1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ቆሻሻ እንደ ሸቀጥ?

Eshete Bekele
ረቡዕ፣ መስከረም 11 2015

ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን የሚያቀነቅነው"ሰርኩላር ኤኮኖሚ" የምጣኔ ሐብት ሞዴል የከባቢ አየር ለውጥ፣ የሥርዓተ ምኅዳር ውድመት፣ የቆሻሻ ክምችት እና ብክለትን ለመቋቋም መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል። በዘርፉ እውቀት እና ቴክኖሎጂ ያላቸው የጀርመን ኩባንያዎች በአዲስ አበባ ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው በጉዳዩ ላይ እየመከሩ ነው። እጅ ከምን?

BG | Chile Atacama Wüste Altkleider Zusatz
ምስል MARTIN BERNETTI AFP via Getty Images

ከኤኮኖሚው ዓለም፦ ቆሻሻ እና ተረፈ ምርትን መላልሶ የመጠቀም ዕድል በኢትዮጵያ

This browser does not support the audio element.

ጀርመናዊው ሉካስ ዱር ሰኞ ማለዳ አዲስ አበባ ሲደርሱ ከኩባንያቸው ጋር ተባብሮ የሚሰራ አጋር ማግኘት ቀዳሚ ሐሳባቸው ነበር። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የተጓዙት ሉካስ የሚመሩት ኩባንያ መቀመጫውን በጀርመን ኔደር ሳክሰን ግዛት ከብሬመን አቅራቢያ በምትገኝ አነስተኛ ከተማ ያደረገ ሲሆን ተረፈ ምርት ወይም ቆሻሻ መሰብሰቢያ መኪኖችን የሚያመርት ነው። ፋውን ኤክስፖቴክ የተባለው ይኸው ኩባንያ ከ20 ዓመታት በፊት ጀምሮ የቆሻሻ መሰብሰቢያ እና መዳመጫ ተሽከርካሪዎችን ወደ ኢትዮጵያ ቢልክም ሉካስ ዱር እንደሚሉት አሁን ግን በምሥራቅ አፍሪካዊቱ አገር አዲስ ሸሪኮች ይፈልጋል።

"ከዚህ በፊት ለተሽከርካሪዎቻችን ጥገና የሚያደርግ አጋር ነበረን። ይሁንና በዓለም አቀፉ ሁኔታ ምክንያት ከስሯል" የሚሉት ሉካስ ዱር "ለምርቶቻችን እጅግ ጠቃሚው ነገር ለተሽከርካሪዎቻችን ተገቢውን የጥገና አገልግሎት የሚሰጥ አጋር ማግኘት ነው። በመሆኑም ኩባንያችን ፋውን ለሽያጭ፣ ለጥገና እና ለስልጠና ሸሪክ ሊሆኑ የሚችሉ አጋሮች ለማግኘት ጥረት እያደረገ ይገኛል" ሲሉ ለዶይቼቬለ ተናግረዋል።

ሉካስ ዱር ከኢትዮጵያ ኩባንያዎች ሽርክና ለማበጀት ማክሰኞ መስከረም 10 ቀን 2015 በአዲስ አበባ ስካይ ላይት ሆቴል በተካሔደ ውይይት ላይ ተሳትፈዋል። በእርግጥ ከጀርመን ወደ ኢትዮጵያ ተጉዘው በስብሰባው የተሳተፉት የፋውን ኤክስፖቴክ ተወካይ ብቻ አልነበሩም። የኢትዮጵያ የንግድ እና ቀጠናዊ ትሥሥር ሚኒስቴር እና የኢትዮጵያ የአካባቢ ጥበቃ ባለስልጣን ኃላፊዎች፣ የጀርመን ዓለም አቀፍ የልማት ትብብር (GIZ) የዘርፉ ባለሙያዎች ተገኝተው ንግግር ያሰሙበት ውይይት አስር የጀርመን ኩባንያዎች የተወከሉበት ነው። በጀርመን የኤኮኖሚ ጉዳዮች ሚኒስቴር ድጋፍ መድረኩን ያዘጋጁት የጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማኅበር (Afrika-Verein) እና መቀመጫውን በአዲስ አበባ ያደረገው ኢስት አፍሪካ ፓርትነርስ ኮንሰልቲንግ የተባሉ ሁለት ተቋማት ናቸው።

ጥቅም ላይ የዋለውን የውኃ ኮዳ በትንሹ በማድቀቅ ተመልሶ እንደሚሸጥ ያስረዱት እስጢፋኖስ "ቆሻሻ የምንለው ነገር ራሱን የቻለ ሸቀጥ ነው ማለት ነው" ሲሉ አብራርተዋል።  በእንግሊዘኛው "ሰርኩላር ኤኮኖሚ" እየተባለ የሚጠራው የምጣኔ ሐብት ሞዴል ቆሻሻ ተመልሶ ጥሬ ዕቃ ወይም የሌላ ምርት ግብዓት መሆን እንደሚገባው የሚያቀነቅን ነው።ምስል DW/Y. Geberegiabeher

በጀርመን አፍሪካ የቢዝነስ ማኅበር የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ማኔጀር አስማው ኒታሪ ለዶይቼ ቬለ ከአዲስ አበባ "ጀርመን ቆሻሻን ሰብስቦ መልሶ ጥቅም ላይ በማዋል ረገድ ግንባር ቀደም ነች። በሥራው ሥመ-ጥሩ የሆኑ እና አሁንም ሥማቸውን እየገነቡ የሚገኙ ኩባንያዎች ይገኛሉ። እነዚህ ኩባንያዎች ከዚህ ክብ ኤኮኖሚ ትርፍ እያገኙበት ነው። በኢትዮጵያ ግን ያን ያክል አልተራመደም" ሲሉ በሁለቱ አገሮች መካከል በዘርፉ ያለውን ልዩነት አስረድተዋል።  

"በአገሪቱ እንዴት የተሻለ መሥራት እንደሚችሉ መንገድ የሚፈልጉ 20 አካባቢ ኩባንያዎች አሉ። በዚህ ምክንያት የጀርመን ኩባንያዎች በኢትዮጵያ ምን መሥራት ይችላሉ የሚለውን ለመፈተሽ ወደ ኢትዮጵያ የመምጫ ትክክለኛው ጊዜ ነው የሚል ሐሳብ አደረብን" በማለት ስብሰባው የተዘጋጀበትን ገፊ ምክንያት አስማው ኒታሪ ተናግረዋል።

ይኸን ዓላማ ለማሳካት ወደ አዲስ አበባ የተጓዙት የጀርመን ኩባንያዎች ከኢትዮጵያ አቻዎቻቸው የሚወያዩባቸው መድረኮች ተመቻችትዋል። በቢሾፍቱ ቆሻሻ ሰብስቦ ጥቅም ላይ ለማዋል የተቋቋመ የግል ኩባንያ እና የረጲ ደረቅ ቆሻሻ ኃይል ማመንጫ ፕሮጀክትን የመሳሰሉ ቦታዎች በጉብኝት በመርሐ ግብር ከተካተቱ መካከል ናቸው።

ቆሻሻ እንደ ሸቀጥ?

ከ12 ዓመታት የጀርመን አገር ኑሮ በኋላ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰው በመዋዕለ-ንዋይ እና ቢዝነስ ዘርፎች የማማከር አገልግሎት የሚሰጠውን ኢስት አፍሪካ ፓርትነርስ ኮንሰልቲንግ የተባለ ድርጅት ያቋቋሙት አቶ እስጢፋኖስ ሳሙኤል ቆሻሻ ወይም ተረፈ ምርትን በየፈርጁ ለይቶ በመሰብሰብ መልሶ የመጠቀምን አሰራር በቅጡ ያውቁታል። ኩባንያቸው ከጀርመን አፍሪካ ቢዝነስ ማኅበር በመተባበር ያዘጋጀው የአዲስ አበባ ስብሰባ ስያሜም በእንግሊዘኛ "ሰርኩላር ኤኮኖሚ" ተብሎ በሚጠራው ዘርፍ ላይ ያተኮረ ነው።

በምዕራባውያኑ አገራት በተለይም በአውሮፓ በሰፊው ይቀነቀን የያዘው ይኸ አሰራር ቆሻሻን ወይም ተረፈ ምርትን ደግሞ ደጋግሞ መጠቀምን የሚያበረታታ ነው። አቶ እስጢፋኖስ እንደሚሉት "ቆሻሻን እንደ ሸቀጥ ማየት ይቻላል።"

በኢትዮጵያ ቆሻሻ እና ተረፈ ምርትን መልሶ ሥራ ላይ የማዋል ጥረት አዲስ ባይሆንም የሚገባውን ያክል የደረጀ አይደለም።ምስል DW/Y. G. Egziabher

ቆሻሻ "ተሰብስቦ ወደ ባዮ ጋዝ ይቀየራል፣ ተሰብስቦ ከብስባሽ ኃይል ለማመንጨት ሊያገለግል ይችላል። ፕላስቲክ ተሰብስቦ ወደ ውጪ ገበያ ይላካል" የሚሉት አቶ እስጢፋኖስ በኢትዮጵያ የታሸገ ውኃ የሚያመርቱ 120 ገደማ ኩባንያዎች ለሥራቸው የሚያሻቸውን ማሸጊያ ፕላስቲክ ከውጪ ገበያ እንደሚሸምቱ ጠቅሰው በማሳያነት አንስተዋል።

ጥቅም ላይ የዋለውን የውኃ ኮዳ በትንሹ በማድቀቅ ተመልሶ እንደሚሸጥ ያስረዱት እስጢፋኖስ "ቆሻሻ የምንለው ነገር ራሱን የቻለ ሸቀጥ ነው ማለት ነው" ሲሉ አብራርተዋል።  በእንግሊዘኛው "ሰርኩላር ኤኮኖሚ" እየተባለ የሚጠራው የምጣኔ ሐብት ሞዴል ቆሻሻ ተመልሶ ጥሬ ዕቃ ወይም የሌላ ምርት ግብዓት መሆን እንደሚገባው የሚያቀነቅን ነው። "የተጣለው ቆሻሻ ተመልሶ አዲስ ግብዓት ይሆናል። ካርቶን፣ ወረቀት እና ጋዜጣ ለምሳሌ ተመልሶ ደብተር፣ ጋዜጣ እና ሶፍት ሊሆን ይችላል" ይላሉ አቶ እስጢፋኖስ። ይኸ ሞዴል በተለይ የአውሮፓ ኮሚሽን በሰፊው ተግባራዊ እንዲሆን ግፊት የሚያደርግበት ነው።

ተረፈ ምርት እና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን የሚያቀነቅነው የምጣኔ ሐብት ሞዴል የከባቢ አየር ለውጥ፣ የሥርዓተ ምኅዳር ውድመት፣ የቆሻሻ ክምችት እና ብክለትን ለመቋቋም መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል። በኢትዮጵያ ቆሻሻ እና ተረፈ ምርትን መልሶ ሥራ ላይ የማዋል ጥረት አዲስ ባይሆንም የሚገባውን ያክል የደረጀ አይደለም። በዚህ ረገድ የጀርመንን ተሞክሮ ከኢትዮጵያ ጋር ማነጻጸር ሉካስ ዱር እንደሚሉት "ፍትኃዊ አይደለም።"  "በጀርመን ቆሻሻ የሚለየው ከመሠረቱ ነው። በዚያ ላይ ቢያንስ ሶስት የቆሻሻ ማጠራቀሚያዎች አሉ። አንዱ ለወረቀት፣ ሁለተኛው ለተፈጥሯዊ ብስባሽ ሶስተኛው ለፕላስቲክ ናቸው። ይኸ በዚህ በአፍሪካ የለም። ሁሉም በአንድ ይጠራቀማል። ይኸ ትልቅ ፈተና ነው። ሌላው ትልቅ ፈተና የፕላስቲክ ጠርሙሶች አሰባሰብ ነው" የሚሉት ዱር "የጀርመን ኩባንያዎች የአገራቸውን ልምድ ወደ ኢትዮጵያ ከተሞች በማምጣት እነዚህን የፕላስቲክ ጠርሙሶች ምን ማድረግ እንደሚቻል ማሰልጠን እና ማስተማር ይችላሉ" በማለት ተናግረዋል።

እጅ ከምን?

በጀርመን አፍሪካ የቢዝነስ ማኅበር የምሥራቅ አፍሪካ ከፍተኛ ማኔጀር አስማው ኒታሪ ከኢትዮጵያ መንግሥት እና ጥቂትም ቢሆኑ ከዘርፉ ኩባንያዎች ዘንድ ቆሻሻን መልሶ በአግባቡ ለመጠቀም ከፍ ያለ ፍላጎት መኖሩን ታዝበዋል። ኒታሪ አማራጭ ገበያ ፈልገው ወደ ኢትዮጵያ ማማተር የያዙት የጀርመን ኩባንያዎች በእውቀት፣ ክህሎት እና ቴክኖሎጂ ሽግግር ረገድ ላቅ ያለ ሚና መጫወት እንደሚችሉ እምነታቸው ነው።

ተረፈ ምርት እና ቆሻሻን መልሶ ጥቅም ላይ ማዋልን የሚያቀነቅነው የምጣኔ ሐብት ሞዴል የከባቢ አየር ለውጥ፣ የሥርዓተ ምኅዳር ውድመት፣ የቆሻሻ ክምችት እና ብክለትን ለመቋቋም መፍትሔ ይሆናል ተብሎ ታምኖበታል።ምስል Hauke-Christian Dittrich/dpa/picture alliance

"የጀርመን ኩባንያዎች የኢትዮጵያን ገበያ መለማመድ ቢኖርባቸውም ቴክኖሎጂው አላቸው። ከሽያጭ በኋላ ለደንበኞቻቸው ሥልጠና መስጠት ይችላሉ" ሲሉ የተናገሩት አስማው ኒታሪ ወደ ፊት "የኢትዮጵያን ልዑካን ወደ ጀርመን በመውሰድ ሥራው እንዴት እንደሚከናወን የበለጠ እንዲማሩ የማድረግ ሐሳብ ጭምር አለን" በማለት ተናግረዋል።

የኢስት አፍሪካ ፓርትነርስ ኮንሰልቲንግ መሥራች እስጢፋኖስ ሳሙኤል ኢትዮጵያ ለዘርፉ የሚሆን ፖሊሲ እና ሕግጋት ለማበጀት በሒደት ላይ እንደምትገኝ ታዝበዋል። የአዲስ አበባው ውይይት "ቆሻሻን ደጋግሞ ደጋግሞ ደጋግሞ የመጠቀም ፍላጎት በሰፊው እንዳለ" ማሳየቱን  የገለጹት አቶ እስጢፋኖስ በሚቀጥሉት ሁለት እና ሶስት ዓመታት ጠለቅ ያለ ግንዛቤ መፍጠር እንደሚያሻ አስረድተዋል።

ሸሪክ ፈልገው ወደ አዲስ አበባ ብቅ ያሉት ሉካስ ዱር ኢትዮጵያ ዘርፉን ለማሳደግ ዝግጁ በመሆኗ ይስማማሉ። ነገር ግን "የግል ኩባንያዎች እነዚህን መሣሪያዎች የሚገዙበት የገንዘብ አቅም የላቸውም። መንግሥት ቴክኖሎጂውን ሥራ ላይ በማዋል ዘርፉን ወደሚቀጥለው ደረጃ የማሸጋገር ዝግጁነት ቢኖረውም ክፍያውን ማን ይከፍላል? ትልቁ ጥያቄ ይኸ ነው" የሚል አቋም አላቸው። የጀርመን ኩባንያዎች በጀርመን መንግሥት በኩል የተወሰነውን ወጪ መሸፈን የሚችሉበት ዕድል መኖሩን የጠቆሙት ሉካስ ዱር "ይኸ ግን ዘርፉን ወደሚቀጥለው ደረጃ ለማሸጋገር ከሚያስፈልገው አኳያ እጅግ በጣም ጥቂቱን ብቻ የሚሸፍን ነው" ብለዋል።

ይኸ የግል ኩባንያዎች የአቅም ውስንነት ጉዳይ አቶ እስጢፋኖስ ለዶይቼ ቬለ እንደተናገሩት በአዲስ አበባው ውይይት ከተመከረባቸው መካከል አንዱ ነው። ለዚህ የጀርመን መንግሥት የወጪ ንግድን ለማበረታታት የዘረጋው ሥርዓት አንድ መላ ሊሆን እንደሚችል አቶ እስጢፋኖስ ገልጸዋል። ይኸ የአውሮፓዊቱ አገር አነስተኛ እና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በአዳጊ ገበያዎች ለሚያከናውኑት የንግድ ሥራ ዋስትና የሚሰጥ የሔርሜስ ሽፋን የተባለ ሥርዓት ነው። በዚህ አሰራር አቶ እስጢፋኖስ እንደሚሉት "ለገዢው አካል ሻጩ ከጀርመን መንግሥት ጋር ተወያይቶ በሰባት እና ስምንት ዓመታት እንዲከፈል ሥምምነት ማበጀት ይቻላል።" ከዚህ በተጨማሪ በኢትዮጵያ ተሽከርካሪ የሚገጣጥሙ ኩባንያዎች ሉካስ ዱር የሚመሩት ፋውን ኤክስፖቴክን የመሳሰሉ የዘርፉ ተቋማት ከሚያመርቷቸው ማሽኖች በማቀናጀት መፍትሔ ማበጀት እንደሚቻልም አቶ እስጢፋኖስ ጠቁመዋል።

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW