በሕገ መንግሥቱ ላይ የተደረገው ጥናት አላማ እና ውጤት
ሐሙስ፣ ግንቦት 10 2015
የኢትዮጵያ ፖሊሲ ጥናት ተቋም በፖለቲካ ልኂቃን፣ በፖለቲከኞች እና በማኅበረሰብ አንቂዎች ክፉኛ የሚተቸውን የኢትዮጵያ ሕገመንግሥት ላለፉት ሁለት ዓመታት ማጥናቱን ይገልጻል። ሕገ መንግሥቱ ከመነሻው በአጨቃጫቂነቱ እንደሚታወቅ ያመለከቱት በተቋሙ የጥናቱ አስተባባሪ ዶክተር ጥላሁን ተፈራ ጥናቱ እንዲካሄድ መነሻ ነው ያሉትን ገልጸዋል። የፌደራላዊት ሪፑብሊክ ኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት በተመለከተ አሉ ያሏቸውን ሦስት እሳቤችንም ዘርዝረዋል፤ «አንዱ ይኽ ሕገ መንግሥት በምንም መልኩ መነካት የለበትም እንደውም ተጠናክሮ በደንብ ወደ መሬት መውረድ አለበት ሲል፤ ሌላኛው ጽንፍ ሕገ መንግሥቱ የተጻፈበትን ቀለም እንኳ ያህል ዋጋ የለውም ተቀዶ መጣል አለበት በሚል እንደሚጣጥል፤ ሦስተኛው ደግሞ ሕገ መንግሥቱ ጥሩ ነገሮች አሉት እነሱን ማስቀጠል፤ የሚሻሻሉ ካሉ ደግሞ እነሱን እያሻሻሉ መቀጠል እንጂ ከዜሮ መጀመር አስፈላጊ አይደለም የሚል ነው።»
ኢትዮጵያ ውስጥ ለሚታዩ የብሔር መልክ የያዙ ግጭቶችና መፈናቀሎች በዋነኛነት ሕገ መንግሥቱን ሙሉ በሙሉ ተጠያቂ የማድረግ አካሄድ እንደሚታይ ያመለከቱት ዶክተር ጥላሁን መንግሥትን እንደሚያማክር አንደ አንድ መንግሥታዊ ተቋም አንዳንድ ልኂቃንም ሆኑ የማኅበረሰብ አንቂዎች እንደሚሉት ሕገ መንግሥቱ የችግሩ ሁሉ ምንጭ ነው ወይ የሚለውን ለመመልከት መሞከሩንም አንስተዋል። ስለሕገ መንግሥቱ አወዛጋቢ ነጥቦች ይነሳሉ ያሉት የጥናቱ አስተባባሪ የዳሰሳ ጥናቱ ያተኮረው በተለይ ከብሔር ብሔረሰቦች ድንጋጌ ጋር ተያይዘው ባሉት ላይ መሆኑንም አስረድተዋል።
ሕገመንግሥቱን አስመልክቶ የሚሰነዘሩ ትችቶች በጥናቱ ዳሰሳ መንደርደሪ ላይ በስፋት መታየቱንም ዶክተር ጥላሁን ገልጸዋል። በሀገሪቱ ለሚታየው ውዝግብ ተጠያቂ ተደርገው የሚጠቀሱ አንቀጾችን በተመለከተ የተለያየ አስተያየት እንዳለ በማመልከትም የጥናቱን ውጤትም አብራርተዋል።
ለመንግሥት ባቀረቡት ምህረ ሃሳብም መንግሥት አሁን ባለው ሁኔታ ላይ ሕገመንግሥቱን መቀየርም ሆነ ማሻሻልን በተመለከተ ቀነገደብ እንዳያስቀምጥ ማሳሰባቸውን አክለው ገልጸዋል። ሃሳቡ ካለም አስቀድሞ ኅብረተሰቡን ያሳተፈ ተደጋጋሚ ውይይት ሊደረግበት እንደሚገባም አጽንኦት ሰጥተዋል።
የዳሰሳ ጥናቱ ከትግራይ ክልል በቀር በሌሎች በሁሉም ክልሎች መደረጉን ያመለከቱት ዶክተር ጥላሁን ጥናቱ ትልቅ ግብአት ይሆነዋል ላሉት ለሀገራዊ ምክክር ኮሚሽን መሰጠቱንም ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል። አጠቃላይ የዳሰሳ ጥናቱ ያመለከተው ኅብረተሰቡ አንድ ላይ ከመኖር የተለየ ሃሳብ እንደሌለው መሆኑንም አስረድተዋል።
ሸዋዬ ለገሠ
ኂሩት መለሰ