1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

የህወሓት ልዩነት የፕሪቶሪያን ሥምምነት “ባለቤት አልባ” ሊያደርግ እንደሚችል ጌታቸው ተናገሩ

እሑድ፣ ነሐሴ 12 2016

የትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው ልዩነት የፕሪቶርያውን ሥምምነት “ባለቤት አልባ” ሊያደርግ እንደሚችል ተናገሩ። ልዩነቱን “አስጊ” ያሉት አቶ ጌታቸው “ጠላቶች” ብለው የገለጿቸው ኃይሎች ሊጠቀሙበት እንደሚችሉ ሥጋታቸውን ገልጸዋል።

የህወሓት አንድ ክንፍ ስብሰባ
በዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚመራው የህወሓት ክንፍ የሚያካሒደውን ጠቅላላ ጉባኤ የማይሳተፉ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት፣ የቁጥጥር ኮሚሽን አባላት፣ የዞን እና ወረዳ አመራሮች በትግራይ ምክር ቤት አደራሽ የራሳቸውን ስብሰባ አካሒደዋል። ምስል Million Haileselasie/DW

ለሁለት የተከፈሉት የህወሓት አመራሮች በየፊናቸው ዛሬ እሁድ ስብሰባ ላይ ናቸው

This browser does not support the audio element.

ለሁለት ተከፍሎ በመወዛገብ ላይ ያለው ህወሓት፥ ዛሬ እሁድ በአንድ ኪሎ ሜትር ልዩነት በሚገኙ ሁለት አዳራሾች፥ በተለያዩ ስብሰባ ላይ ውሏል። ካለፈው ማክሰኞ ጀምሮ እነ ዶክተር ደብረፅዮን ገብረሚካኤል የሚገኙበት ቡድን በሐወልቲ ሰማእታት አደራሽ ጠቅላላ ጉባኤ ላይ ያለ ሲሆን፥ እነ አቶ ጌታቸው ረዳ ያሉበት ሌላኛው ቡድን ደግሞ በትግራይ ምክርቤት አደራሽ 'የህወሓት ወቅታዊ ሁኔታ ላይ ማእከል ያደረገ' የተባለ ስብሰባ ሲያደርጉ ውለዋል።

በዚሁ መድረክ የህወሓት ቁጥጥር ኮምሽን አባላት፣ ከጉባኤው ራሳቸው ያገለሉ የህወሓት ማእከላይ ኮሚቴ አባላት፣ የዞን እና ወረዳ አመራሮች ጨምሮ በርካታ የፓርቲው አባላት የተገኙበት ሲሆን፥ ተሰብሳቢዎቹ 'በህወሓት ስም እየተካሄደ ነው' ብለው የገለፁት ጉባኤ አውግዘውታል።

አወዛጋቢው የህወሓት ጉባኤ ያሳለፈው ውሳኔ

የትግራይ ግዚያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት እና የህወሓት ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ፥ በስብሰባው ረዥም ንግግር ያደረጉ ሲሆን በህወሓት ከፍተኛ አመራር መካከል ያለ ልዩነት "ጉባኤ ይደረግ አይደረግ" የሚል ሳይሆን፥ እንዴት ይደረግ የሚል መሆኑ አብራርተዋል።

በትግራይ ምክር ቤት አዳራሽ በተካሔደው ስብሰባ የክልሉ ጊዜያዊ አስተዳደር ፕሬዝደንት ጌታቸው ረዳ በህወሓት አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል በፕሪቶሪያ የተፈረመውን ግጭት የማቆም ሥምምነት ባለቤት አልባ ሊያደርግ እንደሚችል ተናግረዋል። ምስል Million Haileselasie/DW

የህወሓት እውቅና ጉዳይ ከፌደራል መንግስት ጋር በሚደረግ ፖለቲካዊ ውይይት መፍትሔ እንዲገኝለት ሁሉም ተግባብቶ እያለ፥ የተወሰኑ ግለሰቦች በጎን በመንቀሳቀስ ወደ የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድ ወረቀት በማስገባት ከመግባባቱ ያፈነገጠ ስራ ከውነዋል በማለት ሌላው የህወሓት ቡድን አመራሮችን ተችተዋል።

ከዚህ በተጨማሪ ህወሓት ውስጥ በተፈጠረ አለመግባባት እና ክፍፍል፥ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ባለቤት አልባ እንዳይሆን ስጋት መኖሩ ያነሱት አቶ ጌታቸው ረዳ ይህ አደጋ ለመቀልበስ ጥረት እንደሚደረግ ተናግረዋል።

አራተኛ ቀኑን የያዘው የሕወሓት ጉባኤ እና የተቃዋሚዎች መግለጫ

አቶ ጌታቸው "ይህ የፕሪቶርያ የሰላም ስምምነት ሂደት ባለቤት አልባ ሊያደርግ የሚችል መሆኑ መረዳት ያስፈልጋል። ይህ ጉባኤ የፌደራል መንግስት አልተቀበለውም። ፌደራል አለመቀበሉ የራሱ ትርጉም አለው። ዋናው ነገር ግን በፓርቲያችን ውስጥ አንድነት እና መቀራረብ፣ በሐሳቦች ዙርያ አብሮ መስራት ሳይሆን መከፋፈል እና መራራቅ የሚያስከትል አደገኛ መድረክ ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው። ይህም ፕሪቶሪያ ያለባለቤት የሚቀርበት ዕድል የሚፈጥር ነው" ብለዋል።

በዝግ ስብሰባ የቀጠለው የህወሓት ጠቅላላ ጉባኤ

ከዚህ በተጨማሪ ህወሓት ውስጥ የተፈጠረው ልዩነት አስጊ እና 'ጠላቶች' ብለው የገለጿቸው ኃይሎች ሊጠቀሙበት የሚችሉ ሲሉ አቶ ጌታቸው ረዳ ተናግረዋል። ይህ በእንዲህ እንዳለ ትላንት ለክልሉ መገናኛ ብዙሐን ማብራርያ በሰጡት ጊዜ፥ የህወሓቱ ምክትል ሊቀመንበር አቶ ጌታቸው ረዳ አሁን ላይ ጉባኤ በማድረግ ላይ ያለ የህወሓት ቡድን ማንነቱ ካልታወቀ የውጭ ኃይል ጋር ግንኙነት ሊኖረው እንደሚችል ጠቁመው ነበር።

የተቃዋሚ ፖለቲካ ፓርቲ አመራሮች እና የሲቪክ ማኅበረሰብ ተወካዮች በህወሓት ከፍተኛ አመራሮች መካከል የተፈጠረው መከፋፈል በሰላማዊ መንገድ እንዲፈታ ጥሪ ሲያደርጉ ቆይተዋል። ምስል Million Haileselasie/DW

አቶ ጌታቸው "የህዝብ የሰላም ፍላጎት ወደጎን በመተው፣ ለግዜው ማን መሆኑ በግልፅ ከማይታወቅ እና እነሱ ደጀን ይሆነናል ያሉት የውጭ ኃይል ተማምነህ፥ ያለ የሆነ ዝግጅት፣ የተወሰነ ግለሰቦች ጠባብ ፍላጎት ሲባል የትግራይ ህዝብን ዳግም ወደ አደጋ ለመዳረግ የሚደረግ እንቅሰቃሴ ነው እየተካሄደ ያለው" ሲሉ ተናግረዋል።

የህወሓት 14ኛ ጠቅላላ ጉባኤ ቃል አቀባይ አቶ አማኑኤል አሰፋ ግን “ይኸ አገላለጽ ትክክል አይደለም” ሲሉ አቶ ጌታቸው ያቀረቡትን ክስ አስተባብለዋል። “ህወሓት እምነቱ በትግራይ ሕዝብ፣ በፕሪቶሪያው የሰላም ሥምምነት በተቋማዊ አሰራር ነው” ያሉት አቶ አማኑኤል “ሁሉም ችግሮች በሰላማዊ ፖለቲካዊ መንገድ ይፈታሉ ብለን ነው የምናምነው” ሲሉ ተናግረዋል። 

ይህ በእንዲህ እንዳለ በ14ተኛ ጉባኤ ላይ ያለው ህወሓት፥ በፓርቲው ስም ፖለቲካዊ እንቅስቃሴ እንዳያደርጉ በማለት የቆየው ማእከላይ ኮሚቴ እና የህወሓት ማእከላዊ ቁጥጥር ኮምሽን ማገዱ ትላንት ማስታወቁ ይታወሳል።

ሚሊዮን ኃይለሥላሴ

እሸቴ በቀለ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW