1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ፖለቲካሰሜን አሜሪካ

ቃለ ምልልስ ከአዲሱ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም ጋር

ሐሙስ፣ መጋቢት 11 2017

ከዚህ ቀደም ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪቃ አገሮች የተዘረጋውና ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የታገደችበት በዩናይትድ ስቴትስ ከቀረጥ ነፃ የንግድ እድል ወይም አጎዋን በተመለከተ ፕሮግራሙ እንዲቀጥል ለአሜሪካ መንግስት ጥያቄ መቅረቡን የገለጹት አምባሳደሩ፣አስተዳደሩ የሚደርስበት ውሳኔ ወደፊት የሚጠበቅ እንደሆነ አመልክተዋል።

USA Äthiopien Botschafter Binalif Andualem
ምስል፦ Tariku Hailu/DW

ቃለ ምልልስ ከአዲሱ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም ጋር

This browser does not support the audio element.

በአሜሪካ የኢትዮጵያ ልዩ መልዕክተኛና ባለሙሉ ስልጣን አምባሳደር ብናልፍ አንዷለም፣ ለአዲሱ ሀላፊነታቸው ወደ ዋሽንግተን ዲሲ ከመጡበት ጊዜ አንስቶ፣እስካሁን በአሜሪካ በተለያየ ደረጃ ከሚገኙ ባለስልጣናት እንዲሁም ሌሎች አፍሪቃውያን ዲፕሎማቶች ጋር አብሮ ለመስራት የሚያስችል ትውውቅ በማድረግ ዐሳብ ሲለዋወጡ መቆየታቸውን ገልጸውልናል።

የአምባሳደሩ ዋነኛ ተልዕኮዎች

በአዲሱ ተልዕኳቸው ትኩረት የሚያደርጉባቸውን ዋና ዋና ጉዳዮችን በተመለከተ ጠይቀናቸው ሲመልሱም፣

"በጣም ስትራቴጂክ ትብብርን ለመመስረት የሚያስችል ዐይነት ግንኙነት እንዲሆን፣ እሱ ላይ ትኩረት ያደረገ ስራ እንድንሰራ ነው በመንግስት በኩል ያለው አጠቃላይ ዐሳብ፣እኔም ያንኑ ዐሳብ ለማስፈጸም ትኩረት አድርጌ ለመስራት ነው እንደ ዕቅድ የያዝኹት። ስለዚህ ይኼ ደግሞ በኢኮኖሚው፣ በፖለቲካው፣ በማኀበራዊ ጉዳዮች የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶች የመሳሰሉ ጉዳዮች ጠንካራ ሆነው እንዲሄዱ ማድረግ ትኩረት ተሰጥቶት መሰራት ያለበት ነገር ነው።

በአሜሪካ የሚኖረው የኢትዮጵያ ዲያስፖራ ማኀበረሰብ፣ በአገሩ ብሄራዊ ጥቅም ላይ አንድ ሆኖ እንዲሰራ እንዲሁም በኢትዮጵያ ፖለቲካዊ፣ ማኀበራዊና ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴዎች ላይ ተሳታፊ እና ተጠቃሚ እንዲሆን ማድረግ ሌላው የተቀመጠ ግብ እንደሆነ አምባሳደር ብናልፍ ጠቁመዋል።የዉጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ስለ ኢትዮጵያ እና አሜሪካ ግንኙነት

"በአጠቃላይ ዲያስፖራው፣መብቱ፣ ጥቅሙና ክብሩ ተጠብቆ የሚኖርበትና ከአገሩ ጋር ያለው ግንኙነት ደግሞ የበለጠ እንዲጠነክር እንዲሳተፍ፣እሱ ተሳታፊ ሆኖ በሃገሩም ጉዳይ ላይ በኢንቨስትመንትም ይሁን በተለያየ ዕውቀቱም የተለያዩ ድጋፍና ዕገዛ እያደረገ እሱም በሃገሩ ልማት ተጠቃሚ የሚሆንበት ነገር የመፍጠር፣ያን ትስስር የማጠናከር ሥራዎች ናቸው።"

የትራምፕ አስተዳደር የፈጠረው መልካም ዕድል

የዶናልድ ትራምፕ አስተዳደር ከአፍሪቃ አገሮች ጋር የሚኖረው ግንኙነት፣ እንደዚህ ቀደሙ በዕርዳታ ላይ ሳይሆን፣ በንግድና ኢንቨስትመንት ላይ የተመሰረተ እንደሚሆን  ማስታወቁ፣ ለኢትዮጵያ መልካም ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አምባሳደር ብናልፍ ይናገራሉ።የኢትዮጵያና የአሜሪካ ግንኙነት እና ሳንካዎቹ

"በጣም ብዙ መልካም ዕድሎች አሉት። ለምሳሌ ኢትዮጵያ በጣም ትልቅ አገር ነው።ከ120 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያለው ሃገር እንደመሆኑ ለአሜሪካ ትልቅ ገበያ ነው። ለስራ ፈጠራም ለተለያዩ የሸቀጥና የተለያዩ የቴክኖሎጂ ልውውጥ ለኢትዮጵያ መልካም ዕድልን ይፈጥራል፤ ለአሜሪካ መልካም እድል ይፈጥራል። እስካሁን በነበረኝ ቆይታ፣ከተለያዩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ኃላፊዎች እና ከአፍሪቃ ጉዳዮች ተጠሪዎች ጋር  ውይይት አድርገናል፤ስለዚህ በጎ እና ቀና  ፍላጎት እንዳላቸው ነው የተረዳኹት።"

የአጎዋና የዩኤስኤይድ ጉዳይ

ከዚህ ቀደም ከሰሃራ በታች ላሉ የአፍሪቃ አገሮች የተዘረጋውና ከሰሜኑ ጦርነት ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያ የታገደችበት በዩናይትድ ስቴትስ ከቀረጥ ነፃ የንግድ እድል ወይም አጎዋን በተመለከተ ፕሮግራሙ እንዲቀጥል ለአሜሪካ መንግስት ጥያቄ መቅረቡን የገለጹት አምባሳደሩ፣አስተዳደሩ የሚደርስበት ውሳኔ ወደፊት የሚጠበቅ እንደሆነ አመልክተዋል። ኢትዮጵያ ከአሜሪካ ተራድኦ ድርጅት ታገኝ የነበረው ዕርዳታ በመቋረጡ፣ ዕርዳታ በሚፈልጉ ወገኖቻችን ላይ ጉዳት እንደሚያስከትል ይታወቃል እና ከዚህ አኳያ ዕርዳታው መልሶ የሚቀጥልበት እድል እንዳለ የሚታወቅ ነገር አለ?ከዚህ አኳያ የደረጋችሁት ውይይት ካለ? ተብለው ለተጠየቁትም

 "ግልጽ የተደረገው አቅጣጫ፣ በእዛው በስቴት ዲፓርትመንት በኩል ነው እንጂ ዩኤስአይዲ እንደተቋም በዚህ መንገድ የሚቀጥልበት ነገር የሚለውን፣ አቋም ወስደዋል።ግን አጣዳፊ የሆኑ ጉዳዮችን እንዴት እናስቀጥላቸዋለን፣አሁን ቶሎ መቀጠል ያለባቸው ፕሮጀክቶች እንዴት ነው የሚቀጥሉት የሚሉ ጉዳዮች ላይ ተነጋገረን አቅጣጫ አስቀምጠን ወደእዚያ ሥራ እንገባለን የሚል ሀሳብ ነው ያነሱት።"የኢትዮጵያ እና የአሜሪካ ግንኙነት

ሕጋዊ ሰነድ የላቸውም የተባሉ ስደተኞች ወደ ሃገራቸው መሸኘታቸው

የትራምፕ አስተዳደር በጀመረውና፣ሕጋዊ ሰነድ የላቸውም ያላቸውን ስደተኞች ወደመጡበት ሃገር የመመለስ ዘመቻ፣እስካሁን የስምንት ኢትዮጵያውያን ጉዳዮች፣ ለኤምባሲው መቅረቡን የተናገሩት  አምባሳደር ብናልፍ፣ ጉዳያቸውም ከአሜሪካ መንግስት ጋር  በመጣራት ላይ መሆኑን አስረድተዋል።

"ከእኛ አኳያ ስምንት የሚሆኑ ጉዳዮች እስካሁን ድረስ በነበረው እንቅስቃሴ፣ወደ እኛ ተልከው ያሳወቁን አሉ።የእነሱን የማጣራት ሥራ እየሰራን ነው ያለነው አብረን ከአሜሪካ መንግስት ጋር።የግለሰቦቹን አጠቃላይ ሁኔታ የማጥናት ስራ እየሰራን ነው።አንድ ሁለት የተመለሱ ይመስለኛል ወደ ኢትዮጵያ።ሌሎቹ ግን ገና በመጣራት ላይ ያሉ ናቸው።"ብለዋል።

ታሪኩ ኃይሉ

ኂሩት መለሰ

አዜብ ታደሰ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW