ቃር፤ ሆድ መንፋትና ማቅለሽለሽ
ማክሰኞ፣ ጥር 13 2017
የውስጥ ደዌ፣ የጨጓራና አንጀት ህክምና ባለሙያን እንግዳችን ለማድረግ ምክንያት የሆኑን የዘወትር አድማጭ እና የዝግጅታችንም ተሳታፊ የሆኑት የመቶ አለቃ ውቤ ናቸው። አድማጫችን፤ አንድ ያሳሰበኝ የጤናዬ ጉዳይ አለ በማለት ጥያቄ ላኩልን። ጥያቄያቸው እንዲህ ይላል፤ «ሆዴን ይነፋኛል። ከአንጀቴ እሰከ ጉሮሮየ ድረስ ቃር ይገሸልጠኛል። ያቅለሸልሸኛል። ሽንት ቤት ስቀመጥ በአግባቡ ለመጠዳዳት ያስቸግረኛል። ሐኪሞችም ሁነኛ መድሃኒት አላገኙልኝም እንዳው ምን ይሻለኝ ይሆን?» አሉና እንደውም የሆድ መነፋትና የሚወጣ አየር መደጋገም እንዳሳሰባቸው ዘርዝረዋል።
ከምግብ መፈጨት ሂደት ጋር በተያያዘ አቃጠለኝ አቃረኝ የሚለው ከብዙዎች የሚሰማ የጤና ችግር ነው። የተከበሩ አድማጫችንን ጥያቄ በመያዝ የዘርፉን የህክምና ባለሙያ አፈላልገን ዶክተር ፈቃዱ ግርማን አግኘንና በቅድሚያ ለመሆኑ ቃር፤ ማቃጠል ከምን ጋ ይገናኛል? ምንድነው እንዴትስ ይከሰታል በማለት ጥያቄያችንን አቀረብን።
ቃር ምንድነው?
ቃር በሁሉም ማኅበረሰብ የሚያጋጥምና የተለመደ እንደሆነ የገለፁት ዶክተር ፈቃዱ፤ ችግሩን ብዙውን ጊዜ በጨጓራ ውስጥ ከሚመረተው አሲድ ጋር የተገናኘ መሆኑን ያመለክታሉ። «አንድ ሰው ምግብ ከበላ በኋላ ከአፍ ቀጥሎ ባለው የምግብ መውረጃ ቱቦ ከወረደ በኋላ ከጨጓራ እንዳይመለስ ይዘጋል። አንዳንዴ ያ ለቀቅ በሚልበት ጊዜ እዚያ ያለው ኃይለኛ አሲድ ወደ ኋላ ይመለሳል።» የሚሉት የህክምና ባለሙያው ያኔ የማቃጠል ወይም የቃር ስሜት እንደሚፈጠር ያስረዳሉ። የጨጓራ መላጥ ወይም አልሰር የሚባለው እንዲሁም የጨጓራ ካንሰርም ይህን ችግር ሊያስከትል እንደሚችልም የዘርፉ የህክምና ባለሙያው ጠቁመዋል። ግን ደግሞ ይህ ብቻም አይደለም፤ ስኳር በሽታም ሆነ የልብ ህመም ሚና አላቸው ባይ ናቸው።
ጠያቂያችን ያነሱት የጤና ችግር በሁለት ተከፍሎ መታየት እንደሚገባው፤ አንደኛው ከላይኛው የሆድ ክፍል ሌላኛው ደግሞ ከታችኛው የሆድ ክፍል ጋር እንደሚያያዝ ያስረዱት ዶክተር ፈቃዱ በተለይ በአግባቡ የመጸዳዳት ችግር በአብዛኛው ከአመጋገብ ጋር ሊገናኝ እንደሚችል፤ ከዚህ በተጨማሪ ደግሞ የአንጀት መኮማተር ወይም ብግነት የሚባለውም ሌላው መንስኤ ሊሆን እንደሚችል ይገልጻሉ።
ድርቀት
ከአይነምድር በአግባቡ አለመወገድ ጋር ተያይዞ ድርቀትን የሚያስከትሉ ነገሮች በአብዛኛው ከአመጋገብ ጋር እንደሚያያዙ ነው በአዳማ ሆስፒታል የህክምና ኮሌጅ የውስጥ ደዌ፣ የጨጓራና አንጀት እንዲሁም የጉበት ህክምና ባለሙያ የሆኑት ዶክተር ፈቃዱ ግርማ የገለጹት። በዚያ ላይ በቂ ውኃ አለመጠጣት፣ ውጥረት እና እንቅስቃሴ አለማድረግ ሁሉ ለዚህ ችግር መከሰት ዓይነተኛ አስተዋጽኦ አላቸው። አመጋገብን በተመለከተ በተለይ አሰር ወይም ፋይበር የበዛባቸውን ምግቦች ስለመመገብ አንስተዋል ዶክተር ፈቃዱ፤ የትኞቹን ማለታቸው ይሆን? በዚያ ላይ ብዙዎች ውኃ ሥራዬ ብለው ለጤናቸው በማሰብ የመጠጣት ልማድ የላቸውም እና የህክምና ባለሙያው እንዲህ ይመክራሉ።
ለጨጓራንም ሆነ የአንጀትን ጤና ለመጠበቅ
ቃርም ሆነ ድርቀት እንዳይመጣ አስቀድሞ የአንጀትንም ሆነ የጨጓራን ጤና ለመጠበቅ እነዚህን ችግሮች የሚያስከትሉ መንስኤዎች ምን እንደሆኑ በጥንቃቄ መከታተል ይገባል። የሰውነት ውፍረት ካለ እንቅስቃሴን ከማዘውተር ጋር ክብደት መቀነስ እንደሚጠቅም፤ አልክሆል መጠጥን ማስወገድ፤ ለስላሳ መጠጦችን እና ካፌይን ያለባቸውን መጠጦችም አለመጠጣት ችግሩን ለመቀነስ ብሎም እንዳይከሰት ለማድረግ እንደሚጠቅሙም መክረዋል። ለሰጡን ሙያዊ ማብራሪያ ዶክተር ፈቃዱ ግርማን እናመሰግናለን። ሙሉ ጥንቅሩን ለማድመጥ የድምፅ ማዕቀፉን ይጫኑ
ሸዋዬ ለገሠ
ማንተጋፍቶት ስለሺ