1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የጋምቤላ ወጣቶች ተዘውታሪ ጨዋታ

ዓርብ፣ ኅዳር 23 2009

ጀምበር ማዘቅዘቅ ስትጀምር የጋምቤላ ከተማ ወጣቶች አንድ ልማድ አላቸው፡፡ ከተማዋን አፍኗት የሚውለው ወበቅ ቀዝቀዝ ማለት ሲጀምር ጋምቤላን ሰንጥቆ ወደሚያልፈው የባሮ ወንዝ ዳርቻ ይተምማሉ፡፡ በወንዙ ዳርቻ ያለውን ነፋሻማዋን አየር እየተመገቡ ሻይ ቡና ለማለት ብዙዎች ቦታውን ያዘወትሩታል፡፡ ወደ ወንዙ ወርዶ ገላን መለቃለቅም ያለ ነው፡፡

Äthiopien Basketball
ምስል Naath Youth Foundation

ጋምቤላዎች እና ቅርጫት ኳስ

This browser does not support the audio element.

ብዙ ወጣቶቹ ግን በጂኒና መገኘትን ይመርጣሉ፡፡ ጂኒና ባሮ ዳርቻ ያለ የስፖርት ማዘውተሪያ ስፍራ ነው፡፡ በዋናነት የቅርጫት ኳስ መጫወቻ ሜዳን ይዟል፡፡ በዚያ አዳጊዎች እና ወጣቶች በቡድን ተከፋፍለው ኳሳቸውን ከመሬት ጋር እያጋጩ እና እየተቀባበሉ የጨዋታ ጥበባቸውን ያሳያሉ፡፡ ከርቀት ወደ ቅርጫት ቀለበት በመወርወር ነጥብ ያሰቆጥራሉ፡፡ መጫወት ያልቻሉቱ ዙሪያውን ከብበው ይመለከታሉ፣ ያደንቃሉ፣ ያበረታታሉ፡፡    

የጋምቤላ ተወላጅ የሆነው የ21 ዓመቱ ሰቢት ኬት ከልጅነቱ ጀምሮ ከዚህ ሜዳ አይጠፋም፡፡ ሁሌም ከትምህርት ቤት መልስ ከሰፈር ጓደኞቹ ጋር ተጠራርቶ ወደ ሜዳው ይሄዳል፡፡ በ12 ዓመቱ የሶስተኛ ክፍል ተማሪ እያለ የተለከፈበት የቅርጫት ኳስ ጨዋታ ፍቅር አድጎም አለቀቀውም፡፡ ይበልጥኑ ባሰበት እንጂ፡፡

“አምስተኛ ክፍል ሆኜ ስጫወት ቅርጫት ኳስ ጨዋታ በትክክለኛው መንገድ ወደ ህይወቴ መጣ፡፡ የቅርጫት ኳስ [የቪዲዮ] ክሊፕ ማየት ጀመርኩ፡፡ አብዛኛውን ጊዜ ራሴን ነው ያለማመድኩት ማለት ይቻላል፡፡ አባቴ ቅርጫት ኳስ እንድጫወት በጣም ይደግፈኝ ነበር፡፡ ኳስ ገዝቶልኝ ቪዲዮዎችን እያየሁ ቤት እለማመዳለሁ፡፡ እና እነዚህን እያየሁ ለመድኩኝ፡፡ ምን እንደምልህ አላውቅም ብቻ ቅርጫት ኳስ ህይወቴ ነው፡፡ ከህጻንነቴ ስለሆነ የጀመርኩት አንዳንዴ ሲከፋኝ ሁሉ የማደርገው ነው፡፡ ያለቅርጫት ኳስ መኖር የማልችል ነው የሚመስለኝ” ይላል ሰቢት ለጨዋታው ያለውን ፍቅር ለመግለጽ ቃላት ለመምረጥ እየተቸገረ፡፡    

እንደ ሰቢት ሁሉ ቅርጫት ኳስ ለብዙ የጋምቤላ ወጣቶች ከጨዋታም በላይ ነው፡፡ በበርካታ የጋምቤላ ወጣቶች ዘንድ የህይወት ዘይቤ መገለጫ ተደርጎ ይወሰዳል፡፡ ይህን አስተሳሰብ ጨዋታውን የሚያዘወትሩ በተለያዩ ሀገራት ያሉ የዕድሜ እኩዩቻቸውም የሚጋሩት ነው፡፡ ከ125 ዓመት በፊት በካናዳዊው ጄምስ ናይስሚዝ የተፈለሰፈውን ይህን ስፖርታዊ ውድድር የሚጫወቱ “አነሳሽ እና አነቃቂ” ሲሉ ያሞካሹታል፡፡

ምስል Naath Youth Foundation

የቡድን ስራን በሚጠይቀው ቅርጫት ኳስ የመሪነት ሚና መወጣትን፣ ባለጠንካራ መንፈስ መሆንን፣ ቁርጠኝነትን፣ ለሚወዱት ነገር ያለን ጥልቅ ፍላጎት እና የተሻለ ሆኖ ለመገኘት መጣርን አይነት ክህሎቶች እንደሚማሩበት ይመሰክራሉ፡፡ ለዚህም ይመስላል ሰቢት ለትምህርት ወደ አዲስ አበባ ሲመጣ እንኳ ከቅርጫት ኳስ ጋር ያልተቆራረጠው፡፡ ሳሚ ብሎ የሚጠራው አሰልጣኙ ድጋፍ ታክሎበት ከትምህርት ቤት እስከ ክፍለ ከተማ ከፍ ሲልም አዲስ አበባን ወክሎ እስከ መወዳደር የዘለቀው፡፡

ከ17 ዓመት በታች የኢትዮጵያ የቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድንን ለመቀላቀል ጫፍ ከደረሰ በኋላ በዕድሜ ዙሪያ በነበረ አለመግባባት እርሱ እና ሌሎቹ ጓደኞቹ ዕድሉን ሳያገኙ ቀርተዋል፡፡ ሰቢት እንደ ቅርጫት ኳስ ሁሉ ትምህርቱ ላይም ብርቱ ነበርና በስፖርቱ ያጣውን ድል በፈተና ውጤት አግኝቶታል፡፡ ወደ ከፍተኛ ትምህርት ተቋም ለመግባት የተሰጠውን ፈተና በአጥጋቢ ሁኔታ ተወጥቶ በደብረ ብርሃን ዩኒቨርስቲ የሁለተኛ ዓመት የኪሚካል ኢንጂነሪንግ ተማሪ ሆኗል፡፡ ዩኒቨርስቲም ሆኖ ግን ቅርጫት ኳስን አልተወም፡፡

“አሁን በቅርብ ጊዜ ከትምህርት ጋር በተያያዘ ጊዜ ትንሽ አጣን እንጂ በትንሹ በሳምንት አራቴ እለማመዳለሁ፡፡ ዩኒቨርስቲ ገብቼ አሁንም ቅርጫት ኳስ እጫወታለሁ፡፡ የማቋርጥ አይመስለኝም፡፡ እዚህ የዩኒቨርስቲ ውድድሮች አሉ፡፡ ትንሽ በረብሻ ምክንያት አልተጀመሩም፡፡ በዚህ ዓመት አለ እየተባለ ነው፡፡ በቅርቡ ልምምድ እንጀምራለን” ይላል ሰቢት፡፡

ሰቢት የልጅነት ጊዜውን ሲያስታውስ ቀድሞ ከፊቱ ድቅን የሚለው ከሰፈሩ ልጆች ተጠራርቶ፣ የተገኘውን ቀማምሶ፣ ወደ ቅርጫት ኳስ ሜዳ የሚደረገው ሩጫ ነው፡፡ ተወልዶ ያደገበት “ኒው ላንድ” በመባል የሚታወቀው የኑዌር ተወላጆች የሚበዙበት ሰፈር ቢሆንም ለጨዋታ የሚቧደነው ለቅርጫት ኳስ ፍቅር ካለው ማንኛውም ታዳጊ ጋር እንደነበር ያስታውሳል፡፡ ቅርጫት ኳስ “አንድነታችንን አጠናክሮታል” ብሎ ያምናል፡፡

ይህን እምነቱን  እንደ እርሱ ከልጅነቱ ከቅርጫት ኳስ ጋር ያደገው የጋምቤላ ተወላጅ ባን ኪል ይጋራዋል፡፡ ገና የ12 ዓመት ልጅ እያለ ቅርጫት ኳስን መጫወት የጀመረው ባን ያለምንም አሰልጣኝ እና ደጋፊ ታላላቆቹን በማየት ብቻ ብቁ ተጫዋች ወጥቶታል፡፡ የእርሱን እና ጓደኞቹን ጥረት የተመለከተ አሰልጣኝ የታዳጊዎች “ፕሮጀክት” አቋቋሞ በዚያ እንዲታቀፉ ያደርጋቸዋል፡፡ ከአሰልጣኙ የቀሰማቸውን ክህሎቶች አዲስ አበባ ለትምህርት ቤቶች ውድድር የሄደ ወቅት በሚገባ ይተገብረዋል፡፡ ይሄኔ የኢትዮጵያ ወጣቶች ስፖርት አካዳሚ ሰዎችን ቀልብ ይይዝና በ14 ዓመቱ በአዲስ አበባ ቀርቶ ስልጠና እንዲከታተል ይሆናል፡፡

ምስል Naath Youth Foundation

ላለፉት ሶስት ዓመታት በስፖርት አካዳሚ የቆየው ባን የኢትዮጵያ የወጣቶች ቅርጫት ኳስ ብሔራዊ ቡድን ተመራጭ ሆኗል፡፡ ቅርጫት ኳስ እንደእርሱ ላሉ ወጣቶች የተሻለ ዕድል ከመክፈት ባሻገር ጠቀሜታው ላቅ ያለ እንደሆነ ያስረዳል፡፡ በጋምቤላ አልፎ አልፎ የሚከሰተው ብሔር ላይ ያተኮረ ውጥረት ቅርጫት ኳስ ሜዳ ላይ ሲደርስ ድራሹ ይጠፋል ባይ ነው፡፡

“እዚያ ብዙ ሰው ታገኛለህ፡፡ ከማታውቀው ሰው ጋር ትገናኛለህ፡፡ ጠብ ያላቸው ሰዎች እንኳ እዚያ ቅርጫት ኳስ ሜዳ ከሄዱ ይገናኛሉ፡፡ ፍቅር ያለው ጨዋታ ነው፡፡ ሁሉም ሰው ይዋደዳል፡፡ ማንኛውም ሰው ይጫወታል፡፡ ያው ሁሉም ብሔር ነው [የሚመጣው]፡፡ ጋምቤላ አምስት ብሔር ነው ያለው፡፡ በጣም ቅርጫት ኳስ የሚጫወቱት ኑዌር እና አኙዋዎች ናቸው፡፡ የጋምቤላ ነገር በኑዌር እና በአኙዋዎች መካከል ያለው ፖለቲካዊ ነው፡፡ ግን ሜዳ ስንገባ ያ ነገር ይጠፋል፡፡ ኑዌር እና አኙዋ ስለተጣላ ቅርጫት ኳስ አንጫወትም የሚል የለም፡፡ እዚያ በፍቅር ነው የምንጫወተው” ይላል የቅርጫት ኳስ ሚና ሲያስረዳ፡፡

በጋምቤላ ክልል ካሉ አምስት ነባር ብሔረሰቦች ውስጥ በህዝብ ብዛት ከፍተኛውን ድርሻ የያዙት ኑዌር እና አኙዋሃ ናቸው፡፡ በሁለቱ ብሔረሰብ ተወላጆች መካከል በስልጣን እና በተፈጥሮ ሃብት ይገባኛል ጥያቄዎች መንስኤነት በየጊዜው የሚያመረቅዝ ግጭት ይከሰታል፡፡ በእብዛኛው በግጭቱ ውስጥ ዋነኛ ተዋናይ የሚሆኑቱ ወጣቶች ቅርጫት ኳስ ሜዳ ሲገናኙ ልዩነቶቻቸውን ወደ ጎን አድርገው ነው፡፡ ጨዋታው እርስ በእርስ እንዲነጋገሩ፣ አንዱ የሌላኛውን አስተሳሰብ፣ አኗኗር እና ባህል እንዲረዱ እንዳደረጋቸው ወጣቶቹ ይናገራሉ፡፡

ቅርጫት ኳስ ለማህበረሰቡ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ ተቀማጭነቱ በአሜሪካ የሆነውን ናዝ የወጣቶች ፋውንዴሽን ወደ ጋምቤላ እንዲመለከት አድርጎታል፡፡ አሜሪካ በሚኖሩ ደቡብ ሱዳናውያን አማካኝነት የዛሬ አራት ዓመት የተቋቋመው ፋውንዴሽን በጋምቤላ ሶስት የቅርጫት ኳስ ውድድሮች አዘጋጅቷል፡፡ መጫወቻ ኳሶች እና ትጥቆችን ለወጣቶች አከፋፍሏል፡፡ በደቡብ ሱዳን እና ኢትዮጵያ ድንበር ላይ በምትገኝ ከተማ የቅርጫት ኳስ ሜዳ ሰርቷል፡፡

በፋውንዴሽኑ በጸሀፊነት በማገልገል ላይ የሚገኙት እና የጋምቤላው የቅርጫት ኳስ ውድድር አስተባባሪ የነበሩት ቦል ሪንግ በጋምቤላ የሚያደርጉት እንቅስቃሴ ከዋና ዓላማቸው የሚመነጭ እንደሆነ ያስረዳሉ፡፡ የፋውንዴሽኑ ዋና ተልዕኮ ስፖርታዊ፣ ትምህርታዊ እና ባህላዊ ዝግጅቶችን በማዘጋጀት ወጣቶች ከሁከት እና ብጥብጥ እንዲርቁ ማድረግ ነው፡፡  

“ወጣቶችን በበጎ ነገሮች እንዲጠመዱ ካደረግካቸው ችግር ውስጥ በሚከታቸው ድርጊቶች ውስጥ የመሳተፋቸው ዕድል የመነመነ ይሆናል፡፡ በጋምቤላ ያዘጋጀነው ውድድርም በዚህ መንፈስ ነው፡፡ መጀመሪያ ቅርጫት ኳስ መጫወት የሚፈልጉ ሁሉንም ወጣቶች ጠራን፡፡ ሚዛናዊ ለመሆን፣ ወጣቶቹ ከሌሎችም ጋር እንዲቀላቀሉ በማሰብ የራሳቸውን ሰዎች ብቻ እንዳይመርጡ አደረግን፡፡ የተከተልነው ዘዴ ምን ነበር? ከአንድ እስከ አምስት ጽፈን በቅርጫት ውስጥ አስቀመጥንና ወጣቶቹ ቁጥሩን እንዲያወጡ አደረግን፡፡ ቁጥሩን ባወጡ ቁጥር በዚያ ቡድን ውስጥ እንዲካተቱ አደረግን፡፡ በዚህም በተለያዩ ቡድኖች ውስጥ የብሔሮች ስብጥር ኖረ፡፡ እንዲህ ዓይነት አንድነት ካላቸው ከግጭት እንዲርቁ ይሆናሉ” ይላሉ፡፡       

ምስል Naath Youth Foundation

ከስፖርታዊ እንቅስቃሴ እና ከመዝናኘነቱ በሻገር በጋምቤላ ጥቅሙ ከፍ ያለው የቅርጫት ኳስ ተገቢውን ትኩረት አለማግኘቱን የክልሉ ወጣቶች ይናገራሉ፡፡ ባሮ ወንዝ አጠገብ ካለው በክልሉ ከተሰራው ጂኒና ሜዳ ውጭ ሌሎች መጫወቻ ቦታዎች ያሉት በካቶሊክ እና አንግሊካን አብያተክርስቲያናት ውስጥ ነው፡፡ ከጋምቤላ ከተማ ውጭ በክልሉ ሁለት ሶስት ቦታ ብቻ ደረጃቸውን የጠበቁ መጫወቻ ሜዳዎች እንዳሉ ይናገራሉ፡፡ የ17 ዓመቱ ባን ለቅርጫት ኳስ ያለው አመለካከት በጋምቤላ ብቻ ሳይሆን በሌሎች የኢትዮጵያ አካባቢዎችም አናሳ እንደሆነ ይገልጻል፡፡

“ጋምቤላ ውስጥ ብቻ ሳይሆን ኢትዮጵያ ውስጥ ቅርጫት ኳስ ትኩረት የለውም፡፡ ሁሉ ነገር የሚሟላው እና ትኩረት ያለው እግር ኳስ ላይ ነው፡፡ ግን በጋምቤላ ክልል ጎበዝ የሚባሉ ተጫዋቾች የቅርጫት ኳስ ተጫዋቾች ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ የክልሎች ደረጃ ሲኖር ቅርጫት ኳስ ነው አሪፍ ደረጃ የሚያመጣው፡፡ ቅርጫት ኳስ የምትጫወት ከሆነ እና ሌሎች ትኩረት የማይሰጡት ከሆነ ተስፋ ያስቆርጣል” ሲል ስፖርቱ ከክልሉ የሚያገኘው ድጋፍ አነስተኛ እንደሆነ ይናገራል፡፡

የጋምቤላ ወጣቶች ተገቢውን ትኩረት ካገኙ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ አንዱ ማመላከቻው በሀገር አቀፍ ደረጃ ያላቸው አመርቂ ውጤት እና ከክልሉ የፈለቁ ወጣቶች የተጓዙበት ርቀት ነው፡፡ የናዝ ፋውንዴሽኑ ቦል በቅርጫት ኳስ ክህሎታቸው ተመርጠው ከጋምቤላ አሜሪካ ለትምህርት ዕድል የተጓዙ አምስት ወጣቶች እንዳሉ ይናገራል፡፡ በትምህርት ቤቶች እና ክልሎች ውድድር ላይ ከጋምቤላ ተወላጆች ጋር አብሮ የመጫወት ዕድል የገጠመው የ21 ዓመቱ ባንተአምላክ ፈለቀም ስለ ጋምቤላ ወጣቶች ክህሎት ከሚመሰክሩት አንዱ ነው፡፡

ከዚህ በፊት በክልል ጨዋታ ላይ ከጋምቤላ ጋር የዋንጫ ደርሰን ነበር፡፡ አብዛኞቹ ረጃጅም ናቸው እና ትንሹ የሚባለው አንድ ሜትር ከሰማንያ ነው፡፡ ረጅም ሲኾን የጨዋታው ክህሎት እምብዛም አይደለም፡፡ ተቀብለህ ኳሱን ለማስቆጠር በጣም ቀላል ቴክኒኮችን በመጠቀም ነው ማስገባት የሚቻለው፡፡ እነርሱ ግን ረጅምም ሆነው የማጣጠፍ እና አንጥሮ የማለፍ የዳበረ ክህሎት ነው ያላቸው” ይላል ባንተአምላክ፡፡

የጋምቤላ ወጣቶች ተፈጥሮ ያደለቻቸውን ፀጋ ተጠቅመው ወደተሻለ ደረጃ ለመሸጋገር ትኩረት እና ድጋፍ ያሻሉ፡፡ እስከዚያው በጂኒና ያፈሰሱትን ላብ በባሮ እየተለቃለቁ መቀጠላቸው አይቀሬ ይመስላል፡፡

 

ተስፋለም ወልደየስ 

ኂሩት መለሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW