1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሊባኖስ አጣብቂኝ ዉስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያዉያን

ረቡዕ፣ ነሐሴ 1 2016

በሊባኖስ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን አካባቢዉ ላይ በተፈጠረዉ ዉጥረት በጣም ግራ ተጋብተዋል። ጋዛ ሰርጥ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ተከትሎ፤ ግጭቱ ድንበር ተሻጋሪ እየሆነ መምጣቱ በሊባኖስ ሌላ ቀዉስ እንዳይቀሰቀስ አስግቷል። ኢትዮጵያዉያን አጣብቂኝ ዉስጥ ናቸዉ።

ሊባኖስ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዉያን
ሊባኖስ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዉያንምስል AFP via Getty Images

በሊባኖስ አጣብቂኝ ዉስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያዉያን

This browser does not support the audio element.

በሊባኖስ  አጣብቂኝ ዉስጥ የሚገኙት ኢትዮጵያዉያን

በሊባኖስ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ኢትዮጵያዉያን አካባቢዉ ላይ በተፈጠረዉ ዉጥረት በጣም ግራ ተጋብተዋል። ጋዛ ሰርጥ በእስራኤል እና በሃማስ መካከል የሚካሄደውን ጦርነት ተከትሎ፤ ግጭቱ ድንበር ተሻጋሪ እየሆነ መምጣቱ በሊባኖስ ሌላ ቀዉስ እንዳይቀሰቀስ አስግቷል። ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብም በአካባቢው ጦርነት እና ግጭት እንዳይስፋፋ ለመከላከል ጥረት እያደረገ መሆኑ ተመልክቷል። በዚህ መሃል ሊባኖስ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዉያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ቤሩት የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ቆንስላ አሳስቧል። 
 
ወጣት ኢትዮጵያዊት ጥሪ «ጨንቆኛል ኢትዮጵያዉያን ሊባኖሳዉያን አሰሪዬ ወደ አሜሪካ ሊሄድ ነዉ እኛስ። አገራችንም ሰላም የለም።»
በቤሩት በቤት ሠራተኝነት የምታገለግል ኢትዮጵያዉያን አጋሮችዋን ሃሳብ ምክራቸዉን እንዲያካፍሏት በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴ ጥሪ ያቀረበችበት መልክት በከፊል ነበር።


ሊባኖስ የሚገኙ በመቶ ሺህ የሚቆጠሩ ወጣት ኢትዮጵያዉያንምስል Getty Images/AFP/J. Eid

ሊባኖስን እየለቀቁ ያሉ ዜጎች
በርካታ ሃገራት ዜጎቻቸው በተገኘዉ የአየር መስመር ሊባኖስን በአስቸኳይ ለቀው እንዲወጡ ከጠየቁ በኋላ ፤ በቤይሩት የሚገኘው ራፊክ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ማረፊያ፤ ሊባኖስን ለቆ ለመዉጣት በሚፈልግ ሕዝብ ተጨናንቋል። የኢትዮጵያዉያኑ ቀጣሪ አሰሪ ሊባኖሳዉያንን ጨምሮ የዉጭ ሀገር ዜጎች በቤሩቱ ራፊክ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣብያ፤ ሀገሪቷን ለቀዉ ለመሄድ እየጠበቁ ይገኛሉ። የሊባኖሱ ራፊክ ሃሪሪ ዓለም አቀፍ አውሮፕላን ጣብያ በአሁኑ ወቅት በረራዎችን የሚያስተናግድ ብቸኛዉ የሀገሪቱ የአየር ማረፍያ ነዉ። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ ከአራት እና አምስት ዓመታት ወዲህ በከፍተኛ የኢኮኖሚ ድቀት ዉስጥ የምትገኘዉ ሊባኖስ አሁን ደግሞ የጋዛ ጦርነት ወላፈን አፍጥጦ ተደቅኖባታል የምትለዉ ትህትና የምትባል ሊባኖስ ዉስጥ በቤት ሠራተኝነት የምታገለግል ኢትዮጵያዊት፤ ፈተናዉ ሀገሪቱ ላይ የመጣ ነዉ ስትል ትገልፃለች። 

በኤኮኖሚ ቀዉስ የተዘፈቀችዉ ሊባኖስ፤ ከ 300, 000 የሚበልጡ ኢትዮጵያዉያን ወጣት ሴቶች በአብዛኛዉ በቤት ሠራተኝነት የሚኖሩባት ነች። እንደ ትህትና፤ በአንድ የሊባኖስ ቀበሌ ዉስጥ ከሁለት ሺህ የማያንሱ ኢትዮጵያዉያን ይኖራሉ። ሊባኖስ ወደ አምስት ሚሊዮን ዜጎች እንዳልዋት ይፋዊ መረጃዎች ያመለክታሉ። አብዛኞች ሊባኖሳዉያን ጥምር ዜግነት ያላቸዉ በዉጭ ሃገራት የሚኖሩም ናቸዉ። 

ጀርመንን ጨምሮ ስዊድን፤ ዩናይትድ ኪንግደም፤ ፈረንሳይ፤ ዮርዳኖስ እና ሳውዲ አረቢያ እንዲሁም ደቡብ ኮርያ ዜጎቻቸው ከሊባኖስ እንዲወጡ ማስጠንቀቅያ አውጥተዋል። ምስል Houssam Shbaro/Anadolu/picture alliance

በመካከለኛዉ ምሥራቅ እየጨመረ የመጣዉ ዉጥረት
በእስራኤልና በኢራን መካከል ያለው ውጥረት ወላፈኑ ምናልባትም ሊባኖስ ላይ ሊደርስ ይችላል በሚል ስጋት፤ ጀርመንን ጨምሮ ስዊድን፤ ዩናይትድ ኪንግደም፤ ፈረንሳይ፤ ዮርዳኖስ እና ሳውዲ አረቢያ እንዲሁም ደቡብ ኮርያ ዜጎቻቸውን ከሊባኖስ እንዲወጡ ማስጠንቀቅያ አውጥተዋል። የአገራቱ ማስጠንቀቅያ በመካከለኛዉ ምሥራቅ እየጨመረ የመጣዉ ዉጥረት ሊባኖስን ሊነካ እና ሰፊ ጦርነት ሊያስከትል ይችላል በሚል ስጋት ነው። 


የጀርመን ሉፍታንሳ፣ የፈረንሳይ አየር መንገድ እና ትራንስቪያ አየር መንገድን ጨምሮ በርካታ አየር መንገዶች ወደ ቤይሩት እና ከቤይሩት የሚደረጉትን በረራዎች በማቋረጣቸዉ በተጓዦች መካከል ግራ መጋባትን ፈጥሯል። የኩዌት አየር መንገድ እና የኳታር አየር መንገድም ወደ ቤይሩት የሚያደርጉትን የምሽት በረራ አቋርጠዋል። በቤይሩት ኢትዮጵያዉያንን በመርዳትዋ የምትታወቀዉ ሰላም ተስፋዬ፤ በከተማዋ የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ቆንስላ ኢትዮጵያዉያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ አሳስቧል፤ የኢትዮጵያ አየር መንገድም የምሽት በረራዉን አቋርጧል ስትል ነግራናለች። 

ሊባኖስ ድንበር ማይስ አል-ጃባል ላይ የደረሰ የቦምብ ጥቃትምስል HASSAN FNEICH/AFP


የኢትዮጵያ ቆንስላ ቢሮ መግለጫ
ቤሩት የሚገኘዉ የኢትዮጵያ ቆንስላ ቢሮ ባለሥልጣናት በሳምንቱ መጨረሻ ኢትዮጵያዉያን ወደ ሚሰባሰቡበት ወደ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስትያን ሄደዉ ወረቀት የሌላቸዉ ኢትዮጵያዉያን እንዲመዘገቡ እና ወደ ኢትዮጵያ መሄድ እንዲችሉ ይመቻቻል ሲሉ መናገራቸዉን ኢትዮጵያዉያኑ አክለዉ ገልፀዋል። በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ጥንቃቄ እንዲያደርጉ ሲል በማኅበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ማሳሰብያዉን ያስተላለፈዉ ቤሩት የሚገኘዉን የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት በሊባኖስ ለሚገኙ ኢትዮጵያዉያን ስለሚደረገዉ ጥንቃቄ ለመጠየቅ በስልክ ለማግኘት ያደረግነዉ ጥረት አልተሳካም። 


አዜብ ታደሰ 
ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW