ስለመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ረቂቅ ማሻሻያ የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አስተያየት
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 30 2017የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት በመገናኛ ብዙኃን ረቂቅ ማሻሻያ አዋጅ ላይ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያቀረባቸው አስተያየቶች በአግባቡ ዕየታዩ ይሆናል ብሎ እንደሚያምን ገለፀ ። በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የዴሞክራሲ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በጉዳዩ ላይ ሕዝባዊ ውይይት ካደረገ በኋላ በተናጠል የመገናኛ ብዙኃን ምክር ቤቱን ጠርቶ ውይይት መደረጉን የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኅን ምክር ቤት ዐሳውቋል ።
ለተወካዮች ምክር ቤት የቀረበው ረቂቅ ማሻሻያ፤ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣኑንም ሆነ የቦርዱን ተቋማዊ ነፃነት የመገደብ አንድምታ አለው ያለው ምክር ቤቱ የቀጥታ ስርጭትን በተመለከተ በማሻሻያ ረቂቁ ላይ የቀረበው ሐሳብ መገናኛ ብዙኃንን የሚጎዳ ነው በሚል እንዲቀር በጽሑፍ እና በቃል ሥጋቱን መግለጹን ዐሳውቋል ።
በረቂቅ አዋጁ እንዲካተቱ እና እንዲሻሻሉ የተጠየቁ ዋና ዋና ገዳዮች
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጥቅምት 19 ቀን፣ 2017 ዓ.ም አዋጅ ቁጥር 1238/2013ን ለማሻሻል የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ላይ ሕዝባዊ ውይይት ተደርጓል። ከወራት በፊት በተደረገው ውይይቱ በአመዛኙ የቀረበው የማሻሻያ ሕሳብ ውድቅ እንዲሆን ጥያቄ በሰፊው የቀረበበት ነበር። ከዚያ ውይይት በኋላ ከሳምንት በፊት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ብቻውን ለውይይት የተጋበዘ ሲሆን የዚህ ምክንያቱ ምንድን ነው የሚለውን የምክር ቤቱን ምክትል ሥራ አስፈፃሚ አቶ ታምራት ኃይሉን ጠይቀናቸዋል። «የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ከ102 በላይ የሚሆኑ መገናኛ ብዙኃንን እና የጋዜጠኞች የሞያ ማህበራትን አንድ ላይ አቅፎ እየተንቀሳቀሰ ያለ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በድምሩ በሚነሱት ሀሳቦች ይንጸባረቃሉ በሚል ሀሳብ ይመስለናል።»
የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአዋጁ ማሻሻያ አሳሳቢ የሆነው በውስጡ ምን ስለያዘ እንደሆነ አብራርቷል። "ፈቃድ ማገድ፣ መሰረዝና አለማደስን የሚመለከተው ስልጣን ከቦርዱ ተወስዶ ለባለስልጣኑ መሰጠቱ፣ የቦርድ አባላት የፖለቲካ ፓርቲ አባል እንዳይሆኑ የሚከለክለው አንቀፅ መውጣት፣ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዲሬክተር በቦርዱ አቅራቢነት በፓርላማው ይሾማል የሚለው አንቀፅ በጠቅላይ ሚኒስትሩ አቅራቢነት በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ይሾማል በሚል መተካቱን ጠቅሷል።
በረቂቁ የ«መገናኛ ብዙኃን ፈንድ» ይቋቋም የሚለው ሐሳብ እንዲካተት ጥሪ ቀርቧል
መገናኛ ብዙኃን በቀጥታ ሥርጭት ወቅት ከዚያኛው ተናጋሪ አካል የሚመጡ ያልተገቡ ሀሳቦችን አስተካክሎ የማለፍ እንጅ እንዲህ ያለው ሁኔታ ሲያጋጥማቸው የወንጀል ተጠያቂ ሊሆኑ የሚገባበት ድንጋጌም ሊቀር እንደሚገባ ነው ጥያቄ የቀረበው። «ግለሰቦች በቀጥታ ውስጥ በሚናገሩበት ወቅት ጋዜጠኛው በዚያኛው ወገን ያለው ተናጋሪ ምን እያሰበ እንደሆነ፣ ቀጥሎ ምን ሊናገር እንደሚችል ማወቅ አይችልም፣ መገመት አይችልም።»
አቶ ታምራት ኃይሉ እንደሚሉት ሌላው ምክር ቤታቸው ያቀረበው ጥያቄ የ "መገናኛ ብዙኃን ፈንድ" እንዲቋቋም ሲሆን፣ ይህም መገናኛ ብዙኃን የገንዘብ እጥረት ሲገጥማቸው ሕዝብን ከማገልገል እንዳይስተጓጎሉ እና ከመክሰም እንዲድኑ በሚል የቀረበ ሐሳብ ነው። «መገናኛ ብዙኃንን ይታደጋል፤ በፕረስ አካባቢ እየጠፋ የመጣውን የሕትመት ሚዲያ ለመታደግ እና ለማገዝ ሌላ አማራጭ ይሆናል የሚል እምነት አለን።»
ይህ ጥያቄ የመገናኛ ብዙኃኑን በነጻነት እና በገለልተኛነት የመሥራት ኹኔታ ጥያቄ ውስጥ አያስገባም ወይ በሚል ጥያቄ የቀረበላቸው አቶ ታምራት መጀመርያ በሀሳቡ ላይ መስማማት ላይ ከተደረሰ የማስተዳደሩ ነገር ሁለተኛ ጉዳይ መሆኑን በመጥቀስ እንዲያውም እንዲጠናከሩ የሚያግዝ ነው ብለዋል።
የመገናኛ ብዙኃን አዋጅ ማሻሻያው በሲቪክ ማኅበራት ተቃውሞ የቀረበበት ነው
ረቂቅ ማሻሻያው ለውይይት በቀረበበት ወቅት 14 የሙያ ማህበራት በጋራ ባወጡት መግለጫ ሂደቱ "ዴሞክራሲን ከማስፈንና የመገናኛ ብዙኃንን ነጻነትን ከማረጋገጥ አንፃር አስቻይ የሕግ ማዕቀፎችን የሚንድና ወደኋላ የሚጎትት እንዳይሆን"፤ በሌላ በኩል "ማሻሻያውን ለማዘጋጀት የተሔደበት መንገድ ግልጽነትና አሳታፊነት የጎደለው፣ የረቂቅ አዋጁ አስፈላጊነት በገለልተኛ አካል በተሠራ ጥናት ስለመለየቱ የቀረበ ማስረጃ የለም።" ሲሉ ማህበራቱ ተቃውመውት ነበር። ይህንን ተቃውሞ ካቀረቡት ሲቪክ ማህበራት ጥቂቲቹ መታገዳቸው ይታወቃል።
ሰለሞን ሙጬ
ማንተጋፍቶት ስለሺ
እሸቴ በቀለ