1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ሳይንስአፍሪቃ

በማንጎ ተክል በሽታ ላይ የተደረገው ምርምር

ነጋሣ ደሳለኝ
ረቡዕ፣ ታኅሣሥ 8 2018

በአሶሳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተስተዋለ የሚገኘውን የማንጎ ተክል በሽታን ለማከም የተደረገው ጥናት ለውጥ ማስገኘቱን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል። ጥናቱ አብዛኛውን የገቢ ምንጫቸው በማንጎ ምርት ላይ ያደረጉት አርሶ አደሮችን ችግር እንደሚፈታ ተገልጿል፡፡

 የማንጎ ተክል በሽታን ለማከም የተደረገው ጥናት
በአሶሳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተስተዋለ የሚገኘውን የማንጎ ተክል በሽታን ለማከም የተደረገው ጥናት ለውጥ ማስገኘቱን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስታወቀ።ምስል፦ Negassa Dessalegn/DW

በማንጎ ተክል በሽታ ላይ የተደረገው ምርምር

This browser does not support the audio element.

 

በአሶሳ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በስፋት እየተስተዋለ የሚገኘውን የማንጎ ተክል በሽታን ለማከም የተደረገው ጥናት ለውጥ ማስገኘቱን የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ አስታውቋል። ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አጋሮች ጋር ለሁለት ዓመታት በተደረገው ጥናት በአሶሳ በሁለት ቦታዎች ላይ በሽታውን በማከም ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኒዎሎጅ ሽግግር ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ዶ/ር አብዱልሙሲን ሀሰን አመልክተዋል፡፡ ጥናቱ አብዛኛውን የገቢ ምንጫቸው በማንጎ ምርት ላይ ያደረጉት አርሶ አደሮችን ችግር እንደሚፈታም አክለዋል፡፡

የማንጎ ይዞታ

ኢትየጵያ በዘመናዊ ምርምር፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በእንስሳት፣ ዕጽዋት፣ በጤና እና አካባቢና በሌሎችም ዘርፎች ላይ በመስራት የሚታወቀው የባዮ እና ኢመርጅንግ ቴክኒዎሎጂ ኢንስትቲዩት የተባለ መንግሥታዊ ተቋም መረጃ እንደሚያመለክተው በኢትየጵያ ደረጃ የማንጎ በሽታ በቤንሻንጉል ጉሙዝ፣ በደቡብ ኢትዮጵያ ክፍልና ሌሎችም ቦታዎች ተስተውሏል፡፡ የአሶሳ ዩኒቨርሲቲም በሽታውን ለማከም ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አካላት ጋር ባደረገው ጥናት ለሙከራ በጀመራቸው ሁለት ስፍራዎች ላይ ለውጥ ማምጣቱን አስታውቋል፡፡

የማንጎ በሽታ ህክምና

ማንጎ በአሶሳ ከተማና አካባቢው በስፋት የሚገኝ ሲሆን ለበርካቶችም የገቢ ምንጭ ሆኖ ያገለግላል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ደግሞ አሶሳን ጨምሮ በተለያዩ የኢትዮጵያ አካባቢዎች በማንጎ ተከል ላይ በሚከሰቱ ተባዩች ይፈጥራል በተባለው በሽታ በማንጎ ምርት ላይ ጉዳት ማድረሱንና ምርቱ መቀነሱ ተገልጿል። አሶሳ ዩኒቨርሲቲ በማንጎ ላይ የተከሰተውን በሽታ ለማከም ያግዛል ያለው ጥናት ለሁለት ዓመት ያህል መደረጉን አመልክቷል።

በአሶሳ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና የቴክኒዎሎጅ ሽግግር ምክትል ፕሬዚደንት የሆኑት ዶ/ር አብዱልሙሲን ሀሰን፤ ከአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች አጋሮች ጋር ለሁለት ዓመታት በተደረገው ጥናት በአሶሳ በሁለት ቦታዎች ላይ በሽታውን በማከም ተጨባጭ ለውጥ መታየቱን ለዶቼ ቬለ ገልጸዋልምስል፦ Negassa Dessalegn/DW

በዩኒቨርሰቲው የምርምርና ሽግግር ምክትል ፕረዝደንት ዶ/ር አብዱልሙሲን ሀሰን ዋይት ማንጎ ሲከል የተባለው የማንጎ በሽታ በማንጎ ቅጠል ላይ የሚፈጠሩ ተባዮች በሚያስከትሉት በሽታ የማንጎ ቅጠል እንዲደርቅና ፍሬውንም በመምጠጥ እንዲበላሽ እና እንዲደርቅ በማድረግ ጉዳት እንደሚደርስ ይናገራሉ።

ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በኢትዮጵያ በሰምንት ክልሎች ማንጎ በስፋት ይገኛል። በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልልም በተለይም በአሶሳ እና አሶሳ ዞን ከፍተኛ መጠን ያለው ማንጎ የሚገኝ ሲሆን ዶ/ር አብዱል ሙሲን እንዳብራሩት 28 በመቶ የሚሆነው ማንጎ ምርት በአዲስ አበባ ለገበያ ይቀርባል። በተጨማሪም ማንጎን በዚህ አካባቢ ኅብረተሰቡም ለጥላ እና ልዩ ልዩ ሃይማኖታዊ ኩነቶችን በዛፉ በመጠለል እንደሚያከናውንም አመልክተዋል። በተክሉ ላይ የተደቀነው በሽታም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ምርቱን ከመቀነስ በተጨማሪም ማድረቅ መጀመሩን ተናግረዋል። ይህንን በሽታ ለመከላከል ከአዳማ ሳይንስና ቴክኒዎሎጂ ዩኒቨርሲቲና ሌሎች የዩኒቨርሲቲው አጋር አከላት ጋር በትብብር የተደረው ጥናት ውጤት ላይ ዩኒቨርሲቲው በቅርቡ በአሶሳ ምክክር አድርጓል።

‹‹በሁለት ቀበሌዎች ላይ ተግባራዊ ተደርጎ ውጤት ተገኝቷል››

የማንጎ ምርት በተለይም ከ2009 ዓ.ም ወዲህ በአሶሳ በማንጎ ተክል ላይ መታየት መጀመሩን የተገለጸ ሲሆን በሽታው በመስፋፋቱ ምክንያት ኑሯቸውን በምርቱ ላይ ያደረጉ በርካታ አርሶ አደሮችን ገቢ መቀነሱንም ተማልክቷል። ዶ/ር አብዱል ሙሲን እንደሚሉት በማንጎ በሽታ ላይ የተደረገው ጥናት በአሶሳ በሁለት ቦታዎች ተግባራዊ የተደረገ ሲሆን በሽታውንም ማከም መቻሉን አብራርተዋል። በአሶሳ ሁለት ቦታዎች በተደረገው ተግባራዊ ጥናት ባስገኘው ውጤትም በሽታው በተከሰተባቸው የክልሉ ሁሉም አካባቢዎች ከግብርና ምርምና ሌሎች የሚመለከታቸው አካላት ጋር በመተባበር እንደሚዳረስም አብራርተዋል።

በሽታው የማንጎ ምርት ከማሳነሱም በተጨማሪም ማንጎን የማጥፋት አቅም ያለው እንደሆነ በማውሳት በጥናቱ መሠረት በሁለት መንገድ በሽታውን ማከም እንደሚቻል ነው ባለሙያው የገለጹት። እነዚህን ሁለት መንገዶች በመጠቀምም በበሽታው የተያዙ ማንጎዎች እንዳገገሙና አዲስ የተተከሉትም በበሽታው አለመጠቃታቸውን አክለዋል።

የአሶሳ ዩኒቨርሲቲ ምስል፦ Negassa Dessalegn/DW

የሌሎች ሃገራት ተሞክሮ

በማንጎ ተክል ላይ የሚከሰተው ይህ ዋይት ማንጎ ሰኬል የተባለው በሽታ በተለያዩ አካባቢዎች መታየቱን የተናገሩት ዶ/ር አብዱሙሲን ሀሰን በጎረቤት ሀገር በኬኒያ ተከስቶ፤ በሽታውን ለማከም አዲስ የስነ ሕይወት ህክምና አሠራር ተግባራዊ መደረጉን አመልክተዋል። በ ኬኒያ ም ተግባራዊ የተደረገውን አሠራርም በኢትዮጵያ ባዩ እና ኢመርጂንግ ቴክኒዎሎጂ ኢንትስትቲዩት ከተባለው መንግሥታዊ ተቋም ጋር በመሆን ተግባራዊ ለማድረግ እንደሚሠሩ ገልጸዋል።

የማንጎ ተክል ላይ የሚስተዋለው ተባይ የሚያስከትለው በሽታ በተለያዩ ክልሎች ከ2009 ዓም ወዲህ በስፋት መታየት መጀመሩ ነው የተገለጸው። በአሶሳ የዋይት ማንጎ እስከል የተባለው በሽታ የአርሶ አደሩን ምርታማነት በእጅጉ ቀንሶ መቆየቱን የገለጹት ዶ/ር አብዱልሙሲን ሀሰን የምርምር ግኝቱ ለአርሶ አደሮችም የተግባር መፍትሄ እንደሆነ ተናግረዋል።

ነጋሳ ደሳለኝ

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW