1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል
ፖለቲካየመካከለኛው ምሥራቅ

ሊባኖስ «ካለፉት ሳምንታት ሲነፃፀር የተረጋጋ ነው»፤ ኢትዮጵያውያን

ልደት አበበ
ዓርብ፣ ነሐሴ 10 2016

የመካከለኛው ምስራቅ ቀውስ ወደ ለየለት ጦርነት ይገባል የሚለው ስጋት አሁንም አለ። እንደሚታወቀው ደግሞ በሊባኖስ በብዙ ሺ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ። ዶይቸ ቬለ እዛ ያሉ ኢትዮጵያውያን በምን ሁኔታ ላይ እንደሚገኙ ጠይቆ ነበር። ከዚያ በኋላ ምን አዲስ ነገር አለ?

በቤይሩት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ ሰዎች ከሊባኖስ ለመውጣት ሲሞክሩ
እጎአ ነሐሴ 9 ቀን 2024 በቤይሩት ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ እስራኤል የሂዝቦላህን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ከገደለች በኋላ ጦርነት ይፈጠራል በሚል ስጋት ሰዎች ከሊባኖስ ለመውጣት ሲሞክሩምስል AFP/Getty Images

ሊባኖስ የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን

This browser does not support the audio element.

እሥራኤል ኢራን ውስጥ አንድ የሀማስን ከፍተኛ መሪ እና  በኢራን የሚደገፈውን የሊባኖስ ሂዝቦላህ ታጣቂ ቡድን መስራቾች አንዱን ሊባኖስ ውስጥ ከገደለች በኋላ በእሥራኤል ላይ ከየአቅጣጫው ዛቻዎች  ተሰምተዋል።  ይህ በተለይም በመካከለኛ ምስራቅ በሚኖሩ ሰዎች ዘንድ ከፍተኛ ስጋት ፈጥሯል።   

ባለፈው ሳምንት የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች ሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩት ድረስ ዘልቀው ዝቅ ብለው ሲበሩ ተሰምቷል።  እስራኤል ከኢራን እና አጋሮቿ ሊደርስ ይችላል ያለችውን የበቀል ርምጃ ለመከላከል በዝግጅት ላይ ሳለች የውጭ በተለይም የምዕራብዊ ሀገራት ዜጎቻቸው ሊባኖስን ለቀው እንዲወጡ ይበልጥ አሳስበዋል። በሌላ በኩል ደግሞ የተፈጠረውን ውጥረት ፈርተው አንዳንድ አየር መንገዶች በረራ በማቋረጣቸው የቤይሩት አውሮፕላን ማረፊያ በሰዎች ተጨናንቆ ነው የሰነበተው።  የተሰጋው አለመከሰቱ በሊባኖስ ለሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ትንሽ እፎይታ እና  ለከፋ ቀን እንዲዘጋጁ እድል ሰጥቷቸዋል።  ቤይሩት የምትኖረው ሰላማዊት ተስፋዬ ወይም ብዙዎች በሚያውቋት መጠሪያ ሰላም ፍካት ኢትዮጵያውያን ስላሉበት ሁኔታ ገልፃልናለች። ወጣቷ የፍካት ለኢትዮጵያ ማህበር አባል እንደመሆኗ ከበርካታ ኢትዮጵያውያን ጋር ግንኙነት አላት። ቤይሩት ከሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንስላ ጋርም መረጃ ትለዋወጣለች።  « ካባለፉት ሳምንት ጋር ሲነፃፀር የተረጋጋ ነው። ወደ ደቡብ ክልል አካባቢ ነው ስጋት ያለው። በወሬም ደረጃ ሰከን ብሏል።  ባለፉት ሳምንታት የጀት ድምፆች ነበሩ። አሁን ግን ረገብ ብሏል ፣ ድምፅ የለም። ጦርነቱ የተቆረጠበት ቀንንም አልፈነዋል፤ እስካሁን ምንም ነገር የለም።»  ስትል ወቅታዊውን ሁኔታ ትገልፃለች።

ጦርነት ቢጀመር ምን ታቅዷል?

«መረጃ የምንለዋወጥበት ሚዲያዎች አሉ» የምትለው ሰላማዊት በአሁኑ ሰዓት በርካታ ሀሰተኛ መረጃ የሚያጋሩ ሰዎች መኖራቸውን እና ይህም እዛ ያሉትን ኢትዮጵያውያን እያስፈራራ እንደሆነ ነግራናለች።  ስለሆነም ሰው ቤት ተቀጥረው የሚሰሩ ኢትዮጵያውያን እዛው አርፈው እንዲቀመጡ ነው የምትመክረው። ለከፍተኛ ባለስልጣናት እንጂ የከፋ ነገር ቢገጥምለኢትዮጵያውያን ሰራተኞች ሀገሪቷን ለቆ መውጣት ከባድ ነው» የምትለው ሰላማዊት በአሁኑ ሰዓት ምን እየተደረገ እንደሆነ ስትናገር « ህዝቡን የማረጋጋት ስራ አለ።  ፅሕፈት ቤቱ አልተዘጋም ስራውን እየሰራ ነው። ሀገር ለቆ አልወጣም። ህዝቡን እየተቆጣጠረ ነው። እኛም ለምንጠይቃቸው ጥያቄዎች ሳይሰለቹ እየመለሱልን ነው። »

እስራኤል ቤሩት ውስጥ የሂዝቦላህን ከፍተኛ ወታደራዊ አዛዥ ከገደለች በኋላ ምስል AFP

የኢትዮጵያ መንግሥት ምን ይላል?

የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ነብዩ ተድላ በዚህ ሳምንት ሐሙስ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ በሊባኖስ ያለው ቀውስ እየተባባሰ ከሄደ በዚያ ያሉ ኢትዮጵያውያንን የሚታደግ ኮሚቴ ተዋቅሮ እንቅስቃሴ እየተደረገ መሆኑን መናገራቸውን የኢትዮጵያ ብሮድካስቲንግ ኮርፖሬሽን ዘግቧል። 
«ማቲ አቢሲኒያ» በሚል ቅፅል ስሜ ነው እዚህ ቤይሩት የምታወቀው ያለን ሌላው ኢትዮጵያዊ እሱ ባለበት አካባቢ እስካሁን ጦርነት ባይካሄድም የከፋ ቀን ቢመጣ ግን «ሊባኖስን በቀላሉ ጥለን መውጣት አንችልም» ይላል።  « በመጀመሪያ እዚህ ሀገር ኤምባሲ ሳይሆን ቆንስላ ነው ያለን።  የኢትዮጵያ መንግሥት ከዚህ ሊያወጣን ይችላል የሚል አቅም አለው ብዬ አላምንም። ቆንስላው ማስታወቂያ ወይም መረጃ አውጥቷል። ከዚህ መረጃ የዘለለ እንደዚህ እናደርግላችኋለን የሚል መረጃ አይሰጥም»

የአውሮፕላን ቲኬት ዋጋ መጨመር እና የበረራዎች መሰረዝ

ለማንኛውም ነገሮች እስከሚረጋጉ በሚል ወደ ሀገራቸው መመለስ የሚፈልጉ ኢትዮጵያዊያን ካሉ እንኳን ጠቀም ያለ ገንዘብ ያስፈልጋቸዋል። ማቲ እንደሚለው የኢትዮጵያ አየር መንገድ የበረራውን ዋጋ በእጥፍ ገደማ ጨምሯል። « ቲኬት ከ 900 ዶላር በላይ ገብቷል። በአሁኑ ሰዓት የሀገሩን ዜጋ ሙሉ በሙሉ ወጪውን ሸፍኖ ባይሆን እንኳን አግዞ ማስወጣት ይችላል። ነገር ግን የቲኬት ዋጋ ጨምሯል። በፊት የቲኬት ዋጋ ከደርሶመልስ ከ450 እስከ 480 ዶላር ነበር። እንደው ይህንን ከግምት ውስጥ ማስገባት ቢቻል መልካም ነበር። » በመካከለኛው ምስራቅ ከተፈጠረው ስጋት ጋር በተያያዘ በርካታ አየር መንገዶች አሁንም ድረስ በረራ እንዳቋረጡ ይገኛሉ።  አብዛኞቹ እስከሚመጣው ሳምንት መጀመሪያ ድረስ የሰረዙትን በረራ አራዝመዋል። 
ሊባኖስ ውስጥ የሚኖሩ ሕጋዊ የጉዞ ሰነድም ሆነ የስራ ፍቃድ የሌላቸው ኢትዮጵያውያን ቁጥር በውል ባይታወቅም እነሱን ማግኘቱ ችግር እንደማይሆን  ሰላማዊት ገልፃልናለች።  ከቆንስላውም ሰነድ አልባ ሰዎችን በሚመለከት ተስፋ ሰጪ ነገር አለ ባይ ናት።  « የተደራጁ ማህበሮች አሉ ። ከዚህ በፊት በኮሮና ጊዜም ብዙ ስራዎች ሲሰሩ ነበር። እንደዛ እንዲሆን ህዝቡን እያነሳሳን ነው። ወረቀትም ፣ ሰነድም ለሌላቸው ፅህፈት ቤቱ የራሱን ዝግጅት እያደረገ ነው። ጠይቀነዋል። ያንንም ምላሽ ሰጥቶናል። ዝም ብሎ እንዳልተቀመጠ ነው የተነገረን።»


የሊባኖስ ፍንዳታና ኢትዮጵያውያን

እንደ የፈረንሳይ ዜና ወኪል መረጃ እስከ ሐሙስ ድረስ በእስራኤል እና  በኢራን በሚደገፈው የሊባኖሱ ሂዝቦላህ ተዋጊዎች መካከል  በሚካሄደው ውጊያ ባለፉት 10 ወራት ውስጥ  570 የሚጠጉ ሰዎች ተገድለዋል። አብዛኞቹ የቡድኑ ተዋጊዎች ናቸው ቢባልም 118 ያህሉ ግን ንፁሀን ሰዎች እንደሆኑ ተገልጿል። ስለሆነም ሰዎች ከጦርነት አካባቢ እየተፈናቀሉ ወይም እየሸሹ ነው። በዚህም የተነሳ ሊባኖስ የሚኖሩ የውጭ ዜጎች ከጦርነት ባሻገር ምን አይነት ፈተና ሊገጥማቸው እንደሚችል ማቲ ገልፆልናል።

እጎአ ነሐሴ 6 ቀን 2024 ዓ.ም. እስራኤል ደቡባዊ ሊባኖስ ውስጥ የሰነዘረችው ጥቃትምስል Ramiz Dallah/Anadolu/picture alliance

 « እዛ በደቡብ አካባቢ የሚኖር ህዝብ ጦርነት በሚኖር ሰዓት ወደ እዚህ ነው ተገልብጦ የሚመጣው። በዚህ ጊዜ እዚህ ቤት የማስለቀቅ ሁኔታ ሊኖር ይችላል።  እዚህ ቤት ተከራይተን ስንኖር ዜጋው በጦርነት ምክንያት ተፈናቅሎ ቢመጣ እኛን ቢያስለቅቀን ለቀን ነው መውጣት የምንችለው።  እንደውም አንድ ጓደኛዬ የሚኖርበት አካባቢ ውጡ እያሉን ነው። ደቡብ አካባቢ ያሉ ዜጎቻችን ባለው ችግር ምክንያት ይመጣሉ ብለው እንዳሏቸው ነው ያጫወተኝ። »

ሰላማዊት እንደተናገረችው ወጣ ያሉ እና ጦርነቱ ይካሄድባቸዋል የተባሉ አካባቢዎች የሚኖሩ ኢትዮጵያውያንን ለማግኘት በማህበራት የተደራጁት ኢትዮጵያውያን በጋራ እየሰሩ ይገኛሉ። ምናልባት ይህንን ዝግጅት የሚከታተሉ እና የበለጠ መረጃ ማግኘት የሚፈልጉ በሊባኖስ ነዋሪ የሆኑ ኢትዮጵያውያን ይኖራሉ እና ሰላማዊትን የት ብለው ይፈልጋቹ ብለናታል። «ሰላም ሰላም» ወይም «ሰላም ፍካት» ብለው ወይም «ሰላም የአርሴማ ልጅ » በሚል ቲክ ቶክ ላይ ማታ ማታ ነገሮችን እያስረዳን ነው ያለነው ። ህዝብን ማረጋጋት ይዘናል። ከአሰሪዎቻቸው ጋር ግጭት እየፈጠሩ ያሉ ሰዎች ስላሉ ያንን ለማርገብ እየሰራን ነው።  እኛን  ማግኘት ካልተቻለ አዳዲስ ነገሮች ካሉ የፅሕፈት ቤቱ ገፅ ላይ መከታተል ይቻላል።» 

ልደት አበበ
ኂሩት መለሰ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW