«ቅርስ ወደ አገሩ፤ ታሪክ ወደ ስሩ» የ15ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሃገራቸዉ
ሐሙስ፣ ኅዳር 17 2019
«ቅርስ ወደ አገሩ፤ ታሪክ ወደ ስሩ» የ15ኛው ክፍለ ዘመን የኢትዮጵያ ቅርሶች ወደ ሃገራቸዉ
«በአሁኑ ጊዜ በአገር ዉስጥ መሰል ቅርስ ማግኘት ከባድ ነዉ፤ አልያም እንዲህ አይነት ታሪካዊ ቅርስ በጣም በጣም በተወሰነ አካባቢ ነዉ የሚገኘዉ። ከሚመለሱት አምስት ቅርሶች መካከል ሦስት መስቀሎች እና ሁለት የብራና ድርሳናት «መጻሕፍት» ይገኙባቸዋል። ባለፈዉ ሳምንት በእንጊሊዝ ለንደን በሚገኘዉ በኢትዮጵያ ኤምባሲ ዉስጥ ርክክብ አድርገናል። ኤምባሴዉ በቅርቡ ቅርሶቹን ይዞ ወደ ኢትዮጵያ ይመጣል።» የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር፤ ረዳት ፕሮፊሰር አበባዉ አያሌዉ፤ በቅርቡ ኢትዮጵያ እጅ ስለገባዉ፤ አምስት ጥንታዊ እና ታሪካዊ ቅርስ ጉዳይ የተናገሩት ነበር።
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን እና የቶሌዶ የጥበብ ሙዚየም ስምምነት
በዩናይትድ ስቴትስ ኦሃዮ ግዛት በሚገኘዉ የቶሌዶ የጥበብ ሙዚየም ፤ የግል ቅርስ ሰብሳቢዉ አሜሪካዊ ባለሃብት ሮበርት ማካርቲ በስብስብ ከያዛቸዉ እና ለሙዚየሙ ካስረከቧቸዉ ከፍተኛ ቁጥር ካላቸዉ የኢትዮጵያ ቅርሶች መካከል አምስቱን በለንደን የኢትዮጵያ ኤንባሲ በኩል ለመመለስ፤ ኤምባሲዉ በፊርማ ሥነ-ስርዓት ተረክቧል። ጥንታዊ ቅርሶችን ወደ ኢትዮጵያ በመመለስ ረገድ የቶሌዶ የጥበብ ሙዚየም ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ጋር በመተባበር እየሠራ እንደሆነ ታዋቂዉ የኢትዮጵያ ታሪክ፤ የሥነ-ጥበብ ታሪክ ምሁር፤ መምህር ተመራማሪ እንዲሁም የኢትዮጵያ ቅርሶች ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፊሰር አበባዉ አያሌዉ ነግረዉናል። ባለፈዉ ሳምንት በለንደን የኢትዮጵያ ኤምባሲ በክብር እጅ ዉስጥ የገባዉ፤ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርስ፤ በለንደን በሚገኝ አንድ መጋዘን ውስጥ ለዓመት ተቀምጦ መቆየቱን፤ ቅርሶቹ ደግሞ በ15ኛው ክፍለ ዘመን የተሰሩ ሁለት የብራና የእጅ ጽሑፍ ድርሳናት እና ሦስት የብር መስቀሎች መሆናቸዉ ተመልክቷል። በለንደን የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ ወደ ኢትዮጵያ ይዞ ለመጓዝ ዝግጅቱን ማጠናቀቁ እና ምናልባትም በሚቀጥለው ወር በኢትዮጵያ አዲስ ሙዚየም ውስጥ ለሕዝብ የዕይታ ይቀርባል ተብሏል። በቅርስ ርክክብ ሥነ-ስርዓቱ ላይ የተገኙት፤ የኢትዮጵያ ቅርስ አስመላሽ ኮሚቴ አባል አሉላ ፓንክረስት ቅርሶቹ ታሪካዊ እና ዉብ የሆኑ ብለዋቸዋል።
« ለየት ያሉ ዉብ እና ከሃይማኖትም ጋር ትስስር ያላቸዉ፤ ንዋየ ቅዱሳት እና ዉብ የሆኑ መስቀሎች ናቸዉ። በይዘታቸዉ ለየት ያሉ ናቸዉ። እነዚህ ቅርሶች አንድ ሮበርት ማካርቲ የሚባል ባለሃብት ከመላዉ የዓለም ሃገራት ካሰባሰባቸዉ ቅርሶች መካከል ነበሩ። እነዚህ ቅርሶች በኢትዮጵያ እጅ የገቡት የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዩናይትድ ስቴትስ፤ ኦሃዮ ግዛት ከሚገኘዉ ከቶሌዶ ሙዚየም ጋር ከተካሄደ ከብዙ ድርድር በኋላ ነዉ። ከዝያም ቅርሱ በለንደን ወደሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤንባሲ ሊመጣ ችሏል።»
የኢትዮጵያን ጥንታዊ ቅርሶች የያዘዉ የቶሌዶ የጥበብ ሙዚየም
እነዚህን ቅርሶች ለማስመለስ ስራዉ የጀመረዉ ከሦስት ዓመት በፊት እንደሆን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፊሰር አበባዉ አያሌዉ ተናግረዋል።
«እንደጎርጎረሳዉያኑ አቆጣጠር 2023 አካባቢ ከቶሌዶ ኦሃዮ ግዛት የሚገኝ ሙዚየም አንድ መረጃ ደረሰን። አዳም ሌቭ የሚባሉት የሙዚየሙ ዋና ዳይሬክተር፤ እንደነገሩን አንድ ባለሃብት በግላቸዉ ያሰባሰቧቸዉን የኢትዮጵያን ቅርሶች መመለስ ይፈልጋሉ የሚል ነበር። ባለፈዉ ዓመት ጥር ወር ዉስጥ ፤ ቴሌዶ ተገኝቼ ቅርሶቹን ተመልክቻለሁ። ወደ 320 የሚሆኑ የኢትዮጵያ ጥንታዊና ታሪካዊ ቅርሶችን አይቻለሁ። ከዝያን ጊዜ ጀምረን በምን አይነት አግባብ ወደ ኢትዮጵያ ይመለሱ የሚለዉን ስናጠና እና ስንከራከር ብዙ ጊዜ ወሰድን። በመጨረሻም፤ አምስት ቅርሶችን በመጀመርያ ሊሰጡን እና በሚቀጥሉት ሁለት ዓመታት ቀስ በቀስ ሊሰጡን ስምምነት ላይ ደረስን። የቶሌዶ ሙዚየም ለኢትዮጵያ የመለሰዉን ታሪካዊ ቅርስ ካስፈለገ፤ በተዉሶ ወስዶ ለእይታ አቅርቦ መመለስ እንደሚችልም ቃል ገብተልነታል።»
በዉጭ ሃገራት በተለይም በአዉሮጳ የሚኖሮ ኢትዮጵያዉያን፤ በግለሰብ እጅ የሚገኙ የኢትዮጵያን ቅርሶች የሚሰበስቡ አሉ። አብዛኙቹ ግን ለኢትዮጵያ ማስረከብ የሚፈልጉት እዉቅናን አግኝተዉ ፤ ቅርሶቹ ኢትዮጵያ ሲገቡ የት እንደተቀመጡ እና ፤ እዉነትም ለተመልካች ለእይታ መብቃታቸዉን ማረጋገጥ እንደሚፈልጉ ይናገራሉ።
«ቅርስ ወደ አገሩ ታሪክ ወደ ስሩ»
በለንደን በሚገኘዉ ኢንባሴ በቅርስ ርክክብ ሥነ-ስርአቱ ላይ የነበሩት የቅርስ ጉዳዮች ባለሞያ እና ለዓመታት በብሪታንያና እና በሌሎች የአዉሮጳ ሃገራት የሚገኙ የኢትዮጵያ ጥንታዊ ቅርሶች እየገዙ የሚሰበስቡት አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ እንደሚሉት የኢትዮጵያን ቅርስ ማስመለስ የመንግሥት ኃላፊነት ብቻ ሳይሆን፤ የሁሉም ኢትዮጵያዊ ኃላፊነት ነዉ።
«ቅርስ ወደ አገሩ ታሪክ ወደ ስሩ እንደሚባለዉ፤ አምስት የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ከቶሌዶ ታሪካዊ የሥነጥበብ ሙዚየም ወደ እናት አገራቸዉ፤ የሚመለሱበት ታሪካዊ ጉዞ ሲጀምር በቦታዉ በመገኘቴ ደስታ ይሰማኛል። በዚህ ዝግጅት ላይ የተጋበዝነዉ ጋዜጠኞች እና የቅርስ ቁዳይ ምሑራን እንዲሁም እንደኔ አይነቱ የቅርስ ጉዳይ ተቆርቋሪ እና የቅርስ ሰብሳቢ ነዉ። አንዳንድ ነገሮች ዋጋቸዉ በገንዘብ አይለካም ከወርቅ ፤ ከብር የበለጠ ከዉዱ እንቁ ከማዕድን የበለጠ ዋጋ ያላቸዉ ነገሮች አሉ። እነሱም የአንድ ሕዝብ ታሪክ ማንነት እምነት ባህል እና የሥልጣኔ ጉዞ ምስክሮች የሆኑ ቅርሶች ናቸዉ። ቅርስ ከትናንት ዘመን የተረፈ እቃ ብቻ አይደለም ፤ ቅርስ የአባቶች የእጅ አሻራ፤ የአያቶች የእዉቀት ዉጤት ፤ የአንድ ሕዝብ የጋራ ትዉስታ እና ለትዉልድ የሚተላለፍ የማንነት መሰረት ነዉ። በቅርስ ዉስጥ የተቀመጠዉ ታሪክ የድንጋይ የብረት ፤ የብራና ወይም የቀለም ታሪክ ብቻ ሳይሆን የሰዉ ልጅ የኑሮ እምነት የጥበብ እና የፈጠራ ታሪክ ነዉ። በዚህ የታሪክ እና የማንነት እሴት ስመለከተዉ፤ በዩናይትድ ኪንግደም የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ኤምባሲ እና የቶሌዶ የሥነ ጥበብ ሙዚየም በትብብር ለመሥራት ባደረጉት ስምምነት እና አምስት ወሳኝ የኢትዮጵያ ቅርሶችን ወደ ሀገራቸዉ ለመመለስ በተደረገዉ፤ ታሪካዊ ዝግጅት ላይ መገኘቴ ለእኔ ልዩ ትርጉም ያለዉ አጋጣሚ ነዉ። »
የብሪታንያዉ በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም
ከኢትዮጵያ እጅግ ውድ ከሆኑ ቅርሶች መካከል ጥቂቶቹ፤ የወርቅ አክሊልን እና ግዙፍ የወርቅ መስቀሎችን ጨምሮ አቶ አለባቸዉ በሚኖሩባት በለንደን ከተማ በሚገኘው በቪክቶሪያ እና አልበርት ሙዚየም ውስጥ፣ በመስታወት መደርደርያ ለተመልካች ይታያሉ። ድርሳናትን ጨምሮ ሌሎች በርካታ የኢትዮጵያ ታሪካዊ ቅርሶች ግን ለሕዝብ እይታ በማይደርሱበት ሁኔታ በምድር ቤት መጋዘን ውስጥ ታሽገዉባቸዉ እንደሚገኙ አቶ አለባቸዉ ሁሌም በቁጭት ይናገራሉ። የኢትዮጵያ ቅርሶች ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር ረዳት ፕሮፊሰር አበባዉ አያሌዉ፤ “እነዚህ ታሪካዊ ቁሶች፤ በቁፋሮ የተገኙ ቅርሶች አይደሉም። ኢትዮጵያ ውስጥ ዛሬም የተቀደሱ እና ከፍተኛ ክብር የሚሰጣቸው ናቸው”ብለዋል። እነዚህን ቅርሶች መያዝ እና መደበቅ ሞራላዊ መሰረት የሌለዉ ጉዳይ መሆኑንም ተናግረዋል። በለንደን ነዋሪ እንደሆኑት እንደ አቶ አለባቸዉ ደሳለኝ ሁሉ፤ ከአገር የወጡ የኢትዮጵያ ቅርሶችን የማስመለስ ሥራ የኢትዮጵያዉያን ሁሉ መሆኑን የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባዉ አያሌዉ ተናግረዋል።
አዜብ ታደሰ
ነጋሽ መሐመድ