1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ውዝግቦችኢትዮጵያ

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በታጣቂዎች ጥቃት 13 ሰዎች ሕይወት አለፈ

ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 3 2016

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ተናገሩ። ጆጅ በተባለ ቦታ በተፈጸመው ጥቃት ተጨማሪ አራት ሰዎች ቆስለዋል። ጥቃቱ የተፈጸመው እህል ለመጫን ጉዞ ላይ በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ነው።

Infografik GRAPHIC Karte Amuru Woreda, Äthiopien
ምስል DW

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በታጣቂዎች ጥቃት 13 ሰዎች ህይወት አለፈ

This browser does not support the audio element.

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በትናንትናው ዕለት ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት 13 ሰዎች ሕይወት ማለፉን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። ጆጅ በተባለ በአንድ ገጠራማ ቀበሌ ውስጥ ወደ ቡሬ ወረዳ በቆ ጣቦ በተባለ ስፍራ እህል ለመጫን በመኪና እየተንቀሳቀሱ ባሉበት ወቅት ጠዋት12፡00 ገደማ ላይ ጥቃቱ መፈጸሙን ነዋሪዎች አመልክተዋል።

ጥቃቱ የደረሰበት የጆጅ ቀበሌ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሲሳይ አበዋ በጥቃቱ 13 ሰዎች ህይወት ማለፉን አረጋግጠዋል። ጽንፈኛ ያሏቸው ሐይሎች ጥቃቱን ማድረሳቸውን ገልጸዋል። በአሙሩ ወረዳ ውስጥ ለረጅም ጊዜ በነበረው የሰላም መደፍረስ ምክንያት 49ሺ የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለው እንደሚገኙ ተገልጿል

በአሙሩ የታጣቂዎች ጥቃት መቀጠሉ

የታጣቂዎች እንቅስቃሴ በስፋት የሚስተዋልባት የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በተደጋጋሚ የታጣቂዎች ጥቃት ሰለባ ሆናለች። በዚሁ ጥቃት ሰበብ በወረዳዋ 10 ከሚደርሱ ቀበሌዎች ውስጥ የተፈናቀሉ ዜጎች በከተማ አካባቢ ተጠልለው ይገኛሉ።

በትናንትናው ዕለትም በአሙሩ ወረዳ ጆጅ በሚትባል ቀበሌ ውስጥ እህል ለመጫን ወደ ቡሬ ወረዳ በቆጣቦ የተባለ ቦታ እያቀና በነበረ ተሽከርካሪ ላይ ጥቃት መፈጸሙንና በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሱን ከስፋራው ለማወቅ ተችሏል፡፡ ጥቃቱ የተፈጸመበት ስፍራ ጆጅ ቀበሌ ነዋሪ የሆኑት አቶ ሐሰን መሀመድ ጥቃቱ ጠዋት 12፡00 ሰዓት ገደማ በደፍጣ የተፈጸመ መሆኑን ገልጸዋል።

በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ በተፈጸመ ጥቃት 13 ሰዎች መገደላቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለሥልጣናት ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። ምስል Amanuel Sileshi/AFP/Getty Images

 

“ጆጅ በሚባል ቦታ ትናንት  ወደ  ጫቦና በቆ ጣቦ እየሄደ ባለበት ሰዓት ጠዋት ላይ ነው ጥቃቱ የተፈጸመው፡፡ መኪናው ከአሙሩ እና ቡሬ ወረዳ በቆ ጣቦና ጫቦ የሚባሉ ቦታዎች መካከል በተለያዩ ጊዜ እየተንሰቀሳቀሰ እህል ይጭን ነበር” ያሉት አቶ ሐሰን መሀመድ “አሽከርካሪውን እና የመንገድ ሠራተኞችን ጨምሮ 13 ሰዎች ህይወት አልፈዋል” ሲሉ አስረድተዋል።

በአሙሩ ወረዳ ውስጥ በትናንትናው ዕለት በታጣቂዎች በደረሰው ጥቃት የተጎዱ ሁለት ሰዎች የህክምና ዕርዳታ እየተሰጣቸው እንደሚገኝ የነገሩን ሌላው የአካባቢው ነዋሪ በአካባቢው የሚንቀሳሰቀሱ ታጣቂዎች በስፍራው ከተሰማራ የሚሊሻ ሀይሎች አቅም በላይ መሆኑን አክለዋል።

 በወረዳው 49ሺ በላይ ሰዎች በሰላም እጦት ተፈናቅለዋል

የጆጅ ቀበሌ ስራ አስኪያጅ የሆኑት አቶ ሲሳይ አበዋ በትናንትናው ዕለት በቀበሌው 17 ሰዎችን ጭነው ወደ ቡሬ ይጓዝ በነበረው መኪና ላይ በደረሰው ጥቃት የሰው ህይወት ማለፉን ተናግረዋል፡፡ በአካባቢው ጽንፈኛ ያሏቸው ሐይሎች ባልታጠቁ ሰዎች ላይ ጉዳት ማድረሳቸውን ገልጸው በህዳር ወር መጀመሪያም በአሙሩ እና ቡሬ ወረዳ አዋሳኝ ስፍራዎች ላይ በሚገኙ ስፍራዎች በደረሰው ጥቃት 3815 ሰዎች ተፈናቅለው በቀበሌው እንደሚገኙ ገልጸዋል።

በሆሮ ጉዱሩ ዞን በተደጋጋሚ በተፈጸሙ ጥቃቶች በሺሕዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ተፈናቅለዋልምስል Seyoum Getu/DW

“በመኪናው ላይ ተሳፍረው ከነበሩት 17 ሰዎች መካከል 13ቱ ህይወታቸው ሲያልፍ 4ቱ ቆስሏል” ያሉት አቶ ሲሳይ “ቦታው በሚሊሻ እየተጠበቀ የሚገኝ ሲሆን ተደብቀው በደፈጣ ነው በመትረየስና ብሬን  እህል ለመሰብስብና ለመጫን እየተንቀሳቀሱ ያሉ ሰላማዊ ሰዎች ላይ ጥቃት ፈጽመው የሸሹት” በማለት ገልጸዋል።  

ከሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አስተዳዳሪ ተጨማሪ መረጃዎች ለማግኘት ዶይቼ ቬለ ጥረት ቢያደርግም ሲሆን ምላሽ ለመስጠት   ፈቃደኛ ባለመሆናቸው ሀሳባቸውን ማካተት አልተቻለም።  ከአሙሩ ወረዳው ገጠራማ ቦታ በሰላም እጦት 45,500 የሚደርሱ ሰዎች ተፈናቅለው ወደ ከተማ ተጠግቶ የሚኖሩ ሲሆን 3815 የሚሆኑት ደግሞ በህዳር 2016 ዓ.ም ከቡሬ ወረዳ ጋር በሚያዋስኑ ቀበሌዎች የተፈናቀሉ ሰዎች እንዳሉ የወረዳው አስተዳደር መረጃ ያመለክታል።

ነጋሳ ደሳለኝ

እሸቴ በቀለ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW