1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በሐይቅ የሚገኙ ተፈናቃዮች የእርዳታ ተማፅዕኖ

ዓርብ፣ መጋቢት 6 2016

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ “ቱርክ” መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የርሀብ ችግር ተጋልጠናል በሚል ለአካባቢው አስተዳደር “በሰልፍ መልክ” ጥያቄ ማቅረባቸውን ተፈናቃዮች ተናግረዋል፣ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብና ጽ/ቤት በበኩሉ እርዳታ ወደ ቦታው ለማድረስ ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ ብሏል፡፡

ሐይቅ ከተማ
ሐይቅ ከተማ ምስል Privat

በሐይቅ የሚገኙ ተፈናቃዮች የእርዳታ ተማፅዕኖ

This browser does not support the audio element.

በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ተሁለደሬ ወረዳ “ቱርክ” መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለከፍተኛ የርሀብ ችግር ተጋልጠናል በሚል ለአካባቢው አስተዳደር “በሰልፍ መልክ” ጥያቄ ማቅረባቸውን ተፈናቃዮች ተናግረዋል፣ የዞኑ አደጋ መከላከልና ምግብና ጽ/ቤት በበኩሉ እርዳታ ወደ ቦታው ለማድረስ ቅድመ ዝግጅት አጠናቅቄያለሁ ብሏል፡፡

“ተቸግረናል አገር ይድረስልን” በሐይቅ የሚገኙ ተፈናቃየች 
በኦሮሚያና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልሎች ቀደም ሲል በነበሩ ግጭቶች ተፈናቅለው በአማራ ክልል ከሚገኙ ተፈናቃዮች መካከል በደቡብ ወሎ ዞን ፣ ተሁለደሬ ወረዳ “ቱርክ” በተባለ መጠለያ ጣቢያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ለምግብ እህል እጥረት መዳረጋቸውን የሚገልጽ ሰልፍ ሰሞኑን ማካሄዳቸውንና ጥያቄያቸውን ለተሁለደሬ ወረዳ አስተዳደር ማሳወቃቸውን ለዶይቼ ቬሌ ገልጠዋል፡፡ 
እንደተፈናቃዮቹ የአካባቢው አስተዳደር “እርዳታ በቅርቡ ይላክላችኋል” እንዳላቸውም አመልክተዋል፡፡ አስተያየታቸውን ከሰጡን የሰልፉ ተሳታፊዎች መካከል አንዷ እንዲህ ብለዋል፡፡ 
“ሰልፍ ያደረግነው ህዝባችን በችግርና በርሀብ በመሰቃየቱ ነው፣ የመንግስት ኃላፊዎች “አይዟችሁ ትረዳላችሁ” ብለው ከፈለግነው ቦታ ሳንደርስ መለሱን፣ አሁን ምንም የምንበላውም፣ የምንጠጣውም የለንም፡፡” 
ሌላዋ አስተያየት ሰጪ በበኩላቸው፣ የወረዳው አስተዳደር በእለቱ “ለእናንተ የሚሆን እርዳታ የለም፣ እንዳላቸውና እስካሁን ያገኙት ነገር እንደሌለ ነው የገለፁት፡፡ 
“ስንዴ ካገኘን 5 ወራችን አልፏል፣ በጣም እየተሰቃየን ነው፣ እራበን ብለን ሰላማዊ ሰልፍ ወጣን፣ ራበን፣ ጠማን ፣ ለልጆቻችን የምንሰታቸው አጣን፣ ብለን አለቀስን፣  የተሁለደረን እስተዳደርና የሐይቅ ከተማን ኃላፊዎች ጠሯቸው፣ መጡ፣ አሁን ለእናንተ የሚሰጥ ነገር የለም፣ ለአካባቢው ተወላጅ እርዳታ ፈላጊዎች ነው እርዳታ ያለው፣ የእናንተ አይደለም ብለው መልስ ሰጡን፣ የተፈናቃይ ኮሚቴዎችና የከተማው አስተዳደርተነጋገሩ ለእኛ ግን ያገኘነው መፍትሔ የለም፡፡” 
ስማቸው እንዳይገለፅ የፈለጉ ሌለው አስተያየት ሰጪ ተፈናቃይ፣ ጥያቄያቸውን ለወረዳው አስተዳደር ለማሳወቅ ወደ ሀይቅ ከተማ ረጅም መንገድ እንደተጓዙ አመልክተዋል፣ በሰልፉ በርካታ ተፈናቃዮች እንደተሳተፉ የነገሩን እኝሁ ተፈናቃይ በአካባቢው ያለው የመንግስት የፀጥታ ኃይል እገዛ እንዳደረገላቸውም ተናግረዋል፡፡

“40 ኪሎ ሜትር የሚሆን መንገድ በእግራችን “ራበን” በማለት ወደ 2000 የምንሆን ተፈናቃዮች ወደ ወረዳው ማዕከል ሐይቅ ተጉዘናል፣ የፀጥታ ኃይሎች መንገድ ላይ ነበሩ፣ የወረዳውን ኃላፊዎች ጠርተው አገናኝተውናል፣ የአካባቢው አስተዳደሮችም ችግሩን እንፈታለን ብለው አወያይተው እኛም የርሀቡን ጉዳይ አስርድተን ተመልሰናል፡፡” ብለዋል፡፡ 
አስተያየት ሰጪዎቹ በእጅጉ እንደተቸገሩና ትኩረት እንዳጡ ነው የሚያስረዱት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ እንደተለመደው ለችግራቸው እንዲደርስላቸውም ተማፅነዋል፡፡ 

ፎቶ ማህደር፤ በአማራ ክልል መጠለያ ጣብያ የሚገኙ ተፈናቃዮች ምስል Alemenw Mekonnen/DW


“... እየተሰቃየን ከሞት ላይ ነው ያለነው፣ በርሀብ አለቅን፣ ... እሺ አይዟችሁ፣ በቃ እኛ እንተባበራችኋለን ብለውን ነበር (የአካባቢው ባለስልጣናት)፣ ምንም ያገኘነው ነገር የለም፣ ታላላቆቹ የሮመዳንና የዐቢይ ፆም በተያዙበት በዚህ ወቅት በጣም ተቸግረናል ድረሱልን፣ ድረሱልን፣ አገር ይድረስልን፣ ህጻናት፣ ነፈሰ ጡሮችር፣ ተጎዳን ወደ ውጪ ወጥተው ለልመና የሄዱም አልሆነላቸውም፡፡ ” 
በጉዳዩ ዙሪያ ተጨማሪ አስተያየት ለማካተት ለተሁለደሬ ወረዳ አስተዳዳሪ ወ/ሮ መቅደስ፣ ለወረዳው ግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ኡስማን ካሳው፣ ለወረዳው አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ በላይ፣ ለክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋሁን ባታብል ከትናንት ጀምሮ ስልክ በተደጋጋሚ ብንደውልም ስልካቸውን ማንሳት አልቻሉም፡፡ 
የደቡብ ወሎ ዞን አደጋ መከላከልና ምግብ ዋትና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አሊ ሰኢድ ሰልፍ ሰለመካሄዱ መረጃ እንዳላቸው ጠቅሰው፣ እርዳታን በተመለከተ “ሰሞኑን ይላክላቸዋል” የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተውናል፡፡ 
“መረጃው (የሰልፉ) ነበረኝ፣ እርዳተው እንደሚቀርብላቸው ካነጋገሯቸው አካላት ጋር ስምምነት ደረሰዋል፣ እርዳታው ተፈቅዶ አልቋል፣ መረጃው ለእኛ ደርሷል ሰሞኑን የእርዳታ እህሉ ይገባላቸዋል፡፡” ነው ያሉት፡፡ 
በደቡብ ወሎ ዞን ብቻ 12 የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያዎች ይገኛሉ፣ በመጠለያ ጣቢያዎቹ 16 ሺህ ተፈናቃዮች ሲኖሩ 30ሺህ ያክሉ ደግሞ ከማህበረሰቡ ጋር ተቀላቅለው የሚኖሩ እንደሆኑ ከዞኑ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡ የአማራና የኦሮሚያ ክልል መንግስታት ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው ለመመለስ የጋራ መግባባት ላይ ደርሰው የተወሰኑ በአማራ ክልል የነበሩ ተፈናቃዮች ወደ ኦሮሚያ ክልል የወለጋ ዞኖች በቅርቡ መመለሳቸው ይታወሳል፡፡

ዓለምነው መኮንን
አዜብ ታደሰ 
ዮኃንስ ገብረግዚአብሔር 
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW