1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በመሬት መንቀጥቀት የተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች አቤቱታ

ሥዩም ጌቱ
ዓርብ፣ የካቲት 28 2017

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ ከቤታቸው የተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች ችግር ላይ ወድቀናል አሉ፡፡ አርብቶ አደሮቹ ከተደጋጋመው ርዕደ መሬት በኋላ ከብቶቻቸውን በሙሉ ይዘው ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል ከተገደዱ ወዲህ ላለፉት ሁለት ወራት ገደማ ፈተና ላይ መዉደቃቸዉን እየገለፁ ነዉ።

በመሬት መንቀጥቀጥ የተፈናቀሉ
በመሬት መንቀጥቀጥ የተፈናቀሉ ምስል፦ private

የኢትዮጵያው መሬት መንቀጥቀጥ ነዋሪዎችን እንዳሰጋ ነዉ

This browser does not support the audio element.

በመሬት መንቀጥቀት የተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች አቤቱታ

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ፈንታሌ ወረዳ ተደጋጋሚ የመሬት መንቀጥቀጥን ተከትሎ ከቤታቸው የተፈናቀሉ አርብቶ አደሮች ችግር ላይ ወድቀናል አሉ፡፡ አርብቶ አደሮቹ ከተደጋጋመው ርዕደ መሬት በኋላ ከብቶቻቸውን በሙሉ ይዘው ከቤት ንብረታቸው ለመፈናቀል ከተገደዱ ወዲህ ላለፉት ሁለት ወራት ገደማ ወደ አስፋልቱ ዳር በመጠለያ ቢሰበሰቡም በሁለት ነገሮች መፈተናቸውን ነው የሚናገሩት፡፡ አንደኛው ችግራቸው በቂ የምግብ ድጋፍ አለመቅረብ፤  ሌላው ችግራቸው ደግሞ እየበረታ በመጣው የበጋ ሃሩር በቂ መኖ የማያገኙት ከብቶቻቸው እያለቁባቸው መሆኑን ነው የገለጹት፡፡

የአርብቶ አደሮቹ ምሬት

ጅማ ፈንታሌ በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ሸዋ ዞን ከፈንታሌ ወረዳ ተራራማ አከባቢዎች ተፈናቅለው ለመጠለያ ወደ ተዘጋጀው ስፍራ ከመጡ የአከባቢው አርብቶ አደሮች አንዱ ናቸው፡፡ አፋር እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳን አከባቢን በተደጋጋሚ የመታውን የመሬት መንቀጥቀጥ ተከትሎ ቤተሰቦቻቸውን እና ከብቶቻቸውን ይዘው መኖሪያ ቀዬያቸውን የለቀቁት ጅማ እና ሌሎችም የአከባቢው አርብቶ አደሮች ድህረ መፈናቀል ግን ህይወት ቀላል የሆነላቸው አይመስልም፡፡ “ከተፈናቀልን ወዲህ አስቸጋሪ ህይወት እየመራን ነው፡፡ በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ከቀዬው የተፈናቀለ ሁሉ በጣም እየተጎዳ ነው፡፡ ያንን ሽሽት ተራራው እንዳይናድብን ብለን አሁን ወደ አስፓልቱ ዳር ብንመጣም አስከፊ ህይወት እየመራን ነው ያለነው” ሲሉ እገፉት ያለው ኑሮ ከለመዱት በተቃራኒ በመሆኑ ፈተናውም እንደከበዳቸው አስረድተዋል፡፡የጠለምት መሬት መንሸራተት ተፈናቃዮች ቅሬታ

ሌላው አስተያየት ሰጪ የአከባቢው ተፈናቃይ አርብቶ አደር አቶ ቡላ ፈንታሌም ላለፉት ሶስት ወራት ኢላላ በተባሌ የፈንታሌ ወረዳ ቀበሌ ውስጥ ከመታሃራ ወደ አዳማ በሚወስድ ወና መንገድ ዳር መኖሪያቸው አድርገዋል፡፡ እንደሳቸው አስተያየትም ያፈናቀላቸው የመሬት መንቀጥቀጥ ቀላል ፈተና ላይ አይደለም የጣላቸው፡፡ “በመሬት መንቀጥቀጡ ምክንያት ከወጣን በኋላ በዚህ በበጋ ሀሩር ጉዳት ላይ ነው የወደቅነው፡፡ ከምንም በላይ አሁን ተፈናቅለን በዚህ አስፓልት ዳር የወደቅንበት ጊዜ ከባድ ሀሩር ያለበት በመሆኑ የፈተነን አንደኛው ነገር እሱ ነው፡፡ እኛ እንዲህ ያለ ፈተና ተጋርጦብን አያውቅም፡፡ አሁን የበጋው ድርቅም ከፍቶብናል፡፡ እጅግ አስቸጋሪ ነው፡፡ እንዲህ መሬት መንቀጥቀት ብሎ ነገር አይተንም ሰምተንም የማናውቅ ነበር መናይነት ቁጣ እንደሆነ ነው ያልገባን” ሲሉ አማረዋል፡፡

የእርዳታ አቅርቦቱ እጥረት

ተፈናቃይ አርብቶ አደሮቹ ቀዬያቸውን ለቀው በመጠለያ በተሰባሰቡበት ባሁን ወቅት እንደ ልባቸው ተንቀሳቅሰው ማምረት እንደማይችሉ ነው የሚገልጹት፡፡ ታዲያ በዚህ በብርቱ ፈተና በሚፈተኑበት በዚህን ወቅት በመጠለያ ሳሉ የሚቀርብላቸው ድጋፍም በቂ አለመሆኑን ነው ያስረዱን፡፡ “በርግጥ የሚደርሰን የተወሰነ እርዳታ አለ፡፡ ግን በበቂ ሁኔታ የሚዳረስ አይደለም፡፡ የተፈናቀለ ሰው እጅግ ብዙ ነው፡፡ እኛ በቁጥር ባናውቅም ቆጥረህ የምትጨርሰው አይደለም፡፡ እጅግ ብዙ ማህበረሰብ ነው አደጋውን ሽሽት ተፈናቅሎ በዚህ አስፓልት ዳር የወደቀው፡፡ የሰባት ቀበሌ ነዋሪ መፈናቀል ማለት ቀላል ነገር አይደለም” ሲሉ የሚቀርበው ድጋፍና የተፈናቀለውና እርዳታ የሚጠብቀው ማህበረሰብ ቁጥር እንደማይመጣጠን አስረድተዋል፡፡

ሌላኛውም ተፈናቃ አስተያየታቸውን ቀጠሉ፤ “እርዳታው አለ፡፡ አልፎ አልፎ ይቀርባል፡፡ ግን በፍፁም በቂ አይደለም፡፡ የሚቀርብልን የተወሰነ የምግብ እንዲሁም እንደ ዛይት ያለ ነገር ነው፡፡ የሚቀርበው ይህ እርዳታ እንደው ሰውን ከሞት አትርፎን ህይወታችንን የሚያቆይልን አይደለም” ብለዋል፡፡

ጠለምት መሬት መንሸራተት ምስል፦ Alemenew Mekonnen/DW

የከብቶች እልቂትየኢትዮጵያው መሬት መንቀጥቀጥ ነዋሪዎችን እንዳሰጋ ነዉ

አርብቶ አደሮቹ ከበጋው ወቅት ጋር ተያይዞ የመጣባቸው መፈናቀሉ በሰው ላይ ብቻ ሳይሆን ይዘው የተፈናቀሉትን ከብቶቻቸውንም በእጅጉ ጎድቶባቸዋል፡፡ አሁን ከተፈናቀሉ ወደ ሶስት ወራት ግድም እየተጠጉ መሆኑን አስታውሰው አስተያየታቸውን የሰጡን አርብቶ አደር ከብቶቻቸውን ይዘው ወደ መጠለያዩ ብመጡን በዚህ በበጋው ሀሩር ከብቶቻቸውን የሚመግቡት በቂ ሳር ግን አያገኙም፡፡ “ከብቶቻችንን እየጎዳብን ነው በጋና የመኖ ፍላጎት እጥረቱ፡፡ በተለይም ፍየሎቻችን እያለቁብን ነው፡፡ ለከብቶቻችን በቂ መኖ የምናገኝበት ያው በዚያ በምንኖርበት ጋራ አከባቢ ነበር፡፡ እዚህ ግን ከብቶቹን የምንመግበው ምንም አንድም ነገር ስለሌለ ከብቶች፣ ፍየሎቻችን እና በጎች እያለቁብን ነው፡፡ እናም ከሰውም በላይ እነሱ እየተጎዱብን ነው” ሲሉ ያፈናቀላቸው መሬት መንቀጥቀጡ ሌላ ጦስ ይዞባቸው እንደመጣ አስረድተዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ አርብቶ አደሮቹ ባቀረቡት አቤቱታ ላይ አስተያየታቸውን እንዲሰጡበት ለምስራቅ ሸዋ ዞን ቡሳጎኖፋ ኃላፊ አቶ ኤሊያስ ቃሲም እና ለክልሉ አደጋ ስጋት ቢሮ (ቡሳ ጎኖፋ) ኃላፊ አቶ ሞገስ ኢዳኤ በተደጋጋሚ ብደውልላቸውም ስልካቸው ባለመመለሱ ለዛሬ አስተያየታቸውን ማካተት አልተቻለም፡፡

አርብቶ አደሮቹ ከባድ ያሉት በተደጋጋሚ የመታቸው የመሬት መንቀጥቀጡ ግን የልጆቻቸውን ናላ የሚያዞር እና አስከፊ እንደነበር በመግለጽ ወደ ቀዬያቸው ለመመለስም አደጋውን እንደሚፈሩ አመልክተዋል፡፡ በአፋር ክልል ዞን ሶስት በሚገኙ ሁለት ወረዳዎች ውስጥም ተመሳሳይ ችግር የደቀነው ርዕደ መሬቱ በቅርቡ የቀሰም ስኳር ፋብሪካ ሰራተኞቹን ለመበተን ማስገደዱን መዘገባችን ይታወሳል፡፡ 

ሥዩም ጌቱ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW