በሙስና የተጠረጠሩ ባለሥልጣናት ታሰሩ
ዓርብ፣ ኅዳር 23 2015
በቅርቡ የተቋቋመው ብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ በሙስና የተጠረጠሩ ባለሥልጣናትን በቁጥጥር ስር ማዋሉን አስታወቀ። ኮሚቴው ሥራውን መጀመሩን ይፋ ባደረገበት በዛሬ መግለጫው የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለን ጨምሮ በሙስና ወንጀል የተጠረጠሩ ባለሥልጣናትን ማሰሩን ገልጿል። ኮሚቴው ዛሬ ይፋ ያደረገው በሙስና የተጠረጠሩ የባለሥልጣናት እስር ወንጀሉ ለሀገርም ለመንግሥትም ስጋትነቱ ከፍተኛ ደረጃ መድረሱን እንደሚያመላክት ተገልጿል።
አቶ ጌዴዎን ጢሞቴዎስ የኢትዮጵያ የፍትኅ ሚኒስትር እና አዲስ የተቋቋመው የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴው አባል በሰጡት መግለጫ፤ «በፍትህ እና በጸጥታ ዘርፍ ሥልጣናቸውን ያለአግባብ በመጠቀም የዜጎችን ሰላም እና የሀገርን ደህንነት የማስጠበቅ ኃላፊነታቸውን ተገን አድርገው በተለያየ ሕገወጥ መንገድ ከግለሰቦች እና ከንግድ ድርጅቶች ገንዘብ እና ሀብት ለመውሰድ የተንቀሳቀሱ ተጠርጣሪዎች» ያሏቸው ባለሥልጣናት መለየታቸውን እና መታሰራቸውን ገልጸዋል። በሙስና ወንጀል ተጠጥረው ከታሰሩት ባለሥልጣናት የፋይናንስ ደህንነት አገልግሎት ዋና ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ በቀለ በስም ተጠቅሰዋል። ዶክተር ጌዲዮዎን አክለውም ከዚህ ቀደምም በተመሳሳይ ወንጀል የተጠረጠሩ አቃቢያነ ሕግ፤ የጽሕፈት ቤት ኃላፊን ጨምሮ የማረሚያ ቤት አዛዦች፤ የፖሊስ ኃላፊዎች እና ዳኞች ጭምር በቁጥጥር ስር ውለው ክስ እንደተመሰረተባቸውም አመልክተዋል። ከዚህም ሌላ ከመሬት እና ኮንዶሚኒየም ባለቤትነት ሰነድ ጋር በተያያዘ ማጭበርበር የፈጸሙ ያሏቸው መለየታቸውን ተናግረዋል።
በወረራ የተያዙ ቦታዎች መታገዳቸውን፤ በወንጀል የተለዩትንም በቁጥጥር ስር ማዋል መጀመሩንም አመልክተዋል። ይኽም ብቻም አይደለም እሳቸው እንደተናገሩት ሀብታቸውን በትክክል ያላስመዘገቡ የመንግሥት ኃላፊዎችን ንብረት በተለይም ቤቶችን ማገድ መጀመሩንም አስታውቀዋል። እርምጃውም ተጠናክሮ ይቀጥላል ብለዋል። ብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ የሰጠውን መግለጫ የተከታተሉት የትራንስፓረንሲ ኢትዮጵያ የሥራ አስፈጻሚ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ካሣሁን እርምጃው ሙስና በሀገር እና በመንግሥት ላይ ያስከተለው ከባድ አደጋ ማሳያ ነው ይላሉ። ምንም እንኳን ስለሙስና ሲወራ ቢሰነብትም እርምጃዎች ባለመወሰዳቸው የድርጊቱ ፈጻሚዎች ሰንሰለት ተጠናክሮ ድርጊቱ ማኅበራዊ ነውር መሆኑ ወደ መቅረት መድረሱንም ነው ያመለከቱት። ሰባት አባላት ያሉት እና ከሳምንታት በፊት መቋቋሙ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ የተገለጸው የብሔራዊ ጸረ ሙስና ኮሚቴ በሙስና ተግባር የተዘፈቁ ያላቸውን ባለሥልጣናት በቁጥጥር ሥር ማዋሉን ከመግለጽ ባለፈ ስለብዛታቸው የተባለ ነገር የለም።
ሸዋዬ ለገሠ
እሸቴ በቀለ