በማኅበረሰብ ተሳትፎ የአካባቢ ተፈጥሮዋን የምትጠብቀው ቡሩንዲ
ማክሰኞ፣ መስከረም 6 2018
ቡሩንዲ በመላው ሀገሪቱ የማኅበረሰብ ፕሮጀክቶችን ዘርግታ ተግባራዊ ስታደርግ ከ20 ዓመታት በላይ ሆኗታል። ሲጀመር የአካባቢ ጽዳትና የፍሳሽ ማስወገጃዎችን ማስተካከል ነበር፤ እየዋለ ሲያድር እነዚህ ፕሮጀክቶች ወደ አካባቢ ተፈጥሮ ጥበቃ እና ዘላቂነት ወዳለው ልማት አቅጣጫቸውን ለወጡ።
ማኅበረሰብን የሚያሳትፈው ሥራ
ከላይ እስከ ታች ያሉ ባለሥልጣናት ታዲያ ቀስበቀስ የልማት ፕሮጀክቶች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ማድረግ ችለዋል። ከእነዚህ ፕሮጀክቶች አንዱ ተዳፋት በሆኑ አካባቢዎች ችግኝ መትከል እና እርከን መሥራት ነው። ይህ ሥራ በየሳምንቱ ቅዳሜ በመላ ቡሩንዲ በአንዱም ቦታ ሳይቀር ሳይታጎል የሚከናወን የዜጎች ተግባር ሆኗል። ዜጎች ተሰባስበው ለበርካታ ሰዓታት ችግኞችን ይተክላሉ፤ እርከኖችን ይሠራሉ፤ ሸለቆዎችን ያጸዳሉ፣ ድልድዮችን፤ ትምህርት ቤቶችን፤ የጤና ማዕከላትንና የስፖርት ሜዳዎችንም ይገነባሉ፤ ያስተካክላሉ።
ይህ ማኅበረሰባዊ የጋራ ሥራ ከመጀመሩ በፊት መሬቱ በውኃና በንፋስ ስለሚጠረግ የሚገኘው ምርት በጣም ዝቅተኛ ነበር። በፕሮጀክቶቹ አማካኝነት ማኅበረሰቡ ስልጠና በማግኘቱ ሕዝቡ መሬቱን እንዴት በዘላቂነት መጠቀም እንደሚችል ለመማር በቅቷል።
ምንም እንኳን በሌላ አካባቢ ዕለተ ቅዳሜ የሳምንቱ ቀናት የመጨረሻ ቢሆንም በቡሩንዲ የተለየች ቀን ናት። በሚሊየኖች የሚቆጠሩ የሀገሪቱ ዜጎች በከተሞችና የገጠር አካባቢዎች በጋራ ለሥራ ይሰባሰባሉ። ይህ ማኅበረሰባዊ የጉልበት ሥራ ላለፌት 20 ዓመታት የዜግነት ግዴታ ሆኖ ቆይቷል።
በቡጁምቡራ ገጠራማ አካባቢ የሚገኘው የሳንግዌ የኅብረት ሥራ ማሕበር የግብርና እንቅስቃሴዎች ዘላቂነት እንዲኖራቸው ኅብረተሰቡን በማንቃት በኩል ጉልህ ሚና መጫወቱ ይነገርለታል። በዚህ ምክንያትም በአካባቢው ድኅነት እና የረሀብ ሁኔታ ቀንሷል። ቡኖንጉ ዠርሚ የሳንግዌ የሕብረት ሥራ ፕሬዝደንት ናቸው።
«የማኅበረሰባዊ ሥራ ጥቅሙ ምንድነው፤ በተመሳሳይ ጊዜ አንድ ሥራ ለመስራት በርካታ ሰዎችን ታገኛለህ፤ ይህ ማለት ደግሞ ሥራው ወዲያው ይከናወናል ማለት ነው። ሌላው ተጨማሪ አዎንታዊ ጠቀሜታው ደግሞ፤ ሰዎች ምን እንደሚሠሩ ለማስተማርና እዚያው ለማሳየትም ይጠቅማል፤ ይህ ደግሞ እነሱም በቀላሉ እንዲረዱት ይረዳቸዋል።»
የጋራ ሥራው ትሩፋቶች
የኅብረተሰቡ ጥረት ታዳያ አሁን ፍሬ አፍርቷል፤ የዚህ ፍሬ ተቋዳሽ ከሆኑት አንዱ በእርሻ እና ከብት እርባታ የሚተዳደረው ናኮሩቡሳ ዣን ማሪ ከቡጁምቡራ በስተ ምዕራብ 50 ኪሎሜትር ርቀት ገደማ የሚኖረው ኅብረተሰቡ የፕሮጀክቶቹን ጠቃሚነት መረዳቱን ይናገራል። ለዓመታት በሚኖርበት ቪያንጉ የተባለው ኮረብታማ መንደር ከአፈር መከላት ጋር ሲታገል ኖሯል።
አሁን በበጋ ወራት ለከብቶቻቸው መኖ ለመፈለግ ሩቅ ቦታ መጓዝ እንደማያስፈልጋቸው የሚናገረው ዣን ማሪ እርከን በጋራ በመገንባት ዛፎችን፤ በተከለሉ ቦታዎች ደግሞ ሣር እንዲተክሉ በመሰልጠናቸው አካባቢያቸው ከዓመት እስከ ዓመት አረንጓዴ መሆኑን ያስረዳል።
«ለእርከን ቦይ በምንቆፍርበት ቦታ የዝናብ ውኃ አፈሩን እንዳይሸረሽረው ለእንስሶቻችን ሣር እንተክላለን። በደረቅ ወቅት ታዲያ ይህ ሣር ለከብቶቻችን ምግብነት ይሆናል።»
ዣን ማሪ ትልቁ ስኬቱ ደግሞ በእርሻ ማሳው ላይ ነው።
«እርከን በየመካከሉ እንዴት መገንባት እንዳለብን ከመማራችን በፊት ዝናብ አብዛኛውን ሰብላችንን አጥቦ ይወስደው ነበር። ምክንያቱም የምናርሰው በቁልቁት ላይ ነው። አሁን ግን እንዲህ አይደለም። በፊት አንድ ቶን ድንች ነበር የማመርተው፤ አሁን ከሦስት ተኩል እስከ አራት ቶን አመርታለሁ።»
በምራባዊ ቡሩንዲ በሚገኘው የናይሩሻንጋ ኮረብታዎች ኅብረተሰቡ ወጥቶ እርከኖችን በመሥራት ላይ ነው። ውኃው ከከፍተኛው ስፍራ ወደታች አፈሩን እያጠበ እንዳያወስደው ከተፈጥሯዊው ሸለቆ ጎን ለጎን እርከኑ በአግባቡ ይገነባል። በየመሀሉ የሚገነባው እርከን ውኃውን በፍጥነት እንዳይወርድ ከመርዳቱ በተጨማሪ አፈሩ እንዳይከላ እና አካባቢው እርጥብ ሆኖ እንዲቆይ ይረዳል። ይህ ቀላል ስልት ታዲያ ኮረብታውን ከመጠበቁ በተጨማሪ መሬቱ ለም እንደሆን ያግዛል። ባለፉት ጊዜያት የኅብረተሰቡ የጋራ ሥራ የሕዝብ መሰብሰቢያ አካባቢዎችን በጽዳት ለመጠበቅ ያለመ ነበር። አሁን ደግሞ ስነምኅዳሩን በይበልጥ ለመንከባከብ አስችሏል። የናይሩሻንጋ ኮረብታዎች አካባቢ አስተዳዳሪ ሳቡሽሚክ አንሰንት፤
«ይህ የኅብረተሰብ ሥራ ለሕዝቡ በጣም ጠቃሚ ነው። ገና የሕብረት ሥራው ሠራተኞች እኛን ለመርዳት ሳይመጡ አስቀድመን፤ በተለይ ደግሞ በገላጣዎቹ ኮረብታዎች ላይ ዛፎችን በመትከል የአካባቢው ነዋሪዎች የተፈጥሮውን ይዞታ እንዲከባከቡ ግንዛቤ ለመፍጠር ተነስተን ነበር። እናም ያ ቀድሞውኑ ውጤት አስገኝቷል።»
በዋና ከተማ ቡጁምቡራ የወንዞች ዳርቻ የተተከሉት ቀርከሀዎች የማኅበረሰቡ የሕብረት ሥራ ውጤቶች ናቸው። ሥራቸው አፈሩን ስለሚይዝ አፈሩን በውኃው ከመጠረግ ያድናል። በዚያም ላይ እየተለወጠ የመጣውን የአየር ንብረት ለውጥ ተጽእኖ ለመቀነስ የሚረዳ አረንጓዴ መፍትሄ ነው።
ሳንግዌ፣ በጋራ ወይም በአንድነት
ወደ ናያሩሻንጋ ስንመለስ፤ ሳንግዌ ማለት በሀገሪቱ ቋንቋ በአንድነት ወይም በጋራ ማለት ነው። በጋራ መሥራት ብቻ ሳይሆን በጋራ ለሚቀጥለው የምርት ዘመን እቅድ ያወጣሉ። የተሻለ የድንች ዘር ያበቀሉ አርሶ አደሮች ያንን ምርት ተከፋፍለው በድጋሚ አፈር ውስጥ ይቀብራሉ፤ በዚህም በጋራ ጥሩ የድንች ምርት ይሰበስባሉ። በነገራችን ላይ እንዲህ ያለው የማኅበረሰብ የጋራ ሥራ ሁልጊዜም በፍላጎትና በፈቃደኝነት የሚሠራ ዓይነት አይደለም። ሁሉም ዜጋ በዚህ ደስተኛ ነው ሊባልም አይችልም ግን በጋራ ስኬቱ ሁሉም የሚጠቀምበት ስለሆነ ሁሉም እንዲሳተፍበት ይጠበቃል ይላሉ ሳቡሽሚክ አንሰንት።
«የየአካባቢውን ቡድኖች መሪዎች በመጠየቅ በማኅበረሰብ ሥራው ማን እንደተሳተፈና እንዳልተሳተፈ በቀላሉ ማወቅ እንችላለን። እያንዳንዱ በሥራው የተሳተፈ ግለሰብ ይመዘገባል። ያልተሳተፉት በመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ ይደርሳቸዋል። የማይሠሩ ከሆነ እገዳዎችን ጨምሮ ተገቢውን እርምጃ እንወስዳለን።»
ሴት አርሶ አደሯ ኮንቺሊ ማቦኒፓ እንዲህ ባለው የማኅበረሰብ የጋራ ሥራ በደስታ እንደምትሳተፍ ትናገራለች። እሷ እንደምትለው፤ ለአንዳንዶች የግዳጅና አድካሚ የሚመስለው ሥራ ለብዙዎቹ ትርጉም ያለውና ውጤቱም ለሀገር የሚተርፍ በጋራ የመሰባሰቢያ አጋጣሚ ነው።
«አንዳንዴ ሥራው ቀላል አይደለም። ነገር ግን ለየግልም ሆነ ለሀገር የሚኖረውን የሥራውን አላማ መረዳቱ ጥንካሬ ይሰጥሀል። በዚህ እርገጠኛ ያልሆኑት እንኳ ካልተሳተፉ ወደኋላ እንደሚቀሩ ይረዳሉ። በጋራ መሥራት መታደል ነው።»
ይህ ትብብር በሁሉም ዘርፍ ነው። ኅብረተሰቡ በየሚኖርበት አካባቢ በየሳምንቱ በጋራ ወጥቶ ለነዋሪዎች የሚጠቅሙሥራዎችን በትብብር ይሠራል። ከ20 ዓመታት በላይ ያስቆጠረው ይህ የማኅበረሰብ የጋራ የአካባቢ ተፈጥሮን የመከባከብ ሥራ ዜጎችን በሙሉ እያሳተፈ በዘላቂነት እንዲቀጥል ከተፈለገ በወር ሁለት ጊዜ ቢሆን የተሻለ ሊሆን እንደሚችል የሚናገሩ አሉ። በቡሩንዲ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ረሚ ማሪ ንኩሩንዚዛ ውጤታማነቱን ከፍ ለማድረግ እና ኅብረተሰቡንም ለማነሳሳት በየሳምንት ቅዳሜ የሚከናወነው መርኀግብር በወር ሁለት ጊዜ ቢደረግ የተሻለ ነው ባይ ናቸው።
«ሁሉም ሰው ይሰበሰባል፤ ሁሉም ሰው ቦታውን ለማሻሻል አስተዋፅኦ ያደርጋል። በዚሁ ከቀጠልን ስለወደፊቱ ጥርጣሬ የለኝም። ሆኖም ግን ለዚህ የኅብረተሰብ የጋራ ሥራ ግልጽ ግብ እና መመሪያ ማቅረብ አለበት። ካልሆነ ግን እንደታሰበው ላይሆን ይችላል።»
እንዲያም ሆኖ ግን አብዛኞቹ የቡሩንዲ ዜጎች በፊት በጎርፍ ውኃ ይታጠብ የነበረው የእርሻ ማሳቸው አሁን በተሠሩት እርከኖች አማካኝነት መትረፉ እንዳስደሰታቸው ነው የሚናገሩት። ዛሬ ኮረብታማው የቡሩንዲ መልክዓ ምድር አረንጓዴ ለብሷል፤ ጎርፉም ተገቷል። የወንዝ ዳርቻዎች በደን ልማት መልሰው በመለምለማቸው ለጎርፍ ተጋላጭ አካባቢዎች ጸድተዋል። ይህ ማኅበረሰባዊ የተፈጥሮ አካባቢን የመከባከብ የጋራ ሥራ ለሌሎችም በምሳሌነት የሚጠቀስ ሆኗል።
ሽዋዬ ለገሠ
ዮሐንስ ገብረእግዚአብሔር