በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የኤችአይቪ ሥርጭት አሳሳቢ ደረጃ ላይ ደርሷል ተባለ
ሰኞ፣ ሚያዝያ 6 2017
መቶ አለቃ ይሳቅ ታንጋ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ፣ የሲዳማ ፤ የደቡብ እና የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክልሎችን የሚሸፍነው የደቡባዊ ኢትዮጵያ ኤች አይ ቪ ፖዘቲቭ ማህበራት ጥምረት ዳይሬክተር ናቸው ፡፡ በአራቱ ክልሎች ብቻ በየዓመቱ ከ2 ሺህ በላይ አዳዲስ ሰዎች በኤች አይ ቪ ኤድስ አማጭው ተህዋሲ እየተያዙ እንደሚገኙ ለዶቼ ቬለ የተናገሩት የጥምረቱ ዳይሬክተር “ የተህዋሲው የሥርጭት መጠን የመጨመር አዝማሚያ እያሳየ ይገኛል ፡፡ አሁን ላይ በአራቱ ክልሎች ተህዋሲው በደማቸው የሚገኝባቸው 68 ሺህ 535 ሰዎች አሉ ፡፡ ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ 11 ነጥብ 4 በመቶ የሚሆን ነው “ ብለዋል ፡፡
ተህዋሲው ለምን ሊጨምር ቻለ ?
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ሆሳዕና ከተማ እየተካሄደ በሚገኘው የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል የንቅናቄ መድረክ በተህዋሲው መስፋፋትና አሳሳቢነቱ ላይ እየመከረ ይገኛል ፡፡ የመድረኩ ተሳታፊዎች “ በሽታውን አስመልክቶ ቀደምሲል ይደረጉ የነበሩ እንቅስቃሴዎች ተዳክመዋል ፣ ቸልተኝነትም በዛቷል “ የሚሉ ሀሳቦችን አንስተዋል ፡፡
በአማራ ክልል የኤች አይቪ ኤድስ ስርጭት መባባስ
በክልሉ ባለፉት ሰባት ወራት ብቻ በጤና ተቋማት ምርመራ ከተደረገላቸው ሰዎች መካከል ስድስት ነጥብ ሰባት በመቶ ያህሉ በደማቸው የበሽታው አማጭ ተህዋሲ እንደተገኘባቸው በክልሉ ጤና ቢሮ የኤች አይ ቪ ኤድስ መከላከል እና መቆጣጠር ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ አለምአየሁ ጌታቸው ለጋዜጠኞች ተናግረዋል ፡፡
በክልሉ በ38 የጤና ተቋማት 381 ሰዎች ምርመራ እንደተደረገላቸው የጠቀሱት አቶ አለማየሁ “ ከእነኝህ መካከል ስድስት ነጥብ ሰባት ሰዎች በደማቸው የበሽታው ተህዋሲ ተገኝቶባቸዋል ፡፡ ቁጥሩ የበሽታው ሥርጭት እያደገ መምጣቱን ያሳያል ፡፡ ይህም አሳሳቢ መሆኑን እና ከወዲሁ የመከላከል ሥራዎች መሠራት እንደሚገባ ጠቋሚ ነው “ ብለዋል ፡፡
አሃዛዊ መረጃዎች
በኢትዮጵያ በደማቸው የኤች አይ ቪ ተህዋስ ያለባቸው 605 ሺህ 238 ሰዎች እንደሚገኙ የአገሪቱ የጤና ጥበቃ ሚንስቴር እ.አ.አ በ2024 ዓም የነሐሴ ወር ላይ ያወጣው ሪፖርት ያመለክታል ፡፡ በአሁኑወቅት በየዓመቱ 7 ሺህ 428 ሰዎች በተህዋሲው እንደሚያዙና ከ10 ሺህ በላይ ሰዎች በዚሁ በሽታ ምክንያት ህይወታቸው እንደሚያልፍ በሪፖርቱ ተጠቅሷል ፡፡
ትግራይ፤ የ HIV ቫይረስ ስርጭት በእጥፍ ጨምሯል ተባለ
የፀረ ኤች አይ ቪ መድሃኒት አገልግሎት ላይ ከዋለበት ከፈረንጆች 2005 ጀምሮ ከፍተኛ ለውጥ መምጣቱን የጠቀሰው ሪፖርቱ 95 በመቶ ያህሉ ተህዋሲው በደማቸው የሚገኙ ሰዎች መድሃኒት እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ጠቁሟል ፡፡
ይህም በሰውነታቸው ውስጥ ያለው የቫይረሱ መጠን እንዲቀንስና ወደ ሌላ ሰው የማስተላለፍ እድላቸውም ዝቅተኛ እንዲሆን አስቸሏል ፡፡ ሚንስቴር መሥሪያቤቱ በፈረንጆች 2030 የኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ የማህበረሰብ የጤና ችግር ወደማይሆንበት ደረጃ ለማድረስ የተያዘው ግብ ለማሳካት እየተሠራ እንደሚገኝም ጠቅሷል፡፡
ዳግም አጀንዳ
የኤች አይ ቪ ኤድስ ወረርሽኝ ከፍተኛ ደረጃ ላይ በነበረበት ወቅት የነበረው የግንዛቤ ማስጨበጫ አሁን ላይ ግን የለም በሚባል ደረጃ መቀነሱን ነው የሚነገረው ። “ የቫይረሱ ሥርጭት ሳናውቀው ችግር ውስጥ እያስገባን ይገኛል “ ያሉትና በሆሳዕናው መድረክ ላይ ላይ የተገኙት የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በበኩላቸው “ ቀደምሲል ተጋላጭ ተብለው ከሚታሰቡት አካባቢዎች ውጭ በአዳዲስ ቦታዎች ጭምር የተህዋሲው ሥርጭት እየሰፋ ይገኛል ፡፡ ከታች ከትምህርት ቤቶች ጀምሮ የመከላከል ሥራዎችን በዕቅድ መሥራት ያስፈልገናል ፡፡ ጉዳዩን ዳግም ቀዳሚ አጀንዳ አድርገን መያዝ አለብን “ ብለዋል ፡፡
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
እሸቴ በቀለ
ዮሐንስ ገብረእግዚዓብሔር