1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የቆምጬ አምባው ታላቁ ስልቱ “ማስገደድ ሳይሆን ማስወደድ ነበር”

ሐሙስ፣ ነሐሴ 16 2016

ቆምጨ አምባው ሌላው የሚታወቁበት፣ እርሳቸው ይበሉትም አይበሉትም፣ ቀልዳቸው ነው፡፡ ቆምጬ አምባው ብለዋቸዋል ከሚባሉ ቀልዶች መካከል በአንድ እግር ኳስ ሜዳ 22 ተጫዋጮች በአንድ ኳስ ሲጫወቱ አይተው፣ “ እንዴት 22 ሰዎች በአንድ ኳስ ይጫወታሉ? ተቸግረው ይሆን?” በማለት ለእያንዳንዱ ተጫዋች ኳስ ገዝተው ሰጥተዋል የሚል ነው

Äthiopien Ato Komchambaw
ምስል private

ቆምጨ አምባው

This browser does not support the audio element.

ቆምጨ አምባው የተባለው ስም በተለይ በጎጃም የታወቀና ገናና ነው፡፡  ቆምጨ አምባው በቀድሞው የኢትዮጵያ መንግስት አስተዳደር (ደርግ) ከ1970ዎቹ እስከ 1983 ዓ.ም በነበሩት ጊዜያት 5 ወረዳዎችን እየተዘዋወሩ በዋና አስተዳዳሪነት መርተዋል፣ ምክትል የአውራጃ አስተዳዳሪም ሆነው አገልግለዋል፡፡ ታዲያ ቆምጨ የወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው በሚሰሩበት ወቅት በሽፍትነትና በውንብድና  ተጠርጥረው ጫካ የገቡ ሰዎችን በምህረትና በይቅርታ በማስገባት፣ በማስተማር፣ በማስታረቅ፣ ለዓመታት የተወዘፈ ግብርን በማሰባሰብ፣ የመሰረተ ትምህርት ግቡን እንዲመታ በማድረግ፣ በችግኝ ተከላና ሌሎችንም የተሰጣቸውን የመንግስት ስራዎች በቅልጥፍናና በታማኘነት  በመፈፀም በእጅጉ ይታወቃሉ፡፡
ውልደትና ትምህርት
ቆምጨ አምባው ውልደታቸው ከእናታቸው ወ/ሮ የሹሜ ዓይናልምና ከፊታውራሪ አምባው ይልማ በቀድሞው ጎጃም ክፍለ ሀገር ደብረማርቆስ አውራጃ ጎዛምን ወረዳ “ማንጅአንገታም” ቀበሌ በ1941 ዓ.ም አካባቢ እንደሆነ ራሳቸው ባለታሪኩ ነግረውናል፡፡
በቤተክህነት ትምህርት  ዳዊት፣ ፆመ ድጓ፣ ድጓና ዲቁና ተምረው በዲቁና ቤተክርስቲያንን አገልግለዋል፡፡ በዘመናዊ ትምህርት ደግሞ  እስከ 10ኛ ክፍል ተምረዋል፡፡
የቆምጬ ስያሜ
ቆምጨ አምባው ስማቸውን ያገኙት በአጋጣሚ ነው፡፡ አባታቸው “መስፍን” የሚል ስም ሰጥተዋቸው እንደነበርና እናታቸው ደግሞ “ልንገርህ” ብለው ይጠሯቸው ነበር፤ ቆምጨ የሚለው ስያሜ ታዲያ ከየት መጣ?
አቶ ቆምጨ አምባው የሚጠሩበት ስም እንዴት ወጣ
“በተኩስ ኢላማ ልምምድ ወቅት ወንድሜን እንዴት ነው የሚተኮስ? ብዬ ስጠይቀው “አንተ እኮ መንፈሳዊ ነህ፣ ተኩስ ምን ያደርግልሀል?” ብሎ ከለከለኝ፣ እኔ ግን መሳሪያ እያሾለክሁ እየወሰድኩ ኢላማ በመምታት እለማመድ ነበር፣ ከዚያም ወንድሜ “እርሱ እኮ ሲተኩስ ቆምጨ ነው (ቆምጦ ይጥላል ለማለት ይመስላል) ይለኝ ነበር፣ እንደቀልድ ስሙ እንደዚያ ወጣ፣ እናቴ ልንገርህ ነው የምትለኝ፣ አባቴ ደግሞ መስፍን ነው የሚለኝ እና ቆምጬ የሚለው ስም ገንኖና ደምቆ ቀረ” ብለዋል፡፡

አቶ ቆምጨ አምባውምስል private


የስራ ዓለም
ቆምጬ አምባው ትዳር በቤክርስቲያን ስርኣት ዲያቆን ሆነው ቢመሰርቱም በወቅቱ በተነሳ የእንስሳት በሽታ በርካታ እንስሳቶቻቸው በመሞታቸው “በምን እተዳደራለሁ?” በሚል ጭንቅ ውስጥ ይገባሉ፣ የመንግስት ስራ ማፈላለግ ይጀምራሉ፣ በወቅቱ አንድ በመንግስት አስተዳደር ውስጥ የሚሰሩ ዘመዳቸው ጋ ይሄዱና የመንግስት ስራ የሚያገኙበትን መንገድ ያማክራሉ፣ በወቅቱ አስተዳደር ውስጥ እርሳቸውን የሚያስቀጥር የስራ መደብ እንደሌለ እኚህ ዘመዳቸው ይገልፁላቸዋል፣  ግን በማረሚያ ቤት በወታደርነት መቀጠር እንደሚችሉ ሲነግሯቸው ማመልከቻቸውን ይዘው ወደ ቦታው  ይሄዳሉ፣ ይቀናቸውና በዚያው በደብረማርቆስ ማረሚያ ቤት አስተባባሪ ሆነው ይቀጠራሉ፡፡ በሂደትም የጎጃም ጠቅላይ ግዛት ማረሚያ ቤቶች የህግ አማካሪና ጉዳይ አስፈፃሚ ሆነው እንዲሰሩ ተመደቡ፡፡ በውትድርናው ዓለም እስከ 10 አለቅነት ማዕረግ ደርሰዋል፣ የታራሚዎችን አያያዝ በማሻሻል ውጤታማ ስራ እንዳከናወኑ ይነገረላቸዋል፡፡
በአንድ ስብሰባ ላይ የተናገሩት ንግግር ግን የህይወታቸውን አቅጣጫ እንደቀየረው 10 አለቃ ቆምጬ ያስታውሳሉ፤ አንድ ቀን በተጠራ ስብሰባ ላይ የታራሚዎች አያያዝ እንዲሻሻል፣ ማረሚያ ቤቱ በጥበቃ እንዲጠናከር “ግሩም” የተባለ ንግግር እንዳደረጉ ቆምጬ ይገልጻሉ፤ “ለውጥ በእጅጉ ያስፈልጋል” ሲሉም በአፅዕኖት ይወተውታሉ፡፡
 ይህን ንግግር ባደረጉ በሶስተኛው ቀን የጠቅላይ ግዛቱ የደህንነት ኃላፊ ወደ ቢሯቸው ይጠሯቸዋል፣ ቆምጬ “ባለፈው ንግግሬ ምን ስህተት ፈፅሜ ይሆን? እያሉ እየተጨነቁና እየተከዙ ከባለስልጣኑ ቢሮ ይደርሳሉ፣ የጠበቃቸው ግን ወቀሳና እርሳቸው እንዳሰቡት ለስጋት የሚጥል ነገር አልነበረም፡፡ በወቅቱ አንድ ስብሰባ ላይ ያደረጉት ንግግር ከፍ ወዳለ ቦታ አሳጭቷቸዋል፡፡ “የወረዳ አስተዳዳሪ እንድትሆን አጭተንሀል” የሚል ነገር ይነገራቸዋል፡፡ በወቅቱ ፈቃደኛ ባይሆኑም ከቤተሰቦቻቸው ጋር ሰፊና ተከታታይ ውይይት ካደረጉ በኋላ ፈቃደኛ ሆነው የቢቡኝ ወረዳ አስተዳዳሪ ሆነው እንዲሰሩ መመደባቸውን ለዶይቼ ቬሌ ተናግረዋል፡፡
ቆምጬ ወደ ቢቡኝ ወረዳ  እንደደረሱ የመጀመሪያ ስራቸው ሽፍታንና በወንጀል የሚጠረጠሩ ጫካ የገቡ ሰዎችን በምህረት ማስገባትና የተወዘፈ ግብርን መሰብሰብ ሆነ፣ በዚህም ውጤታማ ሥራ በማከናወናቸው በህዝቡና በመንግስት ባለስልጣናት ዘንድ ከፍተኛ እምነትና ከበሬታን አግኝተዋል፡፡ ቆምጬ በሁለት እጁ አነሴ፣ በእናርጅ እናውጋ፣ በማቻከልና አቸፈር ወረዳዎች በዋና አስተዳዳሪነት ተመድበው ተመሳሳይ ወንጀልን የመቀነስና ግብርን የመሰብሰብ፣ እንዲሁም የመሰረተ ትምህር ውጤታማ በሆነ ሁኔታ ጎልማሶች እንዲማሩ አድርገዋል፣ ሰፊ የችግኝ ተከላ እንዲካሄድ ውጤታማ ስራ አከናውነዋል፣ ስታዲዮሞችና ድልድዮች እንዲሰሩ ሰፊ ስራ በማከናወን ውጤታማ ሆነዋል፡፡

አቶ ቆምጨ አምባውምስል private


ቆምጨጬ አምባውና “ቀልደዋቸዋል” የተባሉ ቀልዶች
ቆምጨ አምባው ሌላው የሚታወቁበት፣ እርሳቸው ይበሉትም አይበሉትም፣ ቀልዳቸው ነው፡፡ ቆምጬ አምባው ብለዋቸዋል ከሚባሉ ቀልዶች መካከል በአንድ እግር ኳስ ሜዳ 22 ተጫዋጮች በአንድ ኳስ ሲጫወቱ አይተው፣ “ እንዴት 22 ሰዎች በአንድ ኳስ ይጫወታሉ? ተቸግረው ይሆን?” በማለት ለእያንዳንዱ ተጫዋች ኳስ ገዝተው ሰጥተዋል የሚል ነው፣ ሌላው ደግሞ በህዝብ ትራንስፖርት ሲጓዙ ከመኪናው በተገጠመ ራዲዮ ዜና ሲነበብ ስማቸው በዜናው ሲጠቀስ ሰሙና ሾፌሩን መኪናውን እንዲያቆመው በማዘዝ “ቆምጨ አምባው ማለት እኔ ነኝ” በማለት ተሳፋሪው እንዲያውቃቸው አድርገዋል ይባላል፣ በስፋት የሚነገረው ደግሞ፣ የመሰረተ ትምህርትን ውጤታማነት ፕሬዚደንት መንግስቱ ለመጎብኘት ወደነቆምጬ አምባው በሄዱበት ወቅት ቆምጬ ለሁሉም የመሰረተ ትምህርት ተማሪዎች ማንበብ የሚችለውም ሆነ የማይችለው የሚያነብብ እንዲመስል ለሁልም ጋዜጣ ያሰራጫሉ፣ መንጌ ጉብኝቱን ሲያደርጉ አንድ ተማሪ ጋዜጣውን ያለማስተዋል ዘቅዝቆ ይዞ ያዩታል፣ መንጌም ተማሪውን “ለምን ጋዜጣውን ዘቅዝቀህ ያዝክ” ብለው አስተካክለው ሊሰጡትሰ ሲሉ ተማሪው “አይ ቆምጨ ይቆጣሉ፣ እንደዚህ አድርገህ ያዝ ነው ያሉኝ” ብሎ አጋልጦ ሰጥቷቸዋል ይባላል። ቆምጨ ተሳፍረው የሚሄዱበት መኪና ሞተር ይጠፋና መኪናው ይቆማል፣ "ሞተር ጠፋ! ሞተሩ ጠፋ!" ሲባል የሰሙት ቆምጬ  “ ማነው ሞተሩን የሰረቀው” ብለው ተሳፋሪ እንዲበረበር (እንዲፈተሸ) አድርገዋል ይባላል። “መሰረት ትምህርት የማይማር ቡዳ ነው” ብለውም የአካባቢው ገበሬዎች ቡዳ እንዳይባሉ ወደ መሰረተ ትምህርት እንዲሄዱ አድርጓልም ይባላል። ስለቀልዶቹ ቆምጬ አምባውን ጠየቅናቸው፣ ቆምጬ ግን አብዛኛውን አይቀበሉትም። “የተባለው ሁሉ ከእውነት የራቀና ሀሰት ነው” ሲሉ መልሰዋል፡፡ “ታዲያ ይህ ነገር እንዴት ሊፈጠር ቻለ?” ሰንል ጠየቅን፣ ቆምጬ ሲመልሱ፣ “እንዴት ቆምጬ በከፍተኛ ባለስልጣናት እውቅና ሊያገኝ ቻለ?፣ አልተማረም፣  እኛ ዲግሪና ከዚያ በላይ የተማርን ነን፣ ልምድ አለን፣ የተሻለ ስልጠና እኛ አለን ግን ቆምጬ ጎልቶ እንዴት ሊወጣ ይችላል? በሚል ቅናተኞች የሚያስወሩብኝ ነገር ነው፣ ሁሉንም በሚዛን የማይና በስርዓት ያደግሁ ሰው ነኝ” ሲሉ ነው የተባለውን ሁሉ ያስተባበሉት፡፡
ያም ሆኖ በግብርና ስራ ተሰማርቶ ከተማ ለከተማ “ሲያውደለድል” የሚውለውን ያሉትን ገበሬ፣ “ጠንክሮ የማያርስ ወፍራም ጠላ  አይጠጣም” በማለት መልዕክት በማስተላለፋቸው “የከተማ አውደልዳይ” ያሉትን አካል ወደ እርሻ እንዲገባ ማድረጋቸውን አልሸሸጉም፡፡

አቶ ቆምጨ አምባውምስል private


ምስጋናና እውቅና
ኮሎኔል መንግስቱ ኃይለ ማሪያም በአንድ የብሔራዊ ሸንጎ ሰብሰባ ላይ እውቅና እንደሰጠዋቸው ቆምጬ ያስታውሳሉ፡፡ “ራሳቸው ፕረዚደንት መንግስቱ “እንደ ጓድ ቆምጬ ያለ እስከ አፍንጫው የታጠቀውን ሽፍታ በማግባባትና በማሳመን የሚያስገባና ቤተሰብ እንዳይበተን ወንጀለኞች ትምህርት ቤት እንዲገቡ በማድረግ፣ “ካልተማራችሁ ወንጀል መቀነስ አትችሉም” በማለት የሀገሪቱ መንግስት የሚሰራባቸውን ህጎች ማወቅ እንዳለባቸው አስተምሯል፣ አስተምሮና አርቆ ወንጀለኞችን የሚያስገባ ነው፡፡” ብለውኛል ሲሉ አስረድተዋል፡፡ ቆምጬ አምባው ለሰሯቸው ስራዎች በርካታ የምስጋናና የእውቅና ምስክር ወረቀቶችም ተሰጥቷቸዋል፡፡
ምስክርነት
ቆምጨ አምባውን በቅርብ የሚያውቋቸው የደብረማርቆስ ከተማ ነዋሪ አቶ መሐሪ ዘውዴ “ቆምጬ አምባው ለህዝብ የሚሰሩ፣ ህዝብ የሚወዳቸው ቆራጥና ብልህ መሪ ናቸው” ሲሉ ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል፡፡
በወንጀል የሚጠረጠሩ ሰዎችን በጥበብ፣ በብልሀት፣ ቄስና መነኩሴ  በመያዝ በመለመንና በማስለመን ከፍ ሲልም ታቦት ይዞ በመማለድ ተጠርታሪ ሽፍፍቶች በሰላም ወደ ማህበረሰቡ እንዲገቡ ያደርጉ እንደነበርና ችግር የነበረባቸው በእርቅና በይቅርታ እንዲፈታ ያስደርጉ እንደነበርም  አቶ መሐሪ ይናገራሉ፡፡ የቆምጬ አምባው ታላቁ ስልቱ “ማስገደድ ሳይሆን ማስወደድ ነበር” ብለዋል አቶ መሐሪ፡፡
የቆምጬ አምባው መልዕክትና አሁን ያሉበት ደረጃ
ቆምጨ አምባው በመጨረሻም አሁን በአገራችን፣ በተለይም በአማራ ክልል ያለው የፀጥታ ችገር ሰላማዊ በሆነ መንገድ እንዲጠናቀቅ ጥሪ አቅርበዋል፡፡ “የገደለው ልጅሽ፣ የሞተው ወንድምሽ ሐዘንሽ ቅጥ አጣ አልወጣ ከቤትሽ” ነው ነገሩ ብለውታል የወቅቱን የአማራ ክልልን የፀጥታ ሁኔታ፡፡
ቆምጬ አምባው ከ1970ዎቹ መጀመሪያ ጀምሮ እስከ 1983 ዓ.ም በመንግስት ስራ ላይ ቆይተዋል፣ ጡረታ ከወጡ ረዘም ላለ ጊዜ ያሳለፉ ቢሆንም በግላቸው የህግ አማካሪ ሆነው ይሰራሉ፣  ቆምጬ አምባው የልማት አምባሳደር ሆነው እንዲሰሩ በአማራ ክልል መንግስት እውቅና ተሰጥቷቸውም የማስተባበር ስራ እየሰሩ አንደሆነ ነግረውናል፡፡
ዓለምነው መኮንን 
ዮሃንስ ገብረእግዚአብሄር

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW