በሆሮ ጉዱሩ የኦነሰ ታጣቂዎች
ሰኞ፣ መስከረም 19 2018
ትናንት እሁድ በኦሮሚያ ክልል ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በተለያዩ ወረዳዎች አከባቢው ላይ ስንቀሳቀሱ የነበሩ በርካታ የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት ታጣቂዎች ወደ ሰላም ተመልሰዋል ሲል ዞኑ አስታወቀ፡፡
ዞኑ በርካታ ታጠቂዎች የያዙትን ትጥቅ መልሰው ስገቡ ካሳየበት ምስል ጋር ባጋራው መረጃ፤ ትጥቃቸውን አስቀምጠው ተመለሱ ያሏቸውን ታጣቂዎች በሻንቡ ከተማ ተቀብለዋል፡፡ እንደ ዙኑ መንግስት መግለጫ በትናንትናው እለት ከጃርደጋጃርቴ ወረዳ ብቻ 57 የቡድኑ ታጣቂዎች የትጥቅ ትግሉን በማቆም ወደ ሰላም ተመልሰዋል፡፡
የዞኑ ዋና ከተማ ሻምቡ በፊናው በኮሚዩኒኬሽን ጽህፈት ቤቱ በኩል እንዳሳወቀው፤ በጃል ያደሳ የሚመሩ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ወደ ሰላም ስመለሱ በሻምቡ ማህበረሰቡ አቀባበል አድርገውላቸዋል፡፡ ይህ መግለጫ የተመለሱት ታጣቂዎቹ ምን ያህል እንደሆነና የትአከባቢ ስንቀሳቀሱ እንደነበር ግን ያለው ነገር የለም፡፡
የመንግስት አስተያየት
በዚህ ላይ አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡ የኦሮሚያ ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ኃይሉ አዱኛ ታጣቂዎቹ እየተመለሱ የሚገኙት መንግስት እና የአገር ሽማግሌዎች ያቀረቡላቸውን ጥሪ ተከትለው ነው ብለዋል፡፡
“ባለፈው ዓመት መንግስት ያቀረበውን የሰላም ጥሪ ተከትሎ በነጃል ሰኚ የሚመራው ቡድን ወደ ሰላማዊ መንገድ ገብተዋው መንግስት የተሃድሶ ስልጠና በመስጠት የማቋቋም ስራ ሰርቷል፡፡ በጉጂም እንዲሁ የቡድኑ አባላት አባላትን ወደ ሰላም መመለስ ተችሏል፡፡ በተመሳሳይ ሁኔታ በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ የምንቀሳቀሱም ሰላማዊ ጥሪውን ተከትለው መግባት ችለዋል” በማለት ተመሳሳይ ሁኔታዎች በሁሉም የክልሉ ዞኖች ሊያስብል በሚችል ደረጃ ተመሳሳይ ሁኔታዎች ይታያሉም ነው ያሉት፡፡
ሰላም ያመጽናት ስልቱስ?
በነዚህ አከባቢዎች ሰላም በዘላቂነት ጸንቷልን የተባሉት አቶ ኃይሉ፤ “ሰላም መስፈን ማለት ተነጻጻሪ ነው” ያሉት አቶ ኃይሉ የታጣቂ ቡድኑ አባላት ይነስም ብዛ በገቡ ቁጥር ሰላም እየተረጋገጠ እንደሚሄድ ያለውን ተስፋ አስረድተዋል፡፡ “አሁንም እዚህም እዛም ችግሮች የሉም ማለት አይቻልም” ያሉት አቶ ኃይሉ መንግስት በዘለቄታዊ ሰላም ላ ግን እየሰራ እንደሆነ አመልክተዋል፡፡ “መንግስት በግጭት አዙሪት ውስጥ የመቆየት ፍላጎትና ግጭትን በኃይል አማራች ብቻ የመፍታትም ፍላጎት የለውም” በማለትም በሰላም አማራጩ ላይ መንግስታቸው ቁርጠኛ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡
የኦነግ-ኦነሰ ምላሽ
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) አዛዥ አማካሪ የሆኑት አቶ ጅሬኛ ጉደታ በዚሁ የትጥቅ ትግል አቋርጠው ወደ ሰላም እየተመለሱ ነው ስለተባለው ጉዳይ በዶይቼ ቬለ ተጠይቀው ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አቶ ጅሬኛ በምላሻቸው፤ “በስነምግባር ጉድለት ከድርጅቱ ከወጡ ሰዎች ጋር መንግስት እየሰራ ፕሮፓጋንዳ ይሰራል” በማለት ወደ ሰላም እየተመለሱ ነው የተባሉትን የቡድኑ ታጣቂዎች “ዓላማቸውን የረሱ” በማለትም ከሰው ሰራዊቱ ለኦሮሞ ነጻነት ትግል መስራቱን ቀትለዋል በማለት ማስተባበሪያ ሰትተዋል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ሰራዊት (ኦነግ-ኦነሰ) እና የኢትዮጵያ መንግስት ከዚህ በፊት በታንዛንያ ያደረጉት የዘላቂ ሰላም ስምምነት ጥረቶች ሳይሳካ መክሸፉ አይዘነጋም፡፡
ሥዩም ጌቱ
እሸቴ በቀለ
ነጋሽ መሐመድ