1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በማዳበሪያ እጥረት የገበሬው እሮሮ

ሐሙስ፣ ሰኔ 22 2015

በኦሮሚያ ክልል ዘንድሮ ባጋጠመው የማዳበሪያ እጥረት የዘር አዝመራ ወቅቱ እያለፈ በመሆኑ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡የክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች አርሶ አደሮች እንዳሉት፤ የተሰራጨው የማዳበሪያ መጠን ከሚፈለገው አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡መንግስት በበኩሉ አስፈላጊው የአፈር ማዳበሪያ መጠን በቅርቡ ይሰራጫል ባይ ነዉ

Zai in Mali
ምስል Chris Reij

ማደበሪያ ወደ ሐገር ቤት የገባ ነዉ-ግብርና ሚንስቴር

This browser does not support the audio element.

               
በኦሮሚያ ክልል በዘንድሮ የምርት ዘመን ባጋጠመው የማዳበሪያ እጥረት የዘር አዝመራ ወቅቱ እያለፈ በመሆኑ ስጋት ውስጥ መውደቃቸውን አርሶ አደሮች ገለጹ፡፡የክልሉ የተለያዩ አከባቢዎች አርሶ አደሮች እንዳሉት፤ የተሰራጨው የማዳበሪያ መጠን ከሚፈለገው አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡መንግስት በበኩሉ አስፈላጊው የአፈር ማዳበሪያ መጠን በቅርቡ ይሰራጫል ባይ ነዉ።ሥዩም ጌቱ
 “ዘንድሮ እንደ ወትሮም አላረስንም፡፡ ዝናብ እጅጉን በመብዛቱ እንደ ሌላው ጊዜ በስፋት ከማረስ አቅቦናል፡፡” ይህን ያሉት በኦሮሚያ ክልል በምርታማነቱ በሚታወቀው አርሲ ዞን ሌሙና ብልብሎ ወረዳ በቆጂ ዙሪያ ነዋሪነታቸውን ያደረጉ አርሶ አደር ናቸው፡፡ እንደ እኚህ አርሶ አደር አስተያየት የዝናብ ውሃ በመብዛቱ ጥቁር አፈርን አለስልሶ ለግብርና ስራ ማዘጋጀት ብከብድም ቀይ አፈር አከባቢ ያላቸውን ማሳ ግን አርሰው ለዘር ማዘጋጀታቸውን ነግረውናል፡፡ ይሁንና አሁን ላይ ለእሳቸው እና ሌሎችም አርሶ አደሮች የማዳበሪያ ጉዳይ ዘንድሮ አስጊ ነው ይላሉ፡፡
“ማዳበሪያ ትንሽ ገብቷል፡፡ ባለፈው ለእያንዳንዳችን 50 ኪ.ግ. ብቻ ነው የተዳረሰን፡፡ ይህ ከዚህ በፊት ከምንጠቀመው አንጻር እጅግ አነስተኛ ነው፡፡ ምናልባት ቶሎ መዘራት ላለበት ዘር ይሆን እንደሆነ ነው እንጂ አይበቃንም፡፡ ይህ እጥረት ዘንድሮ የተከሰተው የትም መሆኑን ነው እየሰማን ያለው፡፡ አሁን ይገባል ተብሎ በተስፋ እየጠበቅን ነው፡፡ ሰሞኑን በመኪና እየተጫነ ወደ ገደብ አሳሳ ሲያልፍም እያየን ነው፡፡ እኔ ዘንድሮ በዝናብ መብዛት ሁሉንም ማሳዬን አላረስኩም እንጂ እንደሉላ ጊዜ ብሆን እስከ 14 ኩንታል ማዳበሪያ በዓመት እተቀማለሁ፡፡” 
እንደ እኚህ አርሶ አደር አስተያየት በበጋ መስኖ ያረሱት ምርትም ከመጠን በላይ በጣለው የበልግ ዝናብ እንደ ሌላው ጊዜ ውጤታማ አላደረጋቸውም፡፡ “በበልግ ወቅትም ያረስነው ስንዴ ምንም ውጤታማ አላደረገንም ዘንድሮ፡፡ ዝናብ እስካሁን ባለማቋረጥ በመዝነቡና በመሃል ዘለቅ ለ ፀሃይ ባለማግኘታችን ይሄው ተበላሽቷል፡፡ በበልግ ወቅት እና አከባቢ በተሻለ የምንጠቀምበት ድንች ነበር፡፡ እሱን ተከልክለን ስንዴ ብንዘራም ከስረናል፡፡”
ሌላው ከምዕራብ ሸዋ ዞን አደዓ በርጋ ወረዳ አስተያየታቸው የሰጡን አርሶ አደር በዘንድሮ እርሻ ትልቁ ፈተናቸው የማዳበሪያ እጥረት መሆኑን አስረድተዋል፡፡ እንደ እሳቸውም አስተያየት በበቂ ሁኔታ የማይዳረሰው ማዳበሪያ የአዝመራ ወቅቱንም እያሳለፈባቸው ነው፡፡ “አሁን እኔ በነገው እለት ለመዝራት እቅድ ነበረኝ፡፡ ግን ማዳበሪያ አጥቼ ቁጭ ብያለሁ፡፡ ማዳበሪያ በቂ አይደለም፡፡ ከመጣ አንዳንድ 50 ኪሎ ይሰጠናል ከዚያን ሳይዳረስ ይቀራል፡፡ አሁን ከሁሉም ቀበሌ አርሶ አደሩ ተሰባስበው የወረዳ ከተማ እንጪኒ ላይ እየተጠባበቀ ነው፡፡ ከዚህ በፊት የዩሪያ እጥረት ነበር የሚያጋጥመን፡፡ አሁን ግን ዳፕ ጭምር ነው የጠፋው፡፡ ከዚህ ወደ ሆለታ ሄደን እንዳንገዛ በትራንስፖርት የሚያጓጉዝ ከተገኘ ይዘረፋል ተብሏል፡፡ ይሄው ማረስ መዝራት ሲገባን ተቀምጠናል፡፡”
ከዚህ በፊት በአማራ ክልልም አርሶ አደሮች ባጋጠማቸው የአፈር ማዳበሪያ እጥረት የግብርና ወቅቱ እያለፋቸው መሆኑን አማረው ማንሳታቸው በተደጋጋሚ መዘገቡ ይታወሳል፡፡
በ2015 ዓ.ም ከ1 ነጥብ 2 ሚሊየን ሜትሪክ ቶን በላይ የአፈር ማዳበሪያ ግዢ መፈጸሙን የሚገልጸው የኢትዮጵያ መንግሥት ግን ከዚህ ውስጥ ከ669 ሺህ ሜትሪክ ቶን በላይ ወደ አገር ውስጥ ማጓጓዙን ያስረዳል፡፡ ካለፈው ዓመት ከተረፈው 210 ሺህ ሜትሪክ ቶን ማዳበሪያ ጋር ተጨምሮ 879 ሺህ ሜትሪክ ቶን ገደማው ለግብርናው መቅረቡንም የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ትናንት ባወጣው መግለጫ አስረድቷል፡፡ ወደ አገር ውስጥ ከገባውና ከተጓጓዘው የአፈር ማዳበሪያ ውስጥ 842 ሺህ ሜትሪክ ቶኑ ለሕብረት ሥራ ማህበራት ስለመከፋፈሉን ተጠቁሟል፡፡ ወደ አርሶ አደሩ እጅ እንዲደርስ እየተደረገ ያለው የአፈር ማዳበሪያ መጠን ደግሞ 706 ሺህ ሜትሪክ ቶን መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
ማዳበሪያው የሚፈለግበት የእርሻ ወቅት ሳያልፍ ቅድሚያ ሊሰጣቸው የሚገቡ አካባቢዎችን በመለየት ማዳበሪያውን በፍጥነት ለማድረስ እየተሰራ መሆኑም ተነግሯል፡፡ በተጨማሪም የአፈር ማዳበሪያ ጭነው ጅቡቲ ወደብ ከደረሱት 13 መርከቦች መካከል፤ በ5 መርከቦች የተጫነው የአፈር ማዳበሪያ በቅርቡ መጓጓዝ እንደሚጀምርም ተጠቁሟል፡፡
በዚህ ላይ ለዶቼ ቬለ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት በግብርና ሚኒስቴር የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ስራ አስፈጻሚ አቶ ከበደ ላቀው፤ “ለዘንድሮ የምርት ዘመን የተገዛው ማዳበሪያ አሁን ላይ በጂቡቲ ወደብ ላይም የደረሰውን በፍጥነት በተለያዩ የየብስ ትራንስፖርት በማጓጓዝ ለክልሎች የማዳረስ ስራ እየተቀላጠፈ” ነው ብለዋል፡፡ ኃላፊው ክልሎች ባላቸው መዋቅር ኃላፊነትን ባሰፈነ መልኩ በአስቸኳይ የአፈር ማዳበሪያውን ለአርሶ አደሮች ተደራሽ እንዲያደርጉም ጠይቀዋል፡፡
የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን በትናንት መግለጫው፤ በማዳበሪያ ስርጭቱ ብልሹ አሰራር ያለባቸውና ተገቢው ግብአት ለአርሶ አደሩ እንዳይደርስ እንቅፋት የሆኑትን አካላት ተከታትሎ በቁጥጥር ስር የማዋል ተግባር መጀመሩን አሳውቋል፡፡

ምስል Prabhaka Mani Tewari/DW

ስዩም ጌቱ

ነጋሽ መሐመድ

ሸዋዬ ለገሰ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW