1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በመቐለ ፆታዊ ጥቃቶችን በመቃወም ሰላማዊ ሰልፍ ተካሄደ

እሑድ፣ ጥቅምት 30 2012

በትግራይ ክልል ሴቶች ላይ የሚፈፀመው ፆታዊ ጥቃት የሚያወግዝ የተቃውሞ ሰልፍ ዛሬ በመቐለ ከተማ ተካሄደ። በሰልፉ ፆታዊ ጥቃትን የሚያወግዙ መፈክሮች በፅሑፍ የቀረቡ ሲሆን አካላዊ እና ስነ ልቦናዊ ጥቃቶችም በጥበባዊ መንገድ ተንፀባርቀዋል፡፡

Äthopien,  Mekelle: Protest gegen Gewalt an Frauen
ምስል፦ DW/M. Haileselassie

በትግራይ በሴቶች ላይ የሚደርስ ጥቃቶችን የሚቃወም ሰልፍ ተካሄደ

This browser does not support the audio element.

በትግራይ ሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት የሚያወግዝ ሰልፍ ዛሬ ጠዋት በመቐለ ሲካሄድ ቁጥራቸው ሁለት መቶ ገደማ የሚገመቱ በአብዛኛው ሴቶች ተገኝተውበታል። መነሻው እና መድረሻውን በመቐለ ሮማናት አደባባይ ያደረገው የተቃውሞ ሰልፍ በሁለት ክፍል የተከፋፈለ ነበር። 

በመጀመሪያው ክፍል በሰልፉ ተሳታፊዎች አማካኝነት በሴቶች ላይ የሚደርሰው ፆታዊ ጥቃት የሚያወግዙ ግጥሞች እና የሙዚቃ ስራዎች ቀርበዋል። በማስከተል የነበረው ክፍል "ሴቶች ላይ እየደረሰ ነው" የተባለው "መታፈን" በአርምሞ የተንጸባረቀበት ነበር።  

ሰልፈኞቹ "ፆታዊ ጥቃቶች ይቁሙ፣ መንግስት ዜጎቹን ከፆታዊ ጥቃት ይከላከል፣ ይኾኖ" የሚሉ እና ሌሎች በርካታ መፈክሮች ይዘው በዝምታ በዋና ዋና መንገዶች ተቃውሟቸውን ሲያሰሙ ታይተዋል። ከዚህ በተጨማሪ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃቶች የሚገልፁ በሜክአፕ አርቲስቶች የተሰሩ ስራዎችም ቀርበዋል። 

ከሰልፉ አስተባባሪዎች መካከል አንዷ የሆነችው ወይኒ አብርሃ በዛሬው ሰላማዊ ሰልፍ ሴቶች ላይ የሚደርሱ ጥቃቶች በአደባባይ ለማሳየት እንደተሞከረ ለዶይቼ ቬለ (DW)ተናግራለች። በዛሬው የተቃውሞ ሰልፉ ተሳታፊ ከነበሩ ወንዶች መካከል አንዱ የነበረው ለአከ ዘገየ በበኩሉ አጀንዳው ከሴቶች ባለፈ የመላው ማሕበረሰብ ጉዳይ በመሆኑ በሰልፉ መሳተፉን ገልጿል። 

በትግራይ ሴቶች ላይ የሚደርሰውን ፆታዊ ጥቃት ለማውገዝ የተጠራው ሰልፍ በመቐለ ከተማ አስተዳደር እውቅና የተሰጠው ቢሆንም ሰልፉ የተካሄደበት አደባባይ ለተሽከርካሪዎችም ክፍት ስለነበረ ተደጋጋሚ መስተጓጎሎች ሲያጋጥሙ ተመልክተናል። የሰልፉ ተሳታፊዎችም በዚህ ጉዳይ ቅሬታቸውን አሰምተዋል። 

የተቃውሞው ሰልፍ በተደጋጋሚ ይደረጋል ተብሎ አንዴ በከተማው አስተዳደር ክልከላ ሌላ ጊዜ በራሳቸው በአዘጋጆቹ ሲራዘም መቆየቱ ይታወሳል። የሰልፉ አዘጋጆች  “ይኾኖ” በሚል መሪ ቃል በትግራይ ክልል የሚፈፀሙ ፆታዊ ጥቃቶችን የሚቃወም እና የህብረተሰቡን ግንዛቤ ለማሳደግ ያለመ ዘመቻ በማህበራዊ መገናኛ ዘዴዎች ከሰሞኑ ሲያካሄዱ ቆይተዋል።

ሙሉ ዘገባውን ለማድመጥ የድምጽ ማዕቀፉን ይጫኑ። 

ሚሊዮን ኃይለስላሴ

ተስፋለም ወልደየስ
 

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW