በመቀሌ ከተማ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት እና የነዋሪው ስጋት
ዓርብ፣ ኅዳር 19 2018
በመቀሌ ከተማ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት እና የነዋሪው ስጋት
ጥቃቱ ስማቸው ባልተጠቀሰ የሰላም ጸጥታ የስራ ኃላፊ ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን እንዳልቀረ ዶቼ ቬለ ያነጋገራቸው የመቀሌ ከተማ ነዋሪ ተናግረዋል። የከተማዋ የሰላም እና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ረዳኸኝ ፍሰሃ በከተማዋ አዲ ሃቂ ክፍል ከተማ «የሽብር ተልዕኮ በተሰጣቸው » ሰዎች የተወረወረው ቦምቡ በሰው ህይወት ወይም በንብረት ላይ ያደረሰው ጉዳት የለም ብለዋል።
ትናንት ሐሙስ ምሽት መቀሌ ከተማ በአዲ ሃቂ ክፍለ ከተማ የተፈጸመው የቦምብ ጥቃት ስማቸው ያልተገለጸ የሰላም እና ጸጥታ ኃላፊ መኖሪያ ቤት ላይ ያነጣጠረ ሳይሆን እንዳልቀረ ስማቸውንም ሆነ ድምጻቸውን እንዳንጠቀም የጠየቁ የከተማዋ ነዋሪ ለዶቼ ቬለ ተናግረዋል።
«የሰላም እና ጸጥታ ኃላፊ ቤት ነውና ለእሱ ታርጌት የተደረገ ይሆናል የሚል ጥርጣሬዎች አሉ።»
የቦምብ ፍንዳታው እንደደረሰ የቆየ ቦምብ ይሁን አዲስ የተወረወረ ወዲያው መለየት እንዳልተቻለ የተናገሩት ነዋሪዋ በጥቃቱ የቤቶች መስታወት ከመርገፍ ውጭ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ ተናግረዋል።
እንዲያም ሆኖ ግን የአይን ምስክሯ ፍንዳታው በነዋሪው ላይ «ከፍተኛ ድንጋጤ እና ስጋት አሳድሯል።» ብለዋል።
« ነዋሪውማ ምን መሰለህ የፍርሃት ስሜት ነው ያለው። አሁን ያለው ሁኔታ መቼስ ታውቀዋለህ ትግራይ ውስጥ የሰላም እና የጸጥታው ሁኔታ ጠንካራ አይደለም። እንደዚህ የሌላ የተቃዋሚ ድርጅቶች የእነርሱ ገብቶ እንደዚህ ሊያደርጉ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ አለ።
ሌላ ስማቸው እንዳይገለጽ የጠየቁን የከተማዋ ነዋሪ እንደሚሉት የትናንት ምሽቱ የቦምብ ጥቃትም ሆነ በቅርቡ በትግራይ እና አፋር ክክሎች አዋሳኝ አካባቢዎች ተከስቶ የነበረው ውጥረት ከፍተኛ የደህንነት ስጋት ይዞባቸው እንደመጣ ነው።
«ብዙ ችግር ነው የሚፈጥረው ያለው ፤ ብዙ ስጋት በህብረተሰቡ ላይ እያመጣ ነው። እና ብዙ ስጋት ያሳድራል አየህ ። ህዝቡ ጦርነቱ አንገሽግሾታል፤ በጣም ተሰላችቷል፤ እንደገና አሁን እየተሞከረ ያለው እርስ በርስ የሚመስል ጦርነት ነው፤ እርስ በርስ ነው፤ ወንድም ለወንድም ነው።»
የቦምብ ጥቃቱ ስለመፈጸሙ ከማህበራዊ መገናኛ ገጾች እንደተመለከቱ የገለጹ ሶስተኛ ስማቸውን እንዳይጠቀስ የጠየቁን የከተማዋ ነዋሪስለጥቃቱ እየተሰራጨ ያለው መረጃ ትንሽ የተጋነነ ነው ብለዋል።
«እንደተወራው እና ሶሻል ሚዲያ ላይ እንደተገለጸው እንደዚህ አይነት የቦምብ ፍንዳታ ነበር እየተባለ ነው። አጋጣሚ እኛ አካባቢ እንኳ ብዙ የተለየ ድምጽ አልሰማንም ፤ አሁን ባለው ኹኔታ ብዙ ሰውም እንደታሰበው አይደለም።፤ ሶሻል ሚዲያ ላይም እንደሚወራው አይደለም። በአንዳንድ የንግድ አካባቢዎች ተጽዕኖው እስከዚህም አይደለም ፣»
በከተማው ደረሰ ስለተባለው የቦምብ ጥቃት የከተማዋ እና የክልሉ የሰላም እና ጸጥታ ባለስልጣናትን ለማነጋገr ያደረግነው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካልንም። ነገር ግን ጥቃቱን ተከትሎ በሰው እና በንብረት ላይ የደረሰ ጉዳት እንደሌለ የመቀሌ ከተማ የሰላም እና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ረዳኸኝ ፍሰሃ መናገራቸውን ከመቀሌ ከተማ የሚሰራጭ ኤፍ ኤም 104.4 ዘግቧል። አቶ ረዳኸኝ ለሬዲዮ ጣቢያው እንዳሉት ከምሽቱ 4 ሰዓት ከ25 በላይኛው የቢዝነስ ካምፓስ በር አካባቢ «የመቀሌ ሰላም እና ጸጥታን ለማናጋት ህዝብን ለመረበሽ ተልዕኮ ባላቸው» የጥፋት ኃይሎች ሆን ተብሎ የተወረወረ ቦምብ በሰው ህይወት ይሁን በንብተት ጉዳት አላደረሰም።»
እሳቸው እንደዚያ ይበሉ እንጂ አስተያየታቸውን ለዶቼ ቬለ የሰጡ የከተማዋ ነዋሪዎች እንደሚሉት በከተማዋ የጸጥታ ሁኔታ የደህንነት ስጋት እንደገባቸው ነው።
« በጣም ይፈራል፣ ይሰጋል ፣ በቃ እንዳልኩህ መዋቅሩ በተለይ የጸጥታ እና ሰላም ኹኔታው በደንብ የተጠበቀ አይደለም ፤ የሚል ነገር አለ ህብረተሰቡ ዘንድ ። እየሰሩ አይደለም፤ ቢሮው ትንሽ ካሁን በፊትም ዝርፊያዎች ነበሩ በየቤቱ እንደዚህ ሱቆች ምናምን አካባቢ እሱን ባለመፍራታቸው ነው ይህ እያጋጠመ ያለው። »
« ነጻ እንቅስቃሴ ህብረተሰቡ ሰርቶ የመኖር እንቅስቃሴ እየተስተጓጎለ ነው፤ ስርቆት እና ዘረፋምእየበዛ ነው፤ ያለመተማመን እና እርስ በርስ ህዝቡ መጠራጠር እየበዛ ነው፤ ይመስለኛል ህዝቡን እርስ በርሱ ለመለያየት ነው የሚመስለኝ»
መዲናዋ መቀሌን ጨምሮ በመላው በክልሉ እና እንደ ኢትዮጵያ ለሚታዩ የደህንነት እና የጸጥታ ችግሮች መፍትሔ ያሉትን የነገሩን በንግድ ስራ የሚተዳደሩት የከተማዋ ነዋሪ ነጎሮች ከዚህ ገፍተው ሳይሄዱ ሁሉም ለመፍትሔው መምከር እንደሚገባው ነው ያሳሰቡት ።
« ከልባቸው ሁሉም አካሎቶች ይሔኛው ያኛው ሳንል ፣ ሁሉም አካላቶች ከልባቸው ተቀብለው ፣ ሰላም ማስፈን ሰው ተረጋግቶ እንዲሰራ ፣ የኤኮኖሚ ማነቃቂያ ፣ ስራ ዕድል ፈጠራዎች ፣ ዋናው ግን ሰላም ላይ ቢሰሩ የተሻለ ነገር ይኖራል ፤ ሰው ወደ ነበረበት የመመለስ ዕድሉ የተስፋ ጭላንጭል ይኖረዋል።»
ታምራት ዲንሳ
ነጋሽ መሐመድ