ቁጥሮች ስለ ሰባተኛው የኢትዮጵያ ምርጫ ምን ያሳያሉ?
ዓርብ፣ ግንቦት 21 2018
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በመጪው ሰኞ ድምጽ በሚሰጥበት ሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ የ42 የፖለቲካ ፓርቲዎች አባላት እና የግል ተወዳዳሪዎችን ጨምሮ በአጠቃላይ 10,438 ዕጩዎች እንደሚወዳደሩ አስታውቋል። ከእነዚህ መካከል 80 ዕጩዎች የግል ተወዳዳሪ ናቸው።
የቦርዱ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ዛሬ አርብ በአዲስ አበባ በሰጡት ጋዜጣዊ መግለጫ 54,057,861 ድምጽ ሰጪዎች መመዝገባቸውን አስታውቀዋል። ከእነዚህ ውስጥ 20,100 ገደማ የዩቨርሲቲ ተማሪዎች፣ 28,632 ተፈናቃዮች እና 126,498 በወታደራዊ የጦር ሠፈር ውስጥ የሚገኙ ናቸው።
በአማራ ክልል 5 ምርጫ ክልሎች እና በጋምቤላ ክልል 4 የምርጫ ክልሎች በስተቀር በሁሉም ምርጫ ክልሎች የምርጫ ማስፈጸሚያ ቁሳቁሶች መዳረሳቸውን ሜላተወርቅ ገልጸዋል። “በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ከ547ቱ መቀመጫዎች በ501 ምርጫ ይካሔዳል” ሲሉ የቦርዱ ሰብሳቢ ተናግረዋል።
ብልፅግና ፓርቲ የትግራይ ክልልን ሳይጨምር በ48 የምርጫ ክልሎች አይወዳደርም
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በኦሮሚያ ክልል ጅማ ዞን ውስጥ በሚገኘው ጎማ 2 የምርጫ ክልል ከሁለት የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ ዕጩዎች ጋር ይወዳደራሉ።
ከአዲስ አበባ በ390 ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ በሚገኘው ምርጫ ክልል ነፃነትና እኩልነት ፓርቲን የሚወክሉት ዳግም ዋሪሶ እና የኢዜማ ዕጩ ካልድ ጃማል ሀይደር ከ49 ዓመቱ የብልፅግና ፓርቲ ፕሬዝደንት ሲወዳደሩ የአሁኑ የመጀመሪያቸው አይደለም።
በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ ሁለቱም በጠቅላይ ሚኒስትሩ ተሸንፈዋል። ዐቢይም ይሁኑ ፓርቲያቸው ብልፅግና በሰባተኛው ምርጫ ይኸ ነው የሚባል ፉክክር ይገጥማቸዋል ተብሎ አይጠበቅም።
ብልፅግና ፓርቲ ሰኞ ግንቦት 24 ቀን 2018 ለሚካሔደው ምርጫ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 461 ዕጩዎች አቅርቧል። ፓርቲው በድሬዳዋ፣ ጋምቤላ እና ሐረሪ ክልሎች በሚገኙ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች በሙሉ የሚወዳደሩ ዕጩዎች አስመዝግቧል።
ይሁንና ከ547 የምክር ቤቱ መቀመጫዎች መካከል የትግራይ ክልልን ሳይጨምር በ48ቱ አይወዳደርም። ዐቢይ አሕመድ በፕሬዝደንትነት የሚመሩት ብልፅግና ፓርቲ በ65 የምርጫ ክልሎች የሚወዳደረው ያለ አንዳች ተፎካካሪ ነው።
ገዢው ፓርቲ በርካታ ዕጩ ሳያቀርብባቸው ከቀሩ ክልሎች ቀዳሚው በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 178 መቀመጫዎች ያሉት የአማራ ክልል ነው። በክልሉ ገዢው ፓርቲ በ17 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች ዕጩዎች እንዳላቀረበ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ብርጫ ቦርድ ሰነድ ያሳያል። በክልሉ ስምንት የምርጫ ክልሎች ሰኞ ድምጽ እንደማይሰጥ ቦርዱ ቀደም ብሎ አሳውቆ ነበር።
የኦሮሚያ ክልል በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ካሉት 178 መቀመጫዎች ውስጥ ዕጩ ያስመዘገበው በ172 ነው። የተቀሩት ስድስት መቀመጫዎች የብልፅግና ዕጩዎች አልቀረቡባቸውም።
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በ5 የምርጫ ክልሎች ብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች አላስመዘገበም። በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፣ በሲዳማ ክልል እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልል በእያንዳንዳቸው ሦስት እንዲሁም በቤኒሻንጉል ጉምዝ እና በአፋር ክልሎች አንድ አንድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የገዢው ፓርቲዎች ዕጩዎች እንደማይወዳደሩባቸው የምርጫ ቦርድ ሠነድ ያሳያል።
መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ዕጩዎች ያስመዘገቡት የትኞቹ ፓርቲዎች ናቸው?
ከብልፅግና ፓርቲ በመቀጠል ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ምርጫ ያቀረበው የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ (ኢዜማ) ነው። በቅርቡ መሪው የነበሩት የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሀኑ ነጋን አሰናብቶ በአቶ ኢዮብ መሳፍንት የተካው ኢዜማ በ291 የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫዎች የሚወዳደሩ ዕጩዎች አስመዝግቧል።
የመላው ኢትዮጵያ አንድነት ድርጅት፣ እናት ፖርቲ፣ የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ፓርቲ እና አማራ ግዮናዊ ንቅናቄ የተባሉ ፓርቲዎችን ያቀፈው ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት በ224 መቀመጫዎች ለመወዳደር ዕጩዎችን አቅርቧል። በአጠቃላይ 2,080 ዕጩዎች ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይወዳደራሉ።
መንግሥት ለመመሥረት የሚያስችል ዕጩዎች ያስመዘገቡት ገዢው ብልፅግና ፓርቲ እና የኢትዮጵያ ዜጎች ለማኅበራዊ ፍትህ ናቸው። የኢትዮጵያ ሕገ-መንግሥት አንቀጽ 56 “በምክር ቤቱ አብላጫ መቀመጫ ያገኘ የፖለቲካ ድርጅት ወይም ጣምራ ድርጅቶች” መንግሥት መመሥረት እንደሚችሉ ይደነግጋል።
በሕገ-መንግሥቱ መሠረት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለሚደረግ ምርጫ በአንድ የምርጫ ክልል ውስጥ ከሚወዳደሩት ዕጩዎች መካከል አብላጫ ድምጽ ያገኘው አሸናፊ ይሆናል። ይህ የምርጫ ሥርዓት እንዲቀየር የቀድሞው የኢትዮጵያ ሕዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢሕአዴግ) እና 15 የሚሆኑ ተቃዋሚዎች በጥቅምት 2010 ከሥምምነት ደርሰው ነበር።
ኢሕአዴግ እና ተቃዋሚዎች በወቅቱ የምርጫ ሥርዓቱ ወደ ቅይጥ ትይዩ እንዲቀየር እና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት ቁጥር ከ547 ወደ 660 ከፍ እንዲል ቢስማሙም ገቢራዊ አልሆነም።
ኢትዮጵያ ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት መከተል አለባት የሚል አቋም ያላቸው ዶክተር ብዙነህ ጌታቸው “ጠቅላይ ሚኒስትሩ ወደ ሥልጣን ሲመጡ ይኸን እንደሚቀበሉ አውርተው ነበር” ሲሉ ያስታውሳሉ። በሰሜን አየርላንድ ዋና ከተማ ቤልፋስት በሚገኘው ኩዊንስ ዩኒቨርሲቲ የፖለቲካ መምህር የሆኑት ዶክተር ብዙነህ “ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት የራሱ ተግዳሮቶች አሉት። ለመተግበር ሊያስቸግር ይችላል” ሲሉ ለዶቸ ቬለ ተናግረዋል።
ይሁንና ተመጣጣኝ የምርጫ ሥርዓት “ትናንሽ ፓርቲዎች” ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲገቡ ዕድል በመፍጠር “ለዴሞክራሲ ማበብ የራሱ አስተዋጽዖ ይኖረዋል።” ከምርጫ ሥርዓቱ ባሻገር ጦርነት እና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች የሚካሔዱ ግጭቶ በሰባተኛው ጠቅላላ ምርጫ ላይ አጥልተዋል።
በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት 38 መቀመጫዎች ባሉት የትግራይ ክልል ምርጫው አይካሔድም። ኢትዮጵያ ምርጫ የምታደርገው ህወሓት እና ፌድራል መንግሥቱ ኃይለኛ ውጥረት ውስጥ እያሉ ነው።
በትግራይ ክልል 38 የምርጫ ክልሎች እና በአማራ ክልል ስምንት የምርጫ ክልሎች “ወደፊት አስቻይ ሁኔታ ሲኖር” ምርጫ እንደሚካሔድ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሰብሳቢ ሜላተወርቅ ኃይሉ ተናግረዋል።
ከትግራይ ባሻገር በአማራ እና በኦሮሚያ ክልሎች እየተካሔደ የሚገኘው ግጭት የምርጫው ተዓማኒነት ጥያቄ ውስጥ እንዲወድቅ አድርጎታል። ከሚያዝያ 2015 ጀምሮ ከክልሉ የጸጥታ አስከባሪዎች እና ከመከላከያ ሠራዊት ጋር በመዋጋት ላይ ከሚገኙ ኃይሎች መካከል አንዱ የሆነው የአማራ ፋኖ ብሔራዊ ንቅናቄ የድምጽ የሚሰጥበትን ዕለት ጨምሮ በአማራ ክልል "ለተከታታይ አምስት ቀናት ከአንቡላንሶች በስተቀር ሁሉም መንገዶች ለተሽከርካሪዎች ዝግ መደረጋቸውን” አስታውቋል።
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄን ወክለው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል የነበሩት አቶ ክርስቲያን ታደለን ጨምሮ በርካታ ፖለቲከኞች አሁንም በእስር ላይ ይገኛሉ።
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር (ኦነግ) በ50 ዓመታት ታሪኩ ለመጀመሪያ ጊዜ በኢትዮጵያ ምርጫ ሲሳተፍ ሊቀ-መንበሩ አቶ ዳውድ ኢብሳ በዕጩነት አልቀረቡም። ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና የሚመሩት የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ጥቂት ዕጩዎች ያስመዘገበው በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ላለመሰረዝ ብቻ እንደሆነ አስታውቋል።
ተቃዋሚዎች በምርጫው ሒደት በተዘጋጁ ክርክሮች ሲሳተፉ እና በከተሞች የምረጡኝ ዘመቻ ሲያካሒዱ ቢታዩም መከፋፈላቸው እና መዳከማቸው ገዢውን ፓርቲ መገዳደር የሚያስችል አቅም የላቸውም።
“ተቃዋሚ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጠንካራ አደረጃጀት የላቸውም። በየክልሉ መራጮችን መቀስቀስ አይችሉም” የሚሉት ዶክተር ብዙነህ “የአቅም እና የልምድ ማነስ” እንዳለባቸው ታዝበዋል።
“ከሕዝቡ ጋር ያላቸው ትሥሥር ደካማ ስለሆነ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓቱን ከሚያዳክሙት ውስጥ አንዱ የተቃዋሚዎች አደረጃጀት ነው። ጠንካራ ተቃዋሚ ከሌለ የመድብለ ፓርቲ ሥርዓት ሊኖር አይችልም” ሲሉ ተናግረዋል። ተቃዋሚዎች በፊናቸው መሪዎቻቸውን በማሠር እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴያቸውን በሕጋዊ ክልከላ በማዳከም መንግሥትን ይከሳሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ግን በሕዝብ ተወካዮች ምክር የተቃዋሚዎች ቁጥር “በአምስት እና አስር እጥፍ” እንደሚጨምር ከጥቂት ወራት በፊት ለፓርላማ በሰጡት ማብራሪያ ተንብየዋል።
ተቃዋሚዎች በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት መቀመጫ እንዲኖራቸው ዐቢይ መንግሥታቸው “አውድ ማስፋት ብቻ ሳይሆን ይሁነኝ ብሎ ይሠራዋል” ጠቅላይ ሚኒስትሩ የሥራ ዘመኑን እያገባደደ ለሚገኘው ምክር ቤት ተናግረው ነበር።
“ባለፉት አምስት ዓመታት ከፍተኛ ሚና የነበራቸው የምክር ቤት አካባላት inclusive ምርጫ እንዲኖረን ስለፈለግን እንደ አብርሀም በግ ጥለናቸው ያለፍናቸው አሉ” ብለዋል።
ይህ አካሔድ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትን ብቻ ሳይሆን “በእያንዳንዱ ክልል ምክር ቤትም ብዙ ድምጾች እንዲሰሙ መንግሥት ይሁነኝ ብሎ” የሚከተለው እንደሆነ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አስቀድመው ገልጸዋል።
ከትግራይ ክልል ውጪ ለክልል ምክር ቤቶች እና ለከተማ አስተዳደር ምክር ቤቶች በሚካሔደው ምርጫም ገዢው ብልፅግና ፓርቲ የማይወዳደርባቸው የምርጫ ክልሎች ይገኛሉ። ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት 158 መቀመጫዎች ብልፅግና ፓርቲ 134 ዕጩዎች አስመዝግቧል። ገዢው ፓርቲ ለ24 የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት መቀመጫዎች ዕጩ እንዳላስመዘገበ የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሠነድ ያሳያል።
ከብልፅግና ፓርቲ በላይ ትብብር ለኢትዮጵያ አንድነት 143 እንዲሁም ህዳሴ ፓርቲ 142 ዕጩዎችን ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት እንዲመረጡ አስመዝግበዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ምክር ቤት መቀመጫዎች ቁጥር በስድስተኛው ጠቅላላ ምርጫ 138 የነበረ ቢሆንም በ20 ጨምሮ 158 ደርሷል። ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት በተጨማሪ የስድስት የክልል ምክር ቤቶች የመቀመጫ ቁጥር እንዲጨምር ተደርጓል።
የኦሮሚያ ክልል ምክር ቤት ካሉት 537 መቀመጫዎች ውስጥ በ532ቱ የብልፅግና ዕጩዎች ይወዳደራሉ። የአማራ ክልል ምክር ቤት ካሉት 294 መቀመጫዎች ብልፅግና ፓርቲ ዕጩዎች ያቀረበው ለ271 ሲሆን ለ28 መቀመጫዎች ዕጩ ሳያስመዘግብ ቀርቷል።
የአፍሪካ ኅብረት እና የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት (ኢጋድ) ምርጫውን እንደሚታዘቡ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ገልጿል። ይሁንና የአውሮፓ ኅብረትን ጨምሮ ዓለም አቀፍ ተቋማት ታዛቢዎቻቸውን ወደ ኢትዮጵያ አላሰማሩም።
አርታዒ አዜብ ታደሰ