1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቅርጽና አድማሱን ያሰፋው የሱዳን ጦርነት

ቅዳሜ፣ ሰኔ 10 2015

ሦስት ወራት ባለፈው የሱዳን ጦርነት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሺህ መብለጡ ተዘግቧል ። በጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን በሚመራው የሱዳን ጦር ሠራዊት (ASF) እና በቀድሞ ምክትላቸው ሞሐመድ ሀማዳን ዳግሎ በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል ሚያዚያ 7 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የፈነዳው ውጊያ እንደቀጠለ ነው ።

Sudan West Darfur | Geneina
ምስል Satellite image ©2023 Maxar Technologies/AFP

ጦርነቱ ቅርጽና አድማሱን እየቀየረ ነው

This browser does not support the audio element.

ሁለት ወራት ባለፈው የሱዳን ጦርነት የተገደሉ ሰዎች ቁጥር ከ2 ሺህ መብለጡ ተዘግቧል ።   በጄኔራል አብዱል ፈታህ አልቡርሀን በሚመራው የሱዳን ጦር ሠራዊት (ASF) እና በቀድሞ ምክትላቸው ሞሐመድ ሀማዳን ዳግሎ በሚመራው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል (RSF) መካከል ሚያዚያ 7 ቀን፣ 2015 ዓ.ም የፈነዳው ውጊያ እንደቀጠለ ነው ። በውጊያው ለሥልጣን ከሚሻኮቱት ሁለቱ ጄኔራሎች አንዳቸውም በቅርቡ አሸንፈው አይወጡም እየተባለ ነው ። ቴዎዶር መርፊ በአውሮጳ ካውንስል የውጭ ግንኙነት የአፍሪቃ መርኃ ግብር ኃላፊ ናቸው ።

«ሱዳን ውስጥ በግጭቱ ከሁለቱ ተፋላሚ ጄኔራሎች በፍጥነት አንዱ እንደማያሸንፍ ግልጽ እየሆነ ነው ። ይልቁንም ከሁለቱም በኩል የበለጠ ድጋፍ በማግኘት ሌላውን አዳክሞ ጎልቶ መውጣቱ ላይ ነው ያተኮረው ።  ያ ድጋፍ ከውጭ ኃይላት ሊሆን ይችላል ። ማለትም ከቀጣናው ደጋፊዎች የሚገኝ የገንዘብ እና የጦር መሣሪያ ድጋፍ ። ሱዳን ውስጥ ያሉ የአማጺ ቡድኖች አንዱ በአንዱ ላይ እንዲነሱ በማድረግ የሚገኝ ውስጣዊም ሊሆን ይችላል ። »

ሱዳን ውስጥ እስካሁን ከሞቱ ከቆሰሉት በተጨማሪ 2.2 ሚሊዮን ሰዎች በጦርነቱ ዳፋ ከቀያቸው ተፈናቅለዋል። ዓለም አቀፉ የፍልሰት ጉዳዮች ድርጅት እንደሚለው ከተፈናቃዮቹ መካከል 528 ሺሁ ወደ ጎረቤት አገራት ተሰደዋል። 

ግድያ የተፈጸባቸው በምዕራብ ሱዳንዋ የዳርፉር ግዛት ሀገረ-ገዥ ክሀሚስ አብደላ አባካርምስል SUNA/AFP

በምዕራብ ሱዳንዋ የዳርፉር ግዛት ራቅ ያለ አካባቢ ደግሞ አንድ ሀገረ-ገዥ ሰሞኑን ተገድለዋል። ሀገረ ገዥው ክሀሚስ አብደላ አባካር የተገደሉት ለሳዑዲ አረብያ የቴሌቪዥን ጣቢያ ፈጥኖ ደራሹን ኃይል የሚተች አስተያየት ከሰጡ ከጥቂት ሰዓታት በኋላ ነበር ተብሏል ። ስለ አካባቢው በጥልቀት የሚያውቁ የሀገረ ገዢው መገደል ጦርነቱን ከካርቱም ወደ ዳርፉር በመሳብ ድጋፍ የማግኘት ስልት ነው ይላሉ ። በዋናነትም ካርቱም ውስጥ ብዙም ደጋፊ የሌለው የፈጥኖ ደራሹ ኃይል ቀድሞ ከፍተኛ ድጋፍ ያገኝበት የነበረው የዳርፉር ማኅበረሰብን ለመሳብ የወሰደው ርምጃ ነው የሚሉም አሉ ። የመንግሥት መዋቅር ካርቱም ውስጥ እዙ ስለተበጠሰም ጦር ሠራዊቱም ቢሆን ከማኅበረሰቡ የሚያገኘው ድጋፍ አጠያያቂ ነው ።

በዚህም አለ በዚያ ግን ጦርነቱን በጦር ኃይል ማሸነፍ እንደማይቻል ሁኔታዎች እያመላከቱ ነው ። ግጭቱ ምናልባትም ወደ ተለያዩ የኅብረተሰቡ ክፍሎችና ጎሳዎች እንዳይሻገርም አሥግቷል ። ሐገር ዓሊ በጀርመኑ የዓለም አቀፍና አካባቢ ጥናት ተቋም (GIGA) ተመራማሪ ናቸው ።

«ፍልሚያው ከሞላ ጎደል አደገኛ እየሆነ መምጣቱ ገና ከመመነሻው አደገኛ ስለነበረ ነው ማለት አይደለም ። ይልቁንም ዋናው አሁን ካለበት ከካርቱም የጦር አውድ በምን ያህል ፍጥነት ይዛመታል፤ የሥልጣን ሽኩቻውስ ምን ያህል የከፋ ይሆናል የሚለው ነው ። አል ቡርሃን እና ዳጋሎ ሁለቱም መላወሻ መፈናፈኛ አጥተዋል ። ካርቱም ውስጥ ያለው የሥልጣን ሽኩቻቸውም በጦር ኃይል ብቻ የሚወሰን አለመሆኑ በጣም ግልጽ ሆኗል ።  እናም ሙሉ ለሙሉ ወሳኝ ድል ማግኘቱ አሁን ከጥያቄ ውጪ ሆኗል ።»

ውጊያ የሚካሄድባት የሱዳን ዋና ከተማ ካርቱምምስል AFP/Getty Images

ሱዳን ውስጥ የኤስታናድ ምርምር ተቋም ማእከል ተባባሪ መሥራች ሙዛን ዓልኔል እንደሚሉት፦ በግጭቱ የተነሳ በቅርቡ ሱዳን ውስጥ ረሐብ መከሰቱ አይቀርም ።

«የአቅርቦት እጥረት ባለባት ሱዳን በሲቪሉ ማኅበረሰብ መካከል በማንኛውም ሁኔታ ግጭት እንዳይፈጠር ሥጋት አጭሯል ። ሱዳን ውስጥ   በግልጽ ወደ ረሐብ እያመራን በመሆኑ በማኅበረሰቡ ዘንድ ግጭቱ በሚቀጥሉት ወራት ይከሰታል ተብሎ ይጠበቃል ። በእቅዱ መሠረት የእርሻ ሥራ አልተከወነም ። ከጥቂት ሳምንታት በፊትም ለመጀመሪያ ጊዜ ምናልባትም በቅርብ ጊዜ ታሪካችን ለመጀመሪያ ጊዜ እርሻ ሳይከወን መቅረቱ ነው ።»

ያም በመሆኑ በሚቀጥሉት ወራት እና በክረምት ወቅት ሕዝቡ የሚመገበው ስለመኖሩም እጠራጠራለሁ ሲሉ አክለዋል ።  

ሌሎች ተንታኞች እንደሚሉት ከሆነ ሱዳን ውስጥ በተለይ ካርቱም ከተማ ነዋሪዎች ራሳቸውን ለመጠበቅ በአብዛኛው ጦር መሣሪያ ታጥቀዋል ። እናም ከሁለቱ ጀነራሎች አንዱም አሸናፊ ሆኖ የመውጣቱ ነገር በአጠራጠረበት ወቅት በርካታ የካርቱም ነዋሪዎች በመሀል ብቅ ወደሚሉ የጎበዝ አለቆች መስመር ሊሰለፉ ይችላሉም ተብሏል ። ያ ከሆነ ደግሞ በሁለት ጄኔራሎች የሥልጣን ሽኩቻ የጀመረው ጦርነት ማኅበረሰቡን በጎሳ እና በአካባቢ ለይቶ ወደ ሰፊ የርስ በርስ ጦርነት ሊያቀናም ይችላል ተብሏል ። የዳርፉር የሰሞኑ ግድያ አንደምታም ያን የሚያመላክት ይመስላል ።

ማንተጋፍቶት ስለሺ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW