ቁጣን ያስከተለው የደራ ኢማም ግድያ
ሰኞ፣ ጥቅምት 25 2017ቁጣን ያስከተለው የደራ ኢማም ግድያ
በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ደራ ወረዳ አድዓ መልኬ ቀበሌ የገንዳ አረቡ መስጅድ ኢማም ሼህ ሙሐመድ መኪን ሐጂአረፉ በሳምንቱ መጨረሻ በታጣቂዎች ከታገቱ ከሳምንታት በኋላ መገደላቸው የአከባቢውን ማህበረሰብ ማስቆጣቱ ተነግሯል፡፡ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ ጉዳዩን በቅርበት የተከታተሉ የአከባቢው ነዋሪ አስተያየት ሰጪ አከባቢው ላይ ተከታትሎ በመፈጸም አላቧራ ያለው እገታ እና ተያያዥ በደሎች በአከባቢው ማህበረሰብ ላይ ወትቶ መግባትንም ከባድ አድርጓል፡፡
ነዋሪነታቸውን ደራ-ወረዳ ጉንዶመስቀል ከተማ ያደረጉ አስተያየት ሰጪ፤ ከሰሞኑ ኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከደራ ወረዳ ከተሰማው አስደንጋጭ የመስጊድ ኢማም ግድያ ከ3 ሳምንታት የእገታ ጊዜ በኋላ የተፈጸመ ስለመሆኑ አስረድተዋል፡፡ በወረዳዋ ከተማ ጠረፍ፤ላይ አረቡ በምትባል አከባቢ ስኖሩ የነበረው የመስጊድ እማም የሃይማኖት መሪ ከበርካታ ቤተሰቦቻቸው ጋር ታግተው ከቆዩ በኋላ ያገቷቸው ታጣቂዎች ህልፈታቸውን ለቤተሰብ ያረዱት ከቀናት በፊት በባለፈው ሳምንት የመጨረሻ ቀናት ነው፡፡
“በኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ተገድለው ከተወሰዱሶስት ሳምንታት ግድም ሆኗቸዋል፡፡ ከመስጊድ ውስጥ የታገቱትም በአከባቢው ከሚኖሩ ቁጥራቸው 14 ግድም ከሚሆኑ ሰዎች ጋር ነበር፡፡ እናታቸውና ባለቤታቸው ከሳቸው ጋር ከታገቱት መካከል ይገኛሉ፡፡ ባለቤታውን ወዲያው ነበር ያለምንም ክፍያ ለቀቋቸው፡፡እናታቸውንና እሳቸውን ለመልቀቅ ግን አጋቾች 1.5 ሚሊየን ብር ጠይቀውባቸው ነበር፡፡ ከተጠየቀው ይህን መጠን ያለው ገንዘብ 1.2 ሚሊየን ግድም የሚሆነው ተከፍሎ እናታቸው ተለቀዋል፡፡ ሌሎች ከሳቸው ጋር የታገቱ ሰዎችም ከ100-300 ሺህ ብር በነፍስ ወከፍ እየከፈሉ ተለቀዋል፡፡ እሳቸውን ግን ለማስለቀቅ ቀሪው ገንዘብ በቤተሰብ እየተፈለገ ባለበት ነው ተገድለዋል በሚል ልብሳቸው የተላከው፡፡ አሁን ከቅዳሜ ጠዋት ጀምሮ ቤተሰብ ኢዚሁ ከተማ ውስጥ ለቅሶ ተቀምጠዋል” ብለዋል፡፡
የኢማሙ መገደል ያስከተለው ማህበረሰባዊ ቁጣ
እንደ አስተያየት ሰጪ የአይን እማኙ መረጃ ሼሁ የመስጊድ ኢማም ታግተው እስከ መገደል ያደረሳቸው በደል አይታወቅም፡፡ ቤተሰብ ግን በአጋቾች የተጠየቀውን ቀሪ ገንዘብ በመሙላት እሳቸውን በነፍስ ለማግኘት ላይ ታች ሲል ነበር ነው ያሉት፡፡ እሳቸውን ጨምሮ በርካቶች በታገቱበት የወረዳ ከተማዋ ጉንዶመስቀል አዋሳኝ የገጠር ቀበሌያት አከባቢ ተደጋጋሚ እገታዎች መበራከቱንም አክለው አስረድተዋል፡፡ የአሁኑ የሹህኩ ግድያ ደግሞ ማህበረሰቡን ያስደነገጠና ያስቆጣም ነው ብለዋል፡፡ “ሼህኩ ከታገቱበት እለት ጀምሮ በርካታ የአከባቢው ማህበረሰብ ቤታቸውን ለቀው በመውጣት ወደ ከተማ ተሰደዋል፡፡ አሁንም ማህበረሰቡ እየጠየቀ ያለው በአከባቢው የኬላ ጥበቃ አንዲጠናከርና መንግስት ማህበረሰቡን እንዲያደራጅ ነው፡፡ የኢማሙ መገደል ግን በከተማዋና አከባቢው ከፍተኛ ቁጣን ቀስቅሷል፡፡ አንድም የሃይማኖት አባት መሆናቸው
ሁለትም ይህን ያህል ከፍተኛ ገንዘብ ተከፍሎ ጭምር መሰል ግድያ የተለመደ ነገር ስላልሆነ እንግዳ ነው የሆነብን” ነው ያሉት፡፡
ግድያው በተለየ መልኩ በማህበራዊ መገናኛም በከፍተኛ ሁኔታ የተጋራው ብዙዎችን በማሳዘን ነው፡፡ እናት ፓርቲ የኢማሙ ከ12 የቅርብ ሰዎቻቸው ጋር ታግተው መቆየትና ኋላም መገደላቸውን አውግዟል፡፡ አካባቢው ላይ ከፍተኛ “ማንነት ተኮር ጭፍጨፋ”ይፈጸማል ሲል የከሰሰው እናት ፓርቲ “ግፉ በመገናኛ ብዙኀን እንዳይነገር” ሆኗል ሲል ወንጅሏልም፡፡
የደራ ወረዳው ሰፊ የጸጥታ ችግር ጥያቄ
በኦሮሚያ እና አማራ ክልሎች አስተዳደራዊ ወሰን ላይ በአስቸጋሪ የመሬት አቀማመጥ ላይ እንደምትገኝ የምነገርላት ደራ ወረዳ ባለፉት ሁለት ዓመታት ፈታኝ የተባለለት የጸጥታ ይዞታን እያስተናገደች ስለመሆኗ ይነገራል፡፡ ወረዳዋ ጠመንጃን ያነገቡ ሁለት ታጣቂ ኃይሎች እንዳሻቸው የሚመላለሱባት ስለመሆኗም ነዋሪዎቻ ያስረዳሉ፡፡ “በዚህ ወረዳ ሁለት ኃይሎች እንዳሻቸው ይንቀሳቀሳሉ፡፡ አንዱ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ሲሆን አሁን ካለፈው ዓመት ጀምሮ ደግሞ ፋኖ የተባለው ኃይልም በተወሰኑ ቀበሌያት ላይ ይንቀሳቀሳል፡፡ አንደኛው ሸማቂ ቡድን እገታ ላይ ስያተኩር ሌላኛው ደግሞ አጋጣሚውን ሲያገኝ ፊትለፊት ይዘርፋል፡፡ እናም ወረዳዋ እንዲህ በሁለቱ ኃይሎች ስትፈተን እስካሁንም እልባት አላገኘምና ከጊዜ ወደ ጊዜ ወጥቶ መግባት ፈተና ሆኗል” ብለዋል፡፡
በቅርቡ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የወረዳው ዋና አስተዳዳሪ አቶ ከፍያለው አደሬ ነዋሪዎቹ ተማረንበታል ያሉትን የጸጥታው ፈተና መኖሩን አልሸሸጉም፡፡ ይሁንና ይላሉ አስተዳዳሪው፤ “ሰላም በሌለበት የሚሳካ አንዳችም ነገር አይኖርም፡፡ ያንን ለመለወጥ ነው እየሰራን ያለነው፡፡ አሁን ያለውን የጸጥታውን ችግር መለወጥ የምቻለው በመጠየቅ ብቻ ሳይሆን እያንዳንዱ ሰው የመንግስትን መዋቅር እየደገፈ ሰላምን ለማረጋገጥ አስተዋጽኦ በማበርከት ብቻ ነው የሚሆነው፡፡ ልዩነት እንኳ ብኖር ህዝቡ ለጋራ ሰላም መተባበር አለበት” ነው ያሉት፡፡
የመልካም አስተዳዳር ጥያቄ
ነዋሪዎች ግን በአከባቢው አለ ያሉትን የመልካም አስተዳደር ችግርንም ጭምር ያነሳሉ፡ “እስከ ኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አስተዳደር ቅሬታችንን በተደጋጋሚ አንስተናል፡፡ በመገናኛ ብዙሃንም ብዙ ጊዜ ችግራችን እያነሳን ነው፡፡ የአከባቢው ባለስልጣናት በግልጸንነት ያለውን ችግር ስታነሳ ወደ እስር ቤት ማጋዝ ነው ምላሻቸው፡፡ ክልሉም ያለውን የመልካም አስተዳደር ችግር ለምን መፍታት እንደተሳነው አናውቅም” ብለዋል፡፡አክለውም “ሰሞኑን እንኳ በከባባድ መሳሪያ የታገዘ ውጊያ እየተደረገ በመሆኑ መውጣትም ከብዷል፡፡ በተለይም ያለፉትን አምስት ቀናት ሰው ከከተማው አይወጣም፡፡ ይህን መንግስም ያውቃልና ከባድ ነው” ብለዋል፡፡
የተራዘመው የኦሮሚያ ግጭት ባለፈው ሳምንት ከምስራቅ ሸዋ ዞን ዱግዳ ወረዳ እና ሰሜን ሸዋ ዞን ወጫሌ ወረዳም በተሰሙ ከባባድ ግድያዎች ዳግም ከፍተኛ ስጋት መደቀኑ ይታወቃል፡፡ በተለይም ለሰሜን ሸዋው
ወጫሌ ወረዳ መንግስት ሸነ ያለውና እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነሰ) ብሎ የሚጠራው ታጣቂ ቡድን ኃላፊነት መውሰዱም ይታወሳል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ