እስረኞች መፍታት ብቻ መፍትሔ አይሆንም- ኮሎኔል ደመቀ
ማክሰኞ፣ የካቲት 13 2010በሽብር ተከስሰው በጎንደር ታስረው የቆዩት ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ትላንት ሰኞ የካቲት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. ሲፈቱ በከተማይቱ ነዋሪዎች ከፍተኛ አቀባበል ተደርጎላቸዋል። በርካታ የጎንደር ነዋሪዎች ኮሎኔል ደመቀ አንገረብ ወንዝ አጠገብ ከሚገኘው ማረሚያ ቤት ከተለቀቁ ጀምሮ በጭፈራ አጅበዋቸው ደስታቸውን ሲገልጹ ታይተዋል። በዛሬው ዕለትም ነዋሪዎች በሰልፍ ሆነው ወደ መኖሪያ ቤታቸው በመዝለቅ ሲጠይቋቸው ውለዋል።
ኮሎኔል ደመቀ ዛሬ ለዶይቼ ቬለ በሰጡት ቃለ ምልልስ የወልቃይት የማንነት ጥያቄ እንዳልተፈታ ገልጸው ጥያቄያቸውን በህጋዊ እና ሰላማዊ ሁኔታ ማቅረባቸውን እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል። «መፍትሄው ከመንግስት እጅ ነው ያለው» ብለዋል። የወልቃይት ማንነት ጥያቄውን በሚያስተባብረው ኮሚቴ ቀደም ሲል ወደ ነበራቸው ድርሻ እንደሚመለሱም አስታውቀዋል። የኢትዮጵያ «መንግስት እስረኞችን መፍታቱ ጥሩ ነው» ያሉት ኮሎኔል ደመቀ «የቀሩትንም ሲፈታ አንድ የህዝብ ጥያቄ ተመለሰ ማለት ይቻላል» ሲሉ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። «እስረኞችን መፍታት ብቻ» ግን አሁን ላለው የፖለቲካ ቀውስ «የመጨረሻ መፍትሔ ይሆናል ብዬ አልገምትም» ሲሉ አክለዋል።
የፌደራል ጠቅላይ አቃቤ ህግ ኮሎኔል ደመቀን ጨምሮ የ101 እስረኞች ክስ መቋረጡን ባለፈው ቅዳሜ የካቲት 10 ቀን 2010 ዓ.ም አስታውቆ ነበር፡፡ ከኮሎኔል ደመቀ ጋር አብረው የተከሰሱ 10 ተጠርጣሪዎች ክስ ትላንት በፌደራል ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቋረጡን የቅርብ ሰዎቻቸው ገልጸዋል። አስሩ ተጠርጣሪዎች ትላንት ከእስር መፈታታቸውን የአማራ መገናኛ ብዙሃን ድርጅት ቢዘግብም እስከ ዛሬ ከሰዓት ከእስር ቤት አለመውጣታቸውን ለዶይቼ ቬለ አስረድተዋል። በአዲስ አበባ ታስረው የሚገኙት የወልቃይት የማንነት ጥያቄ ኮሚቴ አባላት ወደ ጎንደር ሲመለሱ በተመሳሳይ ደማቅ አቀባበል እንደሚደረግላቸው የጎንደር ነዋሪዎች ተናግረዋል።
ኮሎኔል ደመቀ ዘውዱ ለዶይቼ ቬለ የሰጡትን ሙሉ ቃለ ምልልስ የድምጽ ማዕቀፉን ተጭነው ያድምጡት።
ተስፋለም ወልደየስ
ሂሩት መለሰ