በማድመጥ መማር በዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ
ረቡዕ፣ ሰኔ 20 2004 ዶቼቬለ ባስተናገደው ዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ ከ1800 ለሚበልጡ ዓለም ዓቀፍ እንግዶች ስለ ትምህርትና ባህል ገለፃ በሚያደርግበት ወቅት የራሱን ዝግጅቶችም ማስተዋወቁ አልቀረም ። የዶቼቬለ የአፍጋኒስታንና የአፍሪቃ ክፍል ከብዙ ዓመታት አንስቶ በማድመጥ መማር የተሰኘ የትምህርት መርሃ ግብር ያዘጋጃሉ ። በዚህ ዝግጅት በአመዛኙ የሚቀርቡት አዝናኝ ና አስተማሪ የራድዮ ድራማዎች ናቸው ። ቦን የተካሄደው የዓለም ዓቀፍ የመገናና ብዙሃን መድረክ ተሳታፊዎች ይህን የራድዮ ድራማ በህብረት እንዲያዳምጡና እንዲገመግሙ ተደርጎ ነበር የዶቼቬለዋ ማያ ብራውን ስለዚሁ የዘገበችውን ሂሩት መለሰ አጠናቅራዋለች
አፍሪቃ ና አፍጋኒስታን የሚገኙ የዶቼቬለ ራድዮ አድማጮች በራድዮ ብቻ የሚያውቁት በማድመጥ መማር ለዓለም ዓቀፍ የመገናኛ ብዙሃን መድረክ ተሳታፊዎች በመድረክ ቲያትርነት ቀርቦ ነበር ። በክሪስፒን ምዋኪዲ የተፃፈውን ይህንኑ አጭር ቲያትር 4 የዶቼቬለ የአፍሪቃ ክፍል የፕሮግራም አዘጋጆች ነበሩ መድረክ ላይ የተወኑት ።
ተማሪዋ ገፀ ባህርይ ካሪምቦ መምህሮቿ ትምህርት ቤት ያስተማሯትን ደግማ ደጋግማ ለወላጆቿ ለማስተላለፍ ትሞክራለች ። እጅ መታጠብ ጠቃሚ መሆኑንና በሽታን ለመከላከል እንደሚረዳም እየነገረቻቸው ነበር ። በማድመጥ መማር ከዚህም በላይ በትምህርት ቤት የማይነገሩትና እና በቤት ውስጥም አይነኬ የሆኑ ጉዳዮች በማንሳት በተሳካ ሁኔታ መልዕክቱን ለአድማጮች ያስተላልፋል ። ቲያትሩን የተመለከቱት እንግዶች ባካሄዱት ውይይት በሰጡት አስተያየት በዚህ ይስማማሉ ። በኬንያ የመገናኛ ብዙሃን ጉዳዮች አማካሪ ኤሚ ቺርቺር ራሳቸውን በምሳሌነት አቅርበው ነበር ።
«ወላጆቼ ከሞላ ጎደል በደንብ የተማሩ ናቸው ። ይሁንና ስለ ወሲብም ሆነ ስለ ፖለቲካና የፖለቲካ ተሳትፎን ስለመሳሰሉ ጉዳዮች አንድም ቀን እንኳ ቁጭ አድርገው አነጋገረውኝ አያውቁም ። »
ይህን መሰሉ ሁኔታ አይነኬ ጉዳዮች በባዛት በሚገኙበት እንደ አፍጋኒስታን እና እንደ ሰሜን ናይጀሪያ በመሳሰሉ ማህበረሰቦች ይበልጥ ይዘወተራል ። የዶቼቬለ ራድዮ ዝግጅቶችን መልሶ የሚያሰራጨው የሰሜን ናይጀሪያው የፍሪደም ራድዮ ሃላፊ ፋሩክ ዳልሃቱ በማድመጥ መማርን እንደ ትልቅ ስኬት ነው የሚቆጥሩት ። የዚህም አንድ ምክንያት የዝግጅቱ አቀራረብ ነው ይላሉ ።
« በኛ አካባቢ ወሲብንም ሆነ የስነ ተዋልዶ ትምህርትን የተመለከቱ ጥያቄዎች በየትኛውም አቀራረብ ቢሆን ተቀባይነት የላቸውም ። ለልጃገረዶች የሚሰጥ ትምህርትም እንዲሁ ፤ የልጃገረዶችንና የህፃናትን ትምህርት የሚመለከቱ ጥያቄዎችም እንዲሁ አጠያያቂ ናቸው ። ሆኖም ይህ መርሃ ግብር ፤ ታስቦበት ጉዳዮቹን በደንብ አካቶ የተዘጋጀ በመሆኑ መልዕክቱ እነዚህን ስጋቶች የመሸፈን ኃይል አለው »
በአፍጋኒስታን በሚሰራጨው በማድመጥ መማር አስገድዶ መዳር ወይም የአደንዛዥ ዕፅ ዝውውርን ላይ የሚያተኩሩ ዝግጅቶች ላይ ጥሩ አስተያየቶች ይመጣሉ ። ከዶቼቬለ የአፍጋኒስታን ቋንቋ ክፍል አሪፍ ፋራህማንድ ለዝግጅት ክፍሉ በሚደርሱ ገንቢ አሰተያየቶች ደሰተኛ ነው ።
« የአፍጋኒስታን የትምህርት ሚኒስቴርና የባህል ሚኒስቴር የበማድመጥ መማር ዝግጅቶችን በማድነቅ የአፍጋኒስታን መገናኛ ብዙሃንም መሰል ዝግጅቶችን እንዲያቀርቡ ጠይቀዋል ። ይህ የተባለውም የአፍጋኒስታን መገናኛ ብዙሃን ከስርጭት ጊዜያቸው 2 በመቶውን ብቻ ለትምህርታዊ ዝግጅቶች መመደባቸውን መነሻ በማድረግ ነው ። »
በአፍጋኒስታን በመገናኛ ብዙሃን ብቻ ሳይሆን የአጠቃላይ የትምህርት ይዞታ በጣም አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል ። ለበርካታ አሥርት ዓመታት በአፍጋኒስታን ትምህርት ቤቶችን ሲገነቡ የቆዩት ኡርሱላ ኖለ እንደሚሉት ብዙውን ጊዜ ሴቶች ልጆች አይማሩም ። ለነዚህ መሰል ልጆችም ድርጅታቸው በየቤቱ እየተዘዋወረ ትምህርት ይሰጣል ።
« ቤት ውስጥ የሚማሩት ሴቶች ልጆች ብቻ ሳይሆኑ ትልልቅ ሴቶችም ናቸው ። ልጄ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት አጠናቋል እኔ ግን ስሜን እንኳን መፃፍ አልችልም ፤ ማንበብና መፃፍ እፈልጋለሁ የሚሉ የ49 ዓመት ሴቶችም ያጋጥሙናል ። »
የቲያትሯ ገፀ ባህርይ ካሬምቦ ግን መጨረሻው አምሮላታል ። ምንም እንኳን አባቷ ለስራ ቤት ውስጥ ሊቆዩዩዋት ቢፈልጉም ትምህርት ቤት ግን መሄድ ተፈቅዶላታል ።
ማያ ብራውን
ሂሩት መለሰ
ተክሌ የኋላ