠቃ ወረርሽኝ ነበር። እናም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከፍተኛ ጥረት እና ከፍተኛ ንቅናቄ ነበር። ስለሆነም ብዙ የኤች አይ ቪ ተመራማሪዎችም እነዚህን የኮቪድ-19 ሙከራዎች ለማከናወን እገዛ አድርገዋል። ምክንያቱም በዓለም ዙሪያ ቀድመው የተዋቀሩ  ክሊኒካዊ የሙከራ መድረኮች ነበሩና።ከኤች አይ ቪ አንጻርም ቢሆን  ባለፉት ዓመታት የገንዘብ ድጋፍ ተደርጓል። ነገር ግን የኤችአይቪ ክትባት ለማግኘት በጣም አስቸጋሪ ነበር። ኮቢድ-19ን በሚመለከት ግን «ስፓይክ ፕሮቲን» የተባለ ንጥረ ነገር በተዋህሲው ውስጥ በማግኘታችን ትክክለኛውን ዒላማ ለመምታት በጣም ዕድለኞች ነበርን። እናም ተዋህሲው የራሱን ህዋሳት ለማያያዝ የሚጠቀምበትን «ስፓይ ፕሮቲን» የሚፃረሩ  በጣም ጠንካራ ፀረ እንግዳ አካላትን መጠቀም ችለናል። ይህ በኤች አይ ቪ ተዋህሲ በጣም የተወሳሰበ ነው።» በማለት ተናግረዋል።
መረጃዎች እንደሚያሳዩት ብዙ ክትባቶች የሚሠሩት ወደ ሰውነት  የሚገቡ ባዕድ ወራሪዎችን የሚዋጉ ፀረ እንግዳ አካላት ፕሮቲኖችን  በማነቃቃት ነው ፡፡ ነገር ግን የዚያ ጥቃት ዒላማ ያለማቋረጥ መልኩን የሚቀይር ከሆነ  ለመዋጋት በጣም አስቸጋሪ  ነው።
ከዚህ አንፃር የኮቪድ-19  ተዋህሲ ለክትባት ቀላል ዒላማ መሆኑን  በሎንዶን የኢምፔሪያል የህክምና ኮሌጅ ዲንና የረጅም ጊዜ የኤች አይ ቪ ተመራማሪ ጆናታን ዌበር  ገልፀዋል።
 የክትባት ተመራማሪዎች -« ቫይራል ቬክተር» ፣ «ኤም አር ኤን ኤ» እና «አድኖቫይረስ» በተባሉ የምርምር ዘዴዎች የተደረጉ የኮቪድ-19 የክትባት ሙከራዎች  እንደ  ተመራማሪው ዌበር  ሁሉም ውጤታማ ሆነዋል። ነገር ግን በኤችአይቪ ተዋህሲ ተለዋዋጭ ባህሪ  የተነሳ  እነዚህ ሁሉ ዘዴዎች  ተሞክረው የተሳኩ አልሆኑም ፡፡ የኤችአይቪ ክትባት ሙከራዎች እንዲሁ ረዘም ያለ ጊዜ የሚወስዱ ናቸው ፣ ምክንያቱም  ተመራማሪዎች የሚመረቱት ክትባቶች በኤች አይ ቪ እንዳይያዙ ሊያደርጉ ይችሉ እንደሁ ተከታታይ ሙከራ ይፈልጋሉ።  
ያም ሆኖ ጋሬት እንደሚሉት  ኮቪድ-19ን ለመከላከል ጥቅም ላይ በዋሉ  ሁለት ክትባቶች አሁንም ሙከራ እየተካሄደ ነው። 
«በአሁኑ ጊዜ  በመካሄድ ላይ ያሉ ሁለት  የኤች አይ ቪ ክትባት ሙከራዎች አሉ። በሚገርም ሁኔታ በ«ጆንሰን ኤንድ ጆንሰን» በመባል በሚጠራው የኮቪድ-19  ክትባት  ጥቅም ላይ የዋለውን የ« አዴኖቫይረስ ቬክተር»  ዘዴ  ይጠቀማሉ። እንደሚታወቀው የ «ኤም አር ኤን ኤ» /MRNA/ ቴክኖሎጂ  አዲስ ሲሆን ለኮቪድ-19  ክትባት ሆኖ አገልግሏል። ነገር ግን «ኤች አይ ቪ»ን በሚመለከት  እስካሁን በሰዎች ላይ ገና አልተሞከረምና በእውነቱ ያንን በጉጉት እንጠብቃለን።»ነው ያሉት።
ኤች አይቪን በተመለከተ እስካሁን «ኡሃምቦ»/Uhambo/የተባለ አንድ  ክትባት ብቻ በሰዎች ላይ በተደረገ  ሙከራ  ከፊል መከላከልን  ያሳየ ቢሆንም፤ በቅርቡ በደቡብ አፍሪካ በተደረገው ሰፊ ሙከራ ብዙም ውጤታማ አለመሆኑ እየተገለፀ ነው ፡፡
በሌላ በኩል  «ፕሪፕቫክ»/Prepvacc / እና «ሞዛይኮ» / Mosaico/ በተባሉ ሌሎች ሁለት  ክትባቶች ላይ   በአሁኑ ጊዜ በደቡብ አፍሪካ ፣ታንዛኒያ እና ኡጋንዳ ሙከራ እየተካሄደባቸው ይገኛል። ሞዛይኮ በ«አዴኖቫይረስ»በተባለው  የክትባት ማበልፀግ ዘዴ ላይ የተመሠረተ ሲሆን ከብዙ የኤች አይ ቪ ተዋህሲ ዝርያዎች የተወሰዱ ፕሮቲኖችን በማጠናከሪያነት የያዘ ነው ፡፡
ይህም ከጆንሰን እና ጆንሰን ፣ ከኦክስፎርድ-አስትራዛኔካ እና ከሩስያ ስፑኒክ  COVID-19 ክትባቶች ጋር ተመሳሳይ ነው።።«ፕሪፕቫክ» ደግሞ ከፕሮቲን በተጨማሪ የተዋህሲውን «ዲ ኤን ኤ »  ጭምር የያዘ ነው።
የምርምር ቡድኑን  በመምራት የተሳተፉት ፕሮፌሰር ሽትሪክ  ክትባቱ በእንስሳት  ላይ ተሞክሮ ተስፋ ሰጪ ውጤት ካሳየ ወዲህ  ክትባቱ  በተመራማሪዎቹ ዘንድ ተስፋ አሳድሯል ብለዋል። የሽትሪክን ሀሳብ  ሌላኛው ተመራማሪው ናይግል ጋሬትም ይጋሩታል።
« እንደ ብዙዎቹ የሥራ ባልደረቦቼ  በቴክኖሎጂው እጅግ በጣም ደስተኛ ነኝ። የተወሰኑ ዝግጁ  የሆኑና በእንስሳት ላይ የተደረጉ ጥናቶች ነበሯቸው፡፡ ከእነዚህ የ«ኤም አር ኤን ኤ »ጅምር ክትባቶች ውስጥ  «ኤች.አይ.ቪን»  ለመከላከል የተወሰኑ  ውጤቶችን አሳይተዋል። ስለዚህ የኤች አይ ቪ ክትባትን በቅርቡ ለማግኘት የሚያግዝ ትልቅ ተስፋ አለን ብዬ አስባለሁ።»በማለት ገልፀዋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በክትባቱ ዘርፍ ስሙ ተደጋግሞ የሚነሳው ግዙፉ የአሜሪካ የክትባት አምራች  ኩባንያ ሞደርና በሁለት የኤች.አይ.ቪ ክትባቶች ላይ ምርምር እያደረገ  ነው ፡፡ የመጀመሪያው  «ኤም አር ኤን ኤ- 1644» ተብሎ የሚጠራው ዕጩ ክትባት  በጎርጎሪያኑ 2021 መጨረሻ ላይ የመጀመሪያ ደረጃ ሙከራዎችን ይጀምራል ተብሎ ይጠበቃል ፡፡
ሁለተኛውና «ኤም አር ኤን ኤ -1574» በመባል የሚታወቀው ደግሞ ከአሜሪካ  ብሔራዊ የጤና ተቋማት (NIH) ጋር በመተባበር ምርምር እየተደረገበት ነው ተብሏል፡፡ የአሜሪካ  ብሄራዊ የጤና ተቋም የበሽታ መከላከል ባለሙያ የሆኑት ፔንግ ዣንግ  ይህ ክትባት በዝንጀሮዎች ላይ ተሞክሮ  ተመራማሪዎች ተስፋ ሰጪ ውጤት ማየታቸውን ተናግረዋል ፡፡
ተመራማሪዎቹ እንደሚሉት አሁንም ድረስ በ«ኤም አር.ኤን.ኤ.» ክትባት የኤች.አይ.ቪ ተዋህሲን የሚመክት « አንቲጂን» ወይም ፀረ-ዘረመል ያለማግኘት ችግር አለ። ያም ሆኖ መሰናክሎችን ተሻግሮ  ደህንነቱ የተጠበቀ እና ውጤታማ የኤች.አይ.ቪ ክትባት እንደሚያበለፅጉ ተመራማሪዎች ተስፋ ሰንቀዋል።ምክንያቱም አሁን ሊቃውንቱ ከኮቪድ-19  ክትባት ሂደትና ፍጥነት  ትምህርት አግኝተዋል ፡፡ እናም ባለፉት 40 ዓመታት በዓለም ዙሪያ ከ 35 ሚሊዮን በላይ ሰዎችን ለህልፈት የዳረገውን ኤች.አይ.ቪ ኤድስ ለመግታት ይህንን ፍጥነት መጠቀም ይፈልጋሉ።ፕሮፌሰር ሂንድሪክ ሽትሪክም እርግጠኛ ናቸው። የሳቸው ጥያቄ በምን ያህል ፍጥነት  የሚለው ብቻ ነው።
«ስለዚህ ፣ ከሁሉ አስቀድሞ የኮቪድ -19  ምላሽ ከኤች አይ ቪ ኤድስ የዓመታት ምርምር የተቀዳ ለመሆኑ ምንም ጥርጥር የለውም። ለምሳሌ የ«አዴኖቫይረስ»  ዘዴ  ለ«ኤች አይ ቪ » የተሰራ ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በዚህ ዘዴ  የ«ኤች አይ ቪ»    ክትባቶችን  ለማረጋገጥ የሚጠቀሙ ሁለት ሙከራዎች ቀጥለዋል።  በዝንጀሮዎች ላይ ተሞክረውም ተስፋ ሰጭ ውጤቶችን አሳይተዋል።ስለዚህ ውጤታማ የሆነ ክትባት ማግኘት ይቻላል ብዬ አስባለሁ። ነገር  ግን አዳዲስ ነገሮችን  በመሞከር ፣ ትልቅና የሚታይ  ግኝት ላይ በማተኮር፤ ኤች አይ ቪ  ኤድስን ለመግታት  መጣር አለብን። እንደሚቻል አውቃለሁ። ጥያቄው እኛ ምን ያህል ፈጣን ነን? የሚለው ነው። »ብለዋል።
ከኮቪድ -19 የክትባት ሂደቶች የተገኙ ተሞክሮዎች፣ በሂደት ላይ ያሉ የኤችአይቪ ክትባቶች  እና በኤችአይቪ ክትባት ላይ እየታዩ ያሉ  አዳዲስ ተስፋዎችን የቃኘንበት ዝግጅት በዚህ ተጠናቋል። መልካም ጊዜ።

ምስል Frank Hoermann/SVEN SIMON/picture alliance
ምስል Saikat Paul/Pacific Press/picture alliance
ምስል Science Photo Library/imago
ምስል AP

 

ፀሀይ ጫኔ
ሂሩት መለሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW