1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በምርጫ ቅስቀሳ ተግዳሮት ገጠመን ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በደቡብ ወሎ ዞን

ኢሳያስ ገላው
ማክሰኞ፣ ሚያዝያ 27 2018

በ7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በደቡብ ወሎ ዞን የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ገዢው ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን በመጠቀም እያደረሰብን ያለው ተጽዕኖ እና በአካባቢው ያለው የጸጥታ ስጋት ለምርጫ ቅስቀሳ ሥራችን እንቅፋት ሆኖብናል አሉ። ፓርቲዎቹ ይህ የምርጫውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ የሚከተዉ ነዉ ብለዋል።

 የወሎ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ
የወሎ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ ምስል፦ Wollo Democratic Party (WDP)

ለምርጫ ቅስቀሳ ተግዳሮት ገጠመን ያሉ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በደቡብ ወሎ ዞን

This browser does not support the audio element.

በመጪው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ በደቡብ ወሎ ዞን የሚሳተፉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፤ ገዢው ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን በመጠቀም እያደረሰብን ያለው ተጽዕኖ እና በአካባቢው ያለው የጸጥታ ስጋት ለምርጫ ቅስቀሳ ሥራችን እንቅፋት ሆኖብናል አሉ። ፓርቲዎቹ በተለይ  የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከምርጫ ቦርድ መመሪያ ውጭ በፓርቲ ሥራ መጠመዳቸውና ዜጎችን በአስገዳጅነት የመመዝገብ ተግባር እየተከናወነ መሆኑ የምርጫውን ታማኝነት ጥያቄ ውስጥ እንደሚከተው ገልጸዋል። 

መጪው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ የሚሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች በደቡብ ወሎ ዞን የጸጥታ ችግር እና የገዢው ፓርቲ ተጽዕኖ ለምርጫ ስራቸው እንቅፋት መሆኑን ገለጹ። ለመጀመሪያ ጊዜ የሚሳተፈው ገዢው ፓርቲ የመንግሥት መዋቅርን በመጠቀም ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው ሲል የፓርቲው የደቡብ ወሎ ዞን ተጠሪ አቶ መሐመድ የሱፍ ይናገራሉ። 

‘’ ደቡብ ወሎንም ደሴ ከተማ አስተዳደርም የጋራ ምክር ቤት አለን። በጋራ ምክር ቤት አንስተን ገምግመነዋል። ለምሳሌ አንድ ለሦስት የሚሉት አደረጃጀት ነበረ ለካርድ ማውጣት የተጠቀሙበት። ነገር ግን አሁን ወደ ምዕራብ ወሎ አካባቢዎች የሆኑ ተግዳሮቶች አሉ።’’  

በሌላ በኩልም የደቡብ ወሎ ዞን የፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ሰብሳቢና የኢዜማ የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ የሆኑት ሻምበል ደምሌ ተረፈ፤ አሁን ያለው የቅድመ ምርጫ ሂደት እንከን ያለበት መሆኑን ገልጸው ገዢው ፓርቲ ከካርድ ማውጣት ጊዜ ጀምሮ እስካሁን ድረስ ሰዎችን በአስገዳጅነት እየመዘገበ ነው ይላሉ። 

‘’ ገዢው ፓርቲ በየቤቱ እየገባ ነው የሚቀሰቅሰው። አሁን ራሱ እኮ የምርጫ ካርድ ካለቀ በኋላ በየቤቱ እየተዞረ እየተመዘገበ ነው። ምዝገባው ምን አስፈለገ? እኛ ዝም ያልነው አቅም ስላጣን ነው። በየቤቱ እየተገባ የምርጫ አሁን ቅስቀሳ ነው እንጂ በየቤቱ እየገባህ ስም ዝርዝር አትወስድም። ያ ማለት ምርጫውን ታማኝነት ያሳጣዋል ማለት ነው።’’ 

ደቡብ ወሎ ምስል፦ Wollo Democratic Party (WDP)

አሁን ያለው የጸጥታ ሁኔታ በተወሰነ መልኩ መሻሻል የታየበት ነው የሚሉት የወሎ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ተጠሪ አቶ መሐመድ የሱፍ እንደ መቅደላ ባሉ ወረዳዎች ግን ገዢው ፓርቲ ስህተቶችን እየፈጸመ መሆኑን ይናገራሉ። ‘’ ከታጠቀው ኃይልም ያው ማስጠንቀቂያ ነበረ ከዚህ ቀደም። እሱን የጸጥታ ኃይሉ ሥራ ሰርቷል ይመስለኛል። ብዙም አስተማማኝም ባይባልም ሃምሳ ሃምሳ አሁን ማለት። ነገር ግን ውስጥ ያለው ገዢው መንግሥት የሚሰራቸው ስህተቶች አሉ። አሁን ምዕራብ ወረዳ ላይ  እኔ ምዕራብ ወረዳ ነው የምወዳደረው አሁን። መቅደላ ወረዳ ላይ እዛ ላይ የተሰሩ ስህተቶች አሉ። እሱን አሁን ቀጣይ እሁድ በጋራ ምክር ቤት ልናነሳቸው ቀጠሮ ይዘናል። 

የመንግሥትና የፓርቲ ስራዎችን ለይቶ ማስኬድ አልተቻለም የሚሉት ሻምበል ደምሌ ተረፈ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ከምርጫ ቦርድ መመሪያ ውጭ በፓርቲ ስራ መጠመዳቸው የሕዝብን አገልግሎት መስጠት እንዲያቆሙ አድርጓቸዋል ይላሉ። ከሥራ ውጭ መሆን አለበት የሚለውን ምርጫ ቦርድ ከሥራ ውጭ ሆኖ ስራውን መስራት አለበት የሚለው ተወዳዳሪው ብቻ ነው። ዕጩው። ሦስት ወር ፈቃድ አለው። ከእሱ የዓመታዊ ፈቃድ ውጭ ሦስት ወር አራት ወር ፈቃድ አለው። ያ አካል ብቻ ነው ወጥቶ ስራ መስራት ያለበት። አሁን ግን የመንግሥት መሥሪያ ቤቶች ላይ ሹማምንቶች፣ የጽሕፈት ቤት ኃላፊዎች፣ አባላት በተለያየ መንገድ ገብተው ማህበረሰቡ ውስጥ ተሰብስበው ስራ እየሰሩ ነው። ምን እንደሚሰሩ አናውቅም። ምርጫው መጨረሻ ላይ ምን ይሆናል ደግሞ አብረን እናየዋለን።’’ 

ከካርድ አወጣጥ ጀምሮ ያየናቸው ችግሮች አሉ የሚሉት የወሎ ዲሞክራሲያዊ ፓርቲ የደቡብ ተጠሪ የቅድመ ምርጫ ሂደቱ አንዳንድ ተግዳሮቶችን እያስተናገደ ነው ይላሉ። ‘’ ምርጫው መጨረሻው ይታይ። አሁን ካርድ አወጣጡ ያው ችግር አለ እኮ። ብዙ ነጥብ የያዝናቸው ችግሮች አሉ። ምርጫው በተለያዩ ነገሮች ውስጥ ችግር አለ። እንግዲህ ያው እንደበፊቱም አሁን ኮሮጆ ግልበጣ ምናምን ይመጣል ብዬ አላስብም እና ጠንካራ ታዛቢዎችን እዛ እናስቀምጣለን እኛ። ከላይም የፌደራል መንግሥቱ አሁን የዛ አይነት አመለካከት አለው ብዬ አላምንም። ያው መንግሥታቶች ይለያያሉ።’’ 

ደቡብ ወሎ -የምርጫ ቅስቀሳ ምስል፦ Wollo Democratic Party (WDP)

አሁን ላይ በደቡብ ወሎ ዞን የምርጫ ሂደቱ አስቸጋሪ ያልሆነባቸው ቦታዎች ቢኖሩም አብዛኞቹ አካባቢዎች ግን ምርጫ ለመከወን የሚያስችሉ መሆናቸውን ነው ሻምበል ደምሌ ተረፈ የሚገልጹት። ‘’ አስቸጋሪ በሆነ ቦታ ላይ ምርጫ የለም። ለምሳሌ ልጥቀስልህ  ደላንታ ምርጫ አለ። በእርግጥ ወጣ ገባ ነው። ግን ለምርጫ የሚያስቸግራቸው ነገር የለም። ምዕራብ ወረዳ ስትሄድ አሁን መቅደላ ላይ ችግር አለ። ማሻ በተለይ ይገባሉ ይወጣሉ። ምርጫውም ካርድ እንዴት ተመረጠ፣ እንዴት ተያዘ የሚለውም አጠራጣሪ ነው የሚሆነው። ቃሉ ሁለት ቃሉ አንድ እና ቃሉ ሁለት ወይንም አምባ አካባቢ ላይ ክትትል እያደረግን ነው። ግን ደግሞ ካርዱ እንዴት ብሎ ተመዘገቡ? እንዴት ብሎ ወጡ? ያስቸገረበት መረጃ የለም። ይሄ መረጃ የሚያውቀው ማነው? ምርጫ ቦርድ እና ገዢው ፓርቲ ናቸው። መንግሥት የተቆጣጠራቸው ቦታ ላይ ምርጫ አለ ብለን ነው የምናስበው።’’ በደቡብ ወሎ ዞን በሚንቀሳቀሱ የተፎካካሪ ፓርቲዎች ቅሬታ ዙሪያ ሀሳብ እንዲሰጡን በአማራ ክልል የብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊን ለማግኘት ያደረግነው ጥረት አልተሳካም።

ኢሳያስ ገላዉ 

አዜብ ታደሰ 

ሸዋዬ ለገሠ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW