በማህበረሰቡ እልባት የሚሻው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ግጭት
ሰኞ፣ ነሐሴ 12 2017
በማህበረሰቡ እልባት የሚሻው የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ግጭት
በኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን በተራዘመው የመንግስት የፀጥታ ሃይሎች እና አከባቢው ላይ በሸመቁ ታጣቂዎች መካከል የሚደረግ ግጭት መቋጫ አለማግኙ ከፍተኛ የማህበራዊ ቀውስ እያስከተሉ ነው ሲሉ የአከባቢው ማህበረሰብ አስታወቁ፡፡ ግጭቱ ከክልሉም ባሻገር አዋሳን ክልሎች ላይ አሉታዊ ተጽእኖ እያሳደረ ነው ተብሏል፡፡ ይህ በእንዲህ እዳለ በኦሮሚያ ክልል ሰሜን ሸዋ ዞን ከሙሎ ወረዳ በሚመለሱ የባንክ ሰራተኞች ሱሉልታ ወረዳ ውስጥ መገደላቸው ተነግሯል፡፡ የአዋሽ ወንዝ ሞልቶ ሺዎችን አፈናቀለ፤ ቤትና ሰብልም አጠፋ
የኦሮሚያ ክልል ደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አስተያየት ሰጪ በወረዳው ቶሌ፣ ቀርሳ ማሊማ፣ ሰደን ሶዶ እና በቾ ወረዳዎች ለሶስት-አራት ዓመታት የተራዘመው ግጭትና አለመረጋጋት ማህበረሰቡን በብዙ ዘርፍ መጉዳቱን ያስረዳሉ፡፡ አስተያየት ሰጪ ነዋሪዎች ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸውንና ማንነታቸውን ከመግለት ብቆጠቡም፤ በሰጡት አስተያየት ግን የአከባቢው ማህበረሰብ በተለይም በኢኮኖሚው መስተጋብር አስቸጋሪ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል፡፡ “ህዝቡ አሁን በኢኮኖሚው በሁለቱም ተፋላሚዎች ሽኩቻ ክፉኛ ተጎድቷል፡፡ በፊት ይሳለጥ የነበረው የከተማ ገጠር ትራንስፖርት እየተቋረጠ ገቢያውም እየቀዘቀዘ ሄዷል፡፡ ለመግለጽም እጅግ አስቸጋሪ የሆነ ሁኔታ ውስጥ ገብቷል ህዝቡ” ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ይህ በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን ወረዳዎች ውስጥ በአስከፊ ሁኔታ ይስተዋላል የተባለለት ግጭት አለመረጋጋቱ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በተለይም በምስራቅ ጉራጌ ዞን አዋሰኞች በርካታ ማህበራዊ ቀውሶች የአከባቢው ነዋሪዎች ላይ መደቀኑን የገለጹት ደግሞ ሌላው አስተያየት ሰጪ፤ “በኛ ቀጠና አሁንም ህዝቡ ሰላም እያገኘ አይደለም፤ ወደዚህ ወደ ጥያ፣ ታጣቂዎች ማታ ማታ እየመጡ ሰው እያገቱ በገጠራማው ወጣ እያሉ ደግሞ ሴቶች እየደፈሩ አስቸጋሪ ሁኔታ እየተስተዋለ ነውና ለምን በዚህ ሶስት አራት ዓመታት መንግስት ጸጥታ አላስከበረም የሚለው በሰፊው በማህበረሰቡ የሚነሳ ጥያቄ ነው” ሲሉ ለእልባቱ ተጣርተዋል፡፡በደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን እየከፋ የመጣው የንፁሃን ግድያ
መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በአከባቢው በምንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ላይ የምወስዳቸው ወታደራዊ እርምጃዎች እስካሁን ዘላቂ እልባት ሊያመጣ አልቻለም የሚሉት ሰላማዊና መፍትሄ ፈላጊ የአከባቢው ማህበረሰብ የሁሉም ወገኖች ተሳትፎ ያለበት ለህብረተሰቡ ሰላም ያደላ ሰላማዊ ንግግር መደረግ አለበትም ባይ ናቸው፡፡ “ወታደራዊ እርምጃዎቹ እስካሁን ምንም መፍትሄ አላመጣም” የሚሉት አስተያየት ሰጪ በመሃል ሰላማዊ ማህበረሰብ ጉዳት ማስተናገዱን ገልጸዋልም፡፡ የንጹኃን ግድያ፣ መፈናቀልና አፈና ብሎም የኢኮኖሚው ድቀት ከሚደርሱ አሉታዊ የግጭት ጫናዎች ዋነኞቹ መሆናቸውንም አስተያየት ሰጪው የአከባቢው ማህበረሰብ አባል አስረድተዋል፡፡ የማህበረሰቡ አሁናዊ እና አንገብጋቢ ፍላጎት ሰላም ብቻ ነው የሚሉት አስተያየት ሰጪ በአገር ውስጥ እና ከአገር ውጪ ያሉ ተጽእኖ ፈጣሪ ፖለቲከኞች በሙሉ ፍላጎታቸውን ስልጣን ላይ ሳይሆን በማህበረሰቡ ሰላምና እረፍት ላይ የቅድሚያ ትኩረት አድርገው መስራት እንዳለባቸውም ነው የተናገሩት፡፡ የኦሮሚያ ግጭት፡ የሰላማዊ ሰዎች ግድያ እና የሰላም ጥሪ
መንግስት በተለያዩ ጊዜያት በሚሰጣቸው መግለጫዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በተለያዩ አከባቢዎች በትጥቅ የምንቀሳቀሱ የታጠቁ አማጺያን በሰላማዊ መንገድ እጅ አየሰጡ አንጻራዊ ሰላምም እየሰፈነ ነው ይላል፡፡ ከሰሞኑም በዚህ የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ዞን አከባቢን በተመለከተ የአገር መከላከያ ሰራዊት በቶሌ ወረዳ የማዕከላዊ ዕዝ ክፍለጦር በወሰደው ወታደራዊ እርምጃ የነፍስ ወከፍ መሣሪያዎችን እና ተተኳሾችን በመማረክ “የሽብር ቡድን” ብሎ ከጠራቸው የታጠቁ አካላት የጦር መሳሪያዎችን መማረክ ጨምሮ ወታደራዊ ድል መቀናጀቱን በይፋዊው ማህበራዊ ገጹ አስታውቋል፡፡
ይህ በእንዲህ እንዳለ ባሳለፍነው ዓርብ በክልሉ በሰሜን ሸዋ ዞን ሙሎ ወረዳ የታጠቁ አካላት በደፈጣ መንገድ ላይ ጠብቀው ሶስት የባንክ ሰራተኞች ላይ እና እነሱን አጅበውአቸው በነበሩ የመንግስት ፀጥታ ሃይሎች ላይ ጥቃት መፈጸማቸውን ከአከባቢው ማህበረሰብ የአይን እማኞች ተረድተናል፡፡ “ሶስት የባንክ ሰራተኞች በመንግስት ጸጥታ አካላት ታጅበው ከሙሎ ወረዳ ከተማ ብር ተቀብለው ልመለሱ ሲሉ ነው ከጫንጮ አልፎ በምትገኘው አስቸጋሪ ቦታ በሸመቁ ታጣቂዎች ያለቁት” በማለት ስለደረሰው ጉዳት ገልጸዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ታምራት ዲንሳ