1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሊባኖስ አመፅ መስፋፋቱ

ሰኞ፣ ጥቅምት 12 2005

በመኪና በተጠመደ ፈንጂ ከተገደሉት ከፍተኛ የደህንነት መስሪያ ቤት ባለስልጣን ዊሳም አል-ሃሳን የቀብር ስነ-ስርዓት በኋላ የሊባኖስ መዲና ቤሩት ግጭት ተስፋፍቶባታል። ትናንት ማምሻዉን ዛሬም እንዲሁ በተለያዩ አካባቢዎች ጥይት ጥቂት የማይባሉትን ዜጎች ህይወት አጥፍቷል።

GettyImages 154523267 A Lebanese supporter of the March 14 movement, which opposes the Syrian regime of President Bashar al-Assad, demonstrates waving his national flag, as other protesters tried to storm the governmental palace, after the funeral of top intelligence chief General Wissam al-Hassan and his bodyguard, in downtown Beirut, on October 21, 2012. Lebanese police fired in the air and used tear gas to repel protesters trying to storm the office of Lebanese Prime Minister Najib Mikati, amid calls for him to quit. AFP PHOTO / JOSEPH EID (Photo credit should read JOSEPH EID/AFP/Getty Images)
ምስል AFP/Getty Images

ከቤሩት የሚወጡ አንዳንድ ዘገባዎች አመፅ ግጭቱ የሃይማኖት ፅንፍ እንዳይዝ ስጋታቸዉን ያመለክታሉ። በሌላ በኩል ሟቹ የሊባኖስ ከፍተኛ የደህንነት ባለስልጣን ከሶርያ መንግስት ተቀናናቃኞች ቅርበት እንደነበራቸዉ ተገልጿል። የሊባኖስ መንግስት ግድያዉ በሶርያ ካለዉ የዕርስ በርስ ጦርነት ጋር ተያያዥነት እንዳለዉ ይጠረጥራል።

ተቃዋሚዎች ሊባኖስ ውስጥ የሶሪያ መንግስት ደጋፊዎችን ለመቃወም ሰልፍ ጠርተው ነበር። ያኔ ነበር ብጥብጡ ተጀመረ። አርብ ዕለት በመኪና ላይ በተጠመደ ፈንጂም ዊሳም አል-ሃሳን እና ሌሎች ሰባት ሰዎች ተገደሉ። በዚሁ ፍንዳታ 80 የሚሆኑም ቆሰሉ። ቦንቡ የሶሪያ ፕሬዚዳንት ባሽር አሳድን መንግስት ከሚቃወመው ፓርቲ ዋና ጽህፈት ቤት 200 ሜትር ርቀት ላይ ነዉ የፈነዳው። ለፍንዳታው እስካሁን ማንም ኃላፊነት አልወሰደም። የሊባኖስ አንዳንድ ባለስልጣናት በጥቃቱ የሶሪያ እጅ አለበት እያሉ ነዉ።

የዊሳም አል-ሃሳን የቀብር ስነ-ስርዓትምስል Reuters


በዊሳም አል-ሃሳን የቀብር ስነ-ስርዓት ላይ የተቆጡ ዜጎች ወደጠቅላይ ሚኒስትሩ ፅህፈት ቤት ለመግባት እንቅስቃሴ ጀመሩ። ፀጥታ አስከባሪዎች ርምጃዉን ለመግታትና ህዝቡን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ሲረጩ፤ ህዝቡ በፋንታዉ ድንጋይ እና ብረት ወረወረ። በደህነት ባለስልጣኑ መገደል ሃዘንና ብስጭቱን የገለፀዉ ህዝብ ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ ስልጣን እንዲለቁም ጠይቋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከሶሪያ መንግስት ጋ የጠበቀ ግንኙነት አላቸው ሲሉም ይወቅሳሉ።

የሊባኖሲያዊ ተቃዋሚ አስለቃሽ ጪስ ሲወረውርምስል AP


«በዊሳም አል-ሃሳን ሞት፣ ስለ ሀገራችን እና ስለ ራፊክ ሀሪሪ የተሰማንን ሀዘን እና ስቃይ መግለፅ እፈልጋለሁ። ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ ሳይዘገዩ ዛሬውኑ ስልጣን እንዲለቁ እንጠይቃለን። ሚካቲ አሁኑኑ እንዲለቁ እናሳስባለን።» ይላሉ አደባባይ ከወጡት አንዱ። የሀሳን የቅርብ ወዳጅ የነበሩት የቀድሞዉ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ራፊክ ሀሪሪም እኢአ በ2005 ዓ ም ልክ እንደ በተመሳሳይ አደጋ መገደላቸዉ ይታወሳል። በእሳቸዉ ህልፈተ ህይወትም ጎረቤት ሀገር ሶሪያ ተጠርጣሪ ናት። የሀሪሪ ግድያም የሶሪያ እና የሊባኖስ ግንኙነትን እንዳበላቸዉ ይነገራል። በዚህ የተነሳም ሶሪያ በሊባኖስ ለአስርተ አመታት የነበራትን ጦር ከሀገሪቱ ማስወጣት ነበረባት። በስለላ ተግባር የተሰማራዉ አካል ግን አሁንም ሊባኖስ ዉስጥ እንደሚንቀሳቀስ ተገልጿል።

በሊባኖስ የተነሳው አመፅ እንደ ሶሪያ እንዳይስፋፋ ይሰጋልምስል Reuters


በሺ የሚቆጠሩ ሊባኖሳውያን ተቃውሞ የሚያሰሙባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር ናጂብ ሚካቲ ስልጣን እንደሚለቁ አሳውቀው ነበር፤ ሆኖም የሀገሪቷ መሪ ይህንን ጥያቄ አላፀደቁትም። በዊሳም አል-ሃሳን የቀብር ስነ ስርዓት ላይ የተገኙት የሊባኖስ ፕሬዚዳንት ሚቼል ሱሌማን በበኩላቸዉ ወንጀለኞች ከለላ እንደማይሰጥ ነዉ በንግግራቸዉ ያመለከቱት፤
« ለፍትህ አካላት የማቀርበው ጥሪ ህዝቡ ከናንተ ጋ በመሆኑ እንዳትፈሩ ነው። የፀጥታ አስከባሪው ኃይልም የህዝቡ ድጋፍ ስላላችሁ በአቋማችሁ እንድትፀኑ ነው። ፖለቲከኞች፣ መንግስት እና የፖለቲካ ባለስልጣናት የወንጀል ርምጃዎችን እንዳትሸፋፍኑ ጥሪ አደርጋለሁ። ፖሊስ እና ዳኛ ደህንነቱ፤ ወንጀለኞች ደግሞ ከለላ እንደሌላቸዉ ይሰማቸዉ! ይህ የእኛ እና የፖለቲካ መሪዎች ኃላፊነት ነው።»
የጀርመን መንግስት የሊባኖስ መረጋጋት ወደ አስከፊ ሁኔታ እንዳያመራ ስጋቱን ገልጿል። የመንግስት ቃል አቀባይ እስቴፈን ሳይበርት ዛሬ በሰጡት መግለጫ መራሂተ መንግስት መርክል ሁኔታዉ እንዳሳሰባቸው እና የሀገሪቱ ባለስልጣናትም የተነሳው አመፅ እንደ ሶሪያ እንዳይስፋፋ ማሳሰባቸውን ተናግረዋል።

ልደት አበበ
ሸዋዬ ለገሰ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ተጨማሪ መረጃ ይፈልጉ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW