በሐድያ ዞን አንሌሞ ወረዳ የሙስሊሞች ሐይማኖታዊ ጥቃት እደደረሰባቸዉ አስታወቁ
ማክሰኞ፣ ሰኔ 3 2017
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሃድያ ዞን አንሊሞ ወረዳ የሚገኙ የሙስሊም ማህበረሰብ አባላት እንደሚሉት በወረዳው “ በቡድን የተደራጁ “ ባሏቸው አካላት ሃይማኖት ተኮር ጥቃት እየደረሰባቸው ይገኛል ፡፡ የአምነቱን ተከታዮች ማዋከብና ማስፈራራት የተለመደና የቆየ መሆኑን ለዶቼ ቬለ የተናገሩት ከማህበረሰቡ ተወካዮች ከቅርብ ጊዜ ግን ወዲህ ጥቃቱ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል ፡፡
የእምነቱን ተከታዮች ለጥቃት የዳረጋቸው ምክንያት ምንድነው ?
የወረዳው የሙስሊም ማህበረሰብ ተወካይ የሆኑት ሼህ አብዱልፈታህ ነስረዲን እና ያሲን ረመዳን በእምነቱ ተከታዮች ላይ ጥቃቱ መድረስ ከጀመረ ረጅም ጊዜያትን አስቆጥሯል ይላሉ ፡፡ በወረዳው የአምነቱ ተከታዮች አነስተኛ መሆኑ በሌሎች ሃይማኖት የመገፋት አዝማሚያ መኖሩን የጠቀሱት ተወካዮቹ “ ለምሳሌ በወረዳው የተከሰው የሰሞኑ አለመግባባት በመስጂዶች አጠገብ ርቀቱን ያልጠበቀ ቤተክርስቲያን ለመገንባት ከሚደረግ እንቅስቃሴ ጋር የተያያዘ ነው “ ብለዋል ፡፡
“ ድርጊቱ አሁን በሥራ ላይ ያለውንና በቀድሞው የደቡብ ክልል የሥራና ከተማ ልማት ቢሮ በ2007 ዓም የወጣውን አዋጅ የሚጻረር ነው “ በማለት የሚከራከሩት ተወካዮች “ በዚህ አዋጅ በሁለት የተለያዩ የአምልኮ ሥፍራዎች መካከል ያለው ርቀት በከተማ 600 በገጠር ደግሞ እስከ 1ሺህ 500 ሜትር መራራቅ አንዳለበት ይደነግጋል ፡፡ የቤተ ክርስቲያኑ ግንባታ ከህግ አንጻር አግባብ አለመሆኑን ያነሱ የእምነቱ ተከታዮች ወከባና ማሥፈራሪያ እየደረሰባቸው ይገኛል ፡፡ በዚህ ሂደት ላይ ባለፈው ሐሙስ ሌሊት በወረዳው ከአጠገቡ የቤተክርስቲያን ግንባታ የሠራበታል የተባለውና ሱመያ ተብሎ የሚጠራው መስጂድ የታቀደ በሚመስል መልኩ እንዲቃጠል ተደርጓል “ ብለዋል ፡፡
የክልሉ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት መግለጫ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያክልል እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት በወረዳው የደረሰውን የመስጂድ ቃጠሎ በማውገዝ ትናንት ሰኞ መግለጫ አውጥቷል ፡፡ ዶቼ ቬለ በጉዳዩ ላይ ያነጋገራቸው የምክር ቤቱ ዋና ፀሐፊ ኡስታዝ ሳዲቅ ወጌ በወረዳው ሱመያ የተባለው መስጂድ መቃጠሉን አረጋግጠዋል ፡፡ የወረዳው ፖሊስ የድርጊቱን ፈጻሚዎች ይዞ እንዲመረመር ጥያቄ ቢያቀርብለትም እስከአሁን ተግባራዊ ምላሽ አለመሥጠቱን የጠቀሱት የምክር ቤት ዋና ፀሐፊ “ ፖሊስ በተቃራኒው አቤቱታ አቅራቢ የመስጂድ ኮሚቴ አባላትን ለማሰር እየተንቀሳቀሰ ይገኛል “ ብለዋል ፡፡
በምክር ቤቱ ቅሬታ ላይ የፖሊስ ምላሽ
በወረዳው የሙስሊም ማህበረሰቡ አባላት ባነሱት ቅሬታና ተቃጠለ የተባለውን መስጂድ አስመልከቶ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የአንሌሞ ወረዳ ፖሊስ አዛዣ ምክትል ኢንስፔክተር ምሥጋኑ ደገላ በወረዳው የተቃጠለው መስጂዱ ሳይሆን በመስጂዱ ግቢ ውስጥ የነበረና በሣር የተሠራ የወጣቶች የቁራን መመሪያ መድረሳ ጎጆ ቤት ነው ብለዋል፡፡ ፖሊስ በሥፍራው ደረሶ ምርመራ ያልጀመረው ፍላጎት ሥሌለው ሣይሆን የአካባቢው የአገር ሽማግሌዎች ጉዳዩን በባህላዊ አውጫጭኝ ተወያይተን የደረስንበት ለፖሊስ እናሳውቃለን በማለታቸው እንደሆነ የጠቀሱት የፖሊስ አዛዡ “ ነገር ግን የአገር ሽማግሌዎች እስከአሁን ባሉት መሠረት ውጤት ላይ በመድረስ ተጨባጭ ነገር ለፖሊስ ያቀረቡት ነገር የለም ፡፡ በዚህም ምክንያት ፖሊስ በጉዳዩን ላይ የራሱን ምርምራ ለመጀመር ወደ አካባቢው በመጓዝ ላይ እንዳለን ነው አንተም የደወልክልን “ ብለዋል ፡፡
የድርጊቱ ተጣርጣሪ ፈጻሚዎች እንዲያዙ ለፖሊስ አቤቱታ በማቅረባችን ፖሊስ መልሶ እኛኑ ለማሠር እየንቀሳቀሰ ነው በሚል በተነሳው ቅሬታ ላይ የተጠየቁት አዛዡ “ ከእውነት የራቀ “ የሚል አጭር ምላሽ ሰጥተዋል ፡፡
ሸዋንግዛዉ ወጋየሁ
ነጋሽ መሐመድ
ኂሩት መለሰ