በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ያልተፈታው የመምህራን የደሞዝ ጥያቄ
ሐሙስ፣ መስከረም 30 2017ያልተፈታው የመምህራን የደሞዝ ጥያቄ
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የሚገኙ መምህራን ከደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዞ የሚያነሷቸው ቅሬታዎች አሁንም ምላሽ አለማግኘታቸውን እየገለፁ ይገኛሉ ፡፡ በተለይም በክልሉ ሃድያ ዞን ደሞዝ በወቅቱ አይከፈልም ቢከፈልም እስከ ግማሽ ተቆራርጦ እንደሚደርሳቸው የጠቀሱት መምህራኑ በዚህም ለከፋ የኑሮ ችግር መዳረጋቸውን ተናግረዋል ፡፡
በሃድያ ዞን ምሥራቅ ባድዎቾ ወረዳ በሾኔ ከተማ በመምህርነት በማገልገል ላይ የሚገኙ አንድ አስተያየት ሰጪ “ እስከአሁን በ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ከነበረው ምንም የተለወጠ ነገር የለም ፡፡ ግማሾቻችን ከሦስት ወር ደሞዝ 55 በመቶ ሌሎች ደግሞ ከሁለት ወር ደሞዝ 60 በመቶ ተቆራርጦ እስከአሁን አልተከፈለም ፡፡ ክፍያው ባለመፈጸሙ የተነሳ በተለይ በሃድያ ዞን ከግል ትምህርት ቤቶች በስተቀር በአብዛኞቹ የመንግሥት ትምህርት ቤቶች የ2017 ዓ.ም ትምህርት አልተጀመረም “ ብለዋል ፡፡
የደሞዝ ጭማሪው «ሳይመጣ የሄደ ተስፋ» ወይስ ደጓሚ ?
“ ፕሮጀክት አቁማችሁም ቢሆን ደሞዝ ክፈሉ”
በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመምህራን የደሞዝ ጉዳይ የክልሉ ምክር ቤት ጉባዔን ጨምሮ በተለያዩ የስብሰባ መድረኮች ላይ በተደጋጋሚ በአጀንዳነት ሳይነሳ ያለፈበት ጊዜ የለም ፡፡ ምንምእንኳን እስከአሁን ዘላቂ መፍትሄ ባይገኝለትም ፡፡ ያም ሆኖ ከቀናት በፊት በክልሉ በተካሄደው የትምህርት ጉባዔ ላይ ጉዳዩ በድጋሚ ተነስቶ የክልሉ ባለሥልጣናት ምላሽ ሰጥተውበታል ፡ በደሞዝ ጉዳይ በየጊዜው ጭቅጭቅ ውስጥ መግባት የለብንም ያሉት የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እንዳሻው ጣሰው በጉባዔው ለታደሙ የዞንና የወረዳ ባለሥልጣናት ፕሮጀክት አቁማችሁም ቢሆን ደሞዝ ክፈሉ ብለዋቸዋል ፡፡
አማራጭ የገቢ ምንጭ ለመፈለግ የተገደዱት የዎላይታ መንግሥት ሠራተኞች
“ ሥለትምህርት ጥራት የምናስብ ከሆነ የመምህራንን ክፍያ ሳንፈጽም አይሆንም “ ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ ለምሳሌ አንድ ሦስት ዞኖች ያደረጋችሁት ጥረት ጥሩ ነው ፡፡ ነገር ግን አሁንም ቀሪ ውዝፎችን በሦስት ወራት ከፍላችሁ ማጠናቀቅ አለባችሁ ፡፡ ሌሎች የፕሮጀክት ሥራዎችን አቁማችሁም ቢሆን ክፍያው ፈጽሙ “ ብለዋል ፡፡
የማህበሩ ተስፋ
ከመምህራን የደሞዝ ክፍያ ጋር ተያይዘው የሚነሱ ቅሬታዎች እንዲፈቱ በተደጋጋሚ ከክልሉ መንግሥት ጋር ሲነጋገር መቆየቱን የክልሉ መምህራን ማህበር አስታውቋል ፡፡ የክልል ባለሥልጣናት ችግሩ እንዲፈታ በጉባዔው ተስፋ ሰጪ መመሪያ ማስተላለፋቸውን ለዶቹ ቬለ የተናገሩት የማህበሩ ፕሬዝዳንት በርታ ያረቢ “ ማህበሩ የሂደቱን ተፈጻሚነት ይከታተላል “ ብለዋል ፡፡
የቀድሞው የደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች ሕዝቦች ክልል በአራት የክልል መስተዳድሮች መደራጀቱን ተከትሎ በአስተዳደር መዋቅር መስፋትና ሲንከባለል በቆየው የእርሻ ማደባሪያ ዕዳ የተነሳ በተለይ የማዕከላዊ እና የደቡብ ኢትዮጵያ ክልሎች ለበጀት እጥረት መዳረጋቸው ይታወቃል ፡፡ ክልሎቹ ለመምህራንና ለሌሎች የመንግሥት ሠራተኞች ደሞዝ ለመክፈል በመቸገራቸው ሠራተኞች በየጊዜው አቤቱታቸውን እያሰሙ ይገኛሉ ፡፡
ፎቶ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የመንግሥት ጉዳዮች ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ
ሸዋንግዛው ወጋየሁ
ታምራት ዲንሳ
ኂሩት መለሰ