1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሜሊላ የአፍሪቃውያን ስደተኞች ሞት

ማክሰኞ፣ ሰኔ 28 2014

አርብ ሰኔ 17 ቀን 2014 ዓም በሜሊላ በደረሰው አደጋ ቢያንስ 23 ስደተኞች ሞተዋል።የሞሮኮ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ማኅበር የሞቱት ቁጥር 27 ነው ሲል «ዎኪንግ ቦርደርስ» የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የሟቾቹን ቁጥር 37 አድርሶታል። የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንዳስታወቀው ደግሞ በአደጋው 76 ስደተኞች ቆስለዋል።

Migranten in der spanischen Nordafrika-Exklave Melilla
ምስል Javier Bernardo/AP/dpa/picture alliance

በሜሊላ የአፍሪቃውያን ስደተኞች ሞት

This browser does not support the audio element.

ሜሊላ፣የጅብራልተር ሰርጥ ከስጳኝ ዋና ግዛት የሚለያት ፣ስፓኝን ብሎም የአውሮጳ ኅብረትን ከአፍሪቃ ጋር ከሚያዋስኑት ሁለት የስፓኝ ግዛቶች አንዷናት።85 ሺህ ነዋሪ ያላት ራስ ገዝዋ ሜሊላ 12 ሜትር ርዝመት ባለው የብረትና የሽቦ አጥር የተከበበች ከሞሮኮ ጋር የምትዋሰን ግዛት ናት።አጥሩ የተሰራው ስደተኞች እንዲገቡ ለመከላከል ነው። ከአንድ ሳምንት ወዲህ መገናኛ መገናኛ ብዙሀን የዚህችን ግዛት ስም በተደጋጋሚ ሲያነሱ ቆይተዋል። ሜሊላ ትኩረት የሳበችው ከዛሬ 10 ቀን በፊት ስጳኝኝ ድንበር ላይ ከሚገኘው ከሞሮኮው ናዶር፣ ወደ ከተማዋ ለመሻገር የሞከሩ አብዛኛዎቹ ከሰሀራ በታች ከሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት የመጡ ስደተኞች ሕይወት በአሳዛኝ ሁኔታ ካለፈ በኋላ ነው።  የሞሮኮ ባለሥልጣናት በዚህ ሳምንት ሞሮኮ ለሚገኙ የአፍሪቃ ሀገራት አምባሳደሮች ይፋ ያደረጉት ቪድዮ ፣ከሞሮኮዋ ናዶር በርካታ አፍሪቃውያን ግር ብለው ፣ሁለቱ ሀገራት ድንበር ላይ በሚገኝ ከላይ ኤሌክትሪክ ከተጠመጠመበት 12 ሜትር ርዝመት ካለው የብረት አጠር ላይ ተንጠላጥለው ወደ ሜሊላ ለመሻገር ሙከራ ሲያደርጉ ያሳያል። ብዙም ሳይቆይ ወደ አካባቢው የተጠጉት ድንበር ጠባቂ ኃይሎች ወደ ስደተኞቹ  አስለቃሽ ጢስ  ሲተኩሱ የተወሰኑት ወደ ኃላ አፈገፈጉ። በአጥሩ ላይ ተንጠላጥለው የነበሩት ስደተኞች ግን ወደ ሜሊላ ዘለው የመሻገር ሙከራቸውን ቀጠሉ። ይሁንና ድንገት የብረት አጥሩ ሲወድቅ ስደተኞቹም ከአጥሩ ጋር መሬት ላይ ተከሰከሱ። አርብ ሰኔ 17 ቀን 2014 ዓም በደረሰው በዚህ አደጋ ቢያንስ 23 ስደተኞችና ተገን ጠያቂዎች ሞተዋል።የሞሮኮ የሰብዓዊ መብቶች ተከራካሪ ማኅበር  የሞቱት ቁጥር 27 ነው ሲል «ዎኪንግ ቦርደርስ» የተባለው መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት ደግሞ የሟቾቹን ቁጥር 37 ከፍ አድርጎታል።የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት እንዳስታወቀው ደግሞ በአደጋው 76 ስደተኞች ቆስለዋል። የአፍሪቃውያኑ ስደተኞች ሞት ያስከተለው ቁጣና ተቃውሞ ከ10 ቀናት በኋላ አሁንም አልበረደም። 
የ23 ዓመቱ ተማሪ ካርሎታ ሽያቮን ሞሮኮን ከስፓኝ ጋር በምድር በምታዋስነው ሜሊላ ፣ቢያንስ የ23 ስደተኞች ሕይወት መጥፋቱን በመቃወም ባለፈው አርብ በባርሴሎና ከተማ በተካሄደ የአደባባይ ሰልፍ ላይ በመገኘት ቁጣቸውን ከገለጹት ውስጥ አንዱ ነው።      
«ይህ ትክክል አይመስለኝም።የቆዳ ቀለማቸው ምንም ይሁን ምን የሁሉም ሰው ሕይወት እኩል ዋጋ አለው።ይህን መሰሉ ዜናም ከሰለባዎቹ ዘር ጋር ሳይገናኝ እንደሌሎቹ ተመሳሳይ ተጽእኖ ሊኖረው ይገባል።»
አፍሪቃውያን ዳያስፖራዎችም በተገኙበት በከተማማዋ ማዕከል በተካሄደው የባርሴሎናው ሰልፍ በርካቶች ዘረኝነትንና ቅኝ አገዛዝን የሚቃወሙ መዝሙሮችን በማሰማት ጭምር ነበር ቁጣቸውን የገለጹት። ሌላው የሰልፉ ተካፋይ የ62 ዓመቱ ጡረተኛ ፌሊክስ ራቫል አደጋው ምክንያታዊ አይደለም ሲል ቁጭቱን አሰምቷል። 
«ይህን መታገስ አይቻልም።ይህ ከተለመደው የተለየ ነው። ዩክሬኖች በተለየ መንገድ እንክብካቤ ሲደረግላቸው የአፍሪቃውያን አያያዝ ግን የተለየ ነው።ይህ ትክክልም ምክንያታዊም አይደለም።»
ሰልፈኞቹ በአፍሪቃውያኑ ላይ የደረሰው አሳዛኝ አደጋ በገለልተኛ ወገን እንዲጣራም ጠይቀዋል።  የስፓኝ የሠራተኛ ሚኒስትርን የመሳሰሉ የማዕከላዊ መንግሥት ባለሥልጣናት እና የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት አደጋው እንዲጣራ ግፊት እያደረጉ ነው። የተመድ የሰብዓዊ መብቶች ምክር ቤት ሞሮኮና ስጳኝ ከሞቱት ሌላ 76 ስደተኞች የቆሰሉበትን የሜሊላውን አደጋ በገለልተኛ ወገን እንዲያጣሩ ጥሪ አቅርቧል። ምክር ቤቱ ሞሮኮም ስጳኝም የስደተኞችን ሰብዓዊ መብቶች እንዲያከብሩ ጠይቋል። የተመ የሰብዓዊ መብቶች ከፍተኛ ኮሚሽነር ቃል አቀባይ ራቪና ሻምዳስኒ 
«ሰኔ 17 ቀን ከሞሮኮ ወደ ስፓኝ ለመሻገር ሲሞክሩ  ቢያንስ 26 ሰዎች መሞታቸውና 76 ደግሞ መቁሰላቸው በጣም ረብሾናል። እንደ መጀመሪያ እርምጃ የአሟሟታቸውን የተፈጸመባቸውን ጥቃት ሁኔታ ለማወቅ ውጤታማና ገለልተኛ ምርመራ እንዲካሄድ ተጠያቂ ሊሆኑ የሚችሉትም ጉዳይ እንዲጣራ ለሁለቱም ሀገራት ጥሪ እናቀርባለን። ይህ በበርካታ ዓመታት ውስጥ ከሞሮኮ በስጳኞቹ ከተሞች ሜሊላና ሴኡታ በኩል አውሮጳ ለመሻገር በተደረገ ሙከራ በአንድ ቀን የተመዘገበ ከፍተኛ የሞቱ ሰዎች ቁጥር »
ይሁንና የስጳኙ ጠቅላይ ሚኒስትር  ፔድሮ ሳንቼዝ የሞሮኮና የስፓኝ መኮንኖች በስደተኞቹ ላይ የወሰዱትን የአጸፋ እርምጃ ተከላክለዋል፤ስደተኞቹ የፈጸሙትን በስጳኝ ድንበር ላይ የተቃጣ  ጥቃት በማለት ። ከአደጋው በኋላ በሰጡት መግለጫ ለድርጊቱ ተጠያቂ ያሏቸውን ይካሄድ ከተባለው ምርመራ አስቀድመው አሳውቀዋል።
«በመጀመሪያ በከተማይቱ የፀጥታ ኃይሎችና አካላት ለተከናወነው ድንቅ ስራ አድናቆቴን እገልጻለሁ።አንዳንዶቹ የሲቪል ጸጥታ አስከባሪዎች በአደገኛው ጥቃት ተጎድተዋል። ደግሜ መናገር የምፈልገው ጥቃቱ በስፓኝ ከተማ ውስጥ የሰው ልጆችን በሕገ ወጥ መንገድ ከአገር አገር በሚያሻግሩ ማፍያዎች የተቀነባበረ ነው። እናም ይህ በሀገራችን ሉዓላዊነት ላይ በአደገኛ ሁኔታ የተቃጣ ጥቃት ነው።»
ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ ማፍያ ያሉት ቡድን ሜሊላ ሊያስገባ የሞከረው ስደተኛ ቁጥር 2ሺህ ይደርሳል ብለዋል። የሞሮኮና የስፓኝ ባለስልጣናት በስደተኞቹ ተፈጸመ ባሉት ጥቃት፣ከሞሮኮ በኩል 140 የፀጥታ መኮንኖች ከስፓኝ  ወገን ደግሞ 60 የብሔራዊ ፖሊስና የሲቪል ጥበቃ መኮንኖች ጉዳት እንደደረሰባቸው ተናግረዋል። ስደተኞቹ በአጥር ተንጠላጥለው ወደ ሜሊላ ለመግባት ሲሞክሩ አስለቃሽ ጢስ በመተኮስ ሊያስቆሟቸው የሞከሩት የፀጥታ ኃይሎች ላይም ምንነታቸው ያልተገለፀ ነገሮችን ወርረውባቸዋል ብለዋል።  ይህ አስተያየት ሰጭ  ግን ድንበር ለማስጠበቅ ሲባል የሰዎች ሕይወት መጥፋቱን በጽኑ ተቃውመዋል።                                                                                                                                                       

ምስል Antonio Ruiz/europa press/dpa/picture alliance
ምስል Javier Bernardo/AP/dpa/picture alliance

«የስጳኝ ጠቅላይ ሚኒስትር የሞሮኮ ፖሊሲች የስፓኝ ድንበር የሚባለውን ለመጠበቅ አንድ ላይ እንደነበሩ አረጋግጠዋል።እኔ ግን የማስበው ይህ አይደለም። የሆነው ድንበራቸውን ለማስጠበቅ ብዙ ጥቁር ሰዎችን ገደሉ፤ሰዎችን መግደላቸውን ደግሞ ይቀጥላሉ። »
የሞሮኮ የሰብዓዊ መብቶች ማኅበር እንደሚለው እስካሁን የሞቱት ስደተኞች ማንነት አልተለየም፤ የሟቾቹን አስከሬንም ሆነ ቆስለው ሆስፒታል በመታከም ላይ ያሉትን በርካታ ስደተኞች ማየት አልተፈቀደም። ሆኖም ከመካከላቸው ከሱዳን የመጡ ወጣት ወንዶች ይገኙበታል ተብሎ ይታመናል። 
የሞሮኮ ባለሥልጣናት ስደተኞቹ የሞቱት ተረጋግጠው ነው ሲሉ ባለፈው አርብ ባርሴሎና ሰልፍ የወጡት ተቃዋሚዎች ግን የሞታቸው ምክንያት የሁለቱም ወገን ፖሊስ ከመጠን ያለፈ ኃይል መጠቀሙ ነው ብለዋል።ካሪቡ የተባለው ሌላ ማኅበር ዋና ፀሀፊ ኒኮል ንዶንጋላ ለስደተኞቹ ሞት ሞሮኮንና ስጳኝ ተጠያቂ አድርገዋል። 
«የተሻለ ሕይወት ለማግኘት የሚሞክሩ አፍሪቃውያን ርህራሄ  በሌለው ሁኔታ መገደላቸውን አይተናል። የሚሆነው ለሰው ልጆች ሕይወት ደንታ እንደማይሰጥ ነው፤ በተለይ ለጥቁር ዝርያዎች።ተጠያቂዎቹ የሞሮኮና የስጳኝ ፖሊሶች ናቸው። ምክንያቱም በዓለማችን የተንሰራፋውን መንታ አቋም በግልጽ ማየት እንችላለን።ስጳኝ ስደተኞች እንዳይመጡባት የማስቆም ፍላጎት አላት።ሞሮኮ ደግሞ በሳሃራ ፍላጎት አላት። እናም ሁለቱ የሚጫወቱት በሰዎች ሕይወት ነው። ካፒታሊዝም ቅድሚያ ሲሰጠው የሰው ልጆች ሕይወት ምን ያህል ለአደጋ እንደሚጋለጥ እንደገና እያየን ነው።እነዚህ በግልጽ የገንዘብና የስልጣን ሰይጣናዊ ጥመኝነት ናቸው።»
ማድሪድ ባለፈው ሳምንት የስጳኝና የሞሮኮ አጣሪዎች ለሚያከናውኑት ምርመራ ሙሉ ትብብር አደርጋለሁ ብላለች። ስጳኝ ይህን ያለችው የተመድ የሞሮኮና የስጳኝ ድንበር ጠባቂዎች ከመጠን ያለፈ ኃይል ተጠቅመዋል ሲል ድርጊታቸውን ካወገዘ በኋላ ነው።የተመድ ዋና ፀሀፊ የአንቶንንዮ ጉተሬሽ ቃል አቀባይ ሽቴፋን ጁዳሪክ ፣የሁለቱም ሀገራት ባለሥልጣናት ከመጠን ያለፈ ኃይል ሲጠቀሙ አይተናል፤ እነዚህ ተቀባይነት የሌላቸው መጣራት የሚገባቸው ናቸው ብለዋል። የስፓኝ ጠቅላይ ሚኒስትር ሳንቼዝ ከአንድ የሀገራቸው ራድዮ ጋር ባካሄዱት ቃለ ምልልስ የሰዎች ሕይወት መጥፋቱ እንዳሳዘናቸው ገልጸው በአደጋው ከሞቱት ሰዎች ቤተሰቦች ጋር እንደሚተባበሩ አስታውቀዋል።ሳንቼዝ አስቀድመው ጥፋቱን በሌላ ካላከኩ ከቀናት በኋላ ለሟቾች ሀዘኔታቸውን መግለጻቸው ትዝብት ላይ ጥሏቸዋል። የሞሮኮ ባለሥልጣናት በበኩላቸው ከስደተኞቹ አብዛኛዎቹ አጥር ላይ ሲንጠላጠሉ ወድቀው መሞታቸውን ነው የተናገሩት።መጀመሪያ ላይም የሟቾቹ ቁጥር 18 እንደነበር በኋላም ከቆሰሉት መካከል  5 ተጨማሪ ስደተኞች ሲሞቱ ቁጥሩ ወደ 25 ከፍ እንዳለ አስረድተዋል።የሞሮኮ አቃቤ ሕግ ደግሞ አብዛኛዎቹ ሱዳናውያን የሆኑ 65 ስደተኞችን ድንበር ለመጣስ በመሞከር ሊከሱ ነው።
ኂሩት መለሰ

ምስል Manu Fernandez/AP Photo/picture alliance

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW