1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምስራቅ ወለጋ የታጣቂዎች ጥቃት

ዓርብ፣ ሰኔ 9 2015

በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ትናንት ከማለዳ ጀምሮ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ንብረት ላይም ጉዳት ማድረሳቸውን እና የቁም እንስሳት መዝረፋቸውንም ያነጋገርናቸው የኪረሙ ወረዳ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡

Äthiopien | Straßenszene in Mendi
ምስል Negassa Deslagen/DW

በጥቃቱ 8 ሰዎች ተገድለዋል፤ 13 ሰዎች ላይ ደግሞ ቆስለዋል

This browser does not support the audio element.

በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ውስጥ ትናንት ከማለዳ ጀምሮ  ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት የስምንት ሰዎች ህይወት ማለፉን ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡ ታጣቂዎቹ ንብረት ላይም ጉዳት ማድረሳቸውን እና የቁም እንስሳት መዝረፋቸውንም ያነጋገርናቸው የኪረሙ ወረዳ ነዋሪዎች ገልጸዋል፡፡  የምስራቅ ወለጋ ዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ጽ/ቤት ኃላፊ ኮሎኔል ለሜሳ ደሬሳ በኪረሙ ወረዳ ጽንፈኛ ያሏቸው ሀይሎች ጉዳት ማድረሳቸውን በስልክ ተናግረዋል፡፡ የኪረሙ ወረዳ ኮሙኒኬሽን በማህራዊ መገናኛ ዜደው እንደጠቀሰው በደረሰው ጥቃት የ8 ሰዎች ህይወት ማለፉንና 13 ሰዎች ላይ ደግሞ የመቁሰል አደጋ መድረሱን አመልክተዋል፡፡

የጸጥታ ችግር በተደጋጋሚ በተከሰተባቸው የምስራቅ ወለጋ ዞን  እና  የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ውስጥ በተለያየ ስም በሚንቀሰቃሴ ታጣቂዎች የሚደርሰው ጥቃት ትኩረት እንደሚሻ ከዚህ ቀደም የሰብአዊ መብቶች ተቋማት ሲያሳስቡ ቆይተዋል፡፡ በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ዋስት በተባለች አንድ የገጠር ቀበሌ ውስጥ ትናንት የታጣቁ ሐይሎች በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት ማድረሳቸውም ተገልጸዋል፡፡ በመቶዎች የሚቆጠሩ የቁም እንስሳት መዝረፋቸውን አቶ ኦሊ ጃርሶ የተባሉ የአካባቢው ነዋሪ ተናግረዋል፡፡ ትናንት  ማለዳ 12፡00 ሰዓት ገደማ በተለያዩ አቅጣጫ ወደ መንደር በመግባት ጥቃት በማድረስ ዝርፍያ መፈጸማቸውን አብራርተዋል፡፡

" በሶስት አቅጣጫ በማለዳ 12 ሰዓት  ላይ ተኩስ ሲከፍቱ በአካባቢው ያሉት የታጠቁ ሚሊሻዎችና ህዝቡ ራሳቸውን ለመከላከል ሞከሩ ሌሎች ደግሞ ሸሹ፡፡ 8 ሰዎች ህይወታቸው አልፈዋል፡፡ ብዙ ሰዎች ቆስለዋል፣ ከብቶችም ተወስደዋል፡፡ በበአባይ በረሃና በዋስት ቀበሌ አዋሳኝ ቦታዎች ጥቃት እየደረሰ ነው፡፡ የጸጥታው ሁኔታ በጣም አስጊ ነው፡፡  "

ትናንት በኪረሙ በደረሰው ጥቃት ህይወታቸው ያለፈው ሰዎች ያልታጠቁ እና በግብርና ስራ የሚተዳደሩ ሰዎች እንደሆኑ ሌላው ነዋሪ ለዲዳቢሊው ተናግረዋል፡፡ 15 በሚደርሱ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱንና የጠፉ ሰዎችም እየተፈለጉ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡ ጉዳት ከደረሰባቸው ሰዎች መካከል አንዱ ወደ ጊዳ አያና ወረዳ ውስጥ በሚገኘው ጤና ጣቢያ ለህክምና መላካቸውንም ጠቁመዋል፡፡

የምስራቅ ወለጋ ዞን የአስተዳደርና ጸጥታ ጽ/ቤት በበኩሉ በኪረሙ ወረዳ  የታጠቁ ጽንፈኛ  ሀይሎች ጉዳት ማድረሳቸውን አመልክተዋል፡፡ የጽ/ቤቱ ኃላፊ ኮሎኔል ለሜሳ ደሬሳ በኪረሙ ወረዳ ዋስቲ በተባለ ቀበሌ ውስጥ ጥቃት መድረሱን ተከትሎ  የመንግስት ጸጥታ ሐይሎች ወደ ስፋራው መሰማራታቸውን ለዶቼቬለ ተናግረዋል፡፡ በሰው እና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱን ያረጋገጡ ሲሆን የጉዳት መጠኑ ወደ ስፍራው የተሰማራው የጸጥታ ሐይል በኩል ተመዝግቦ ሲጠናቀቅ እንደሚገልጹ አመልክተዋል፡፡

"በኪረሙ ወረዳ በረሃ  ዋስቲ በሚባል ቀበሌ ውስጥ የታጣቁ ጽንፈኛ ሀይሎች በሰላማዊ ሰዎች ላይ ተኩስ መክፍታቸውና ጉዳት መድረሱን ሪፖርት አለን፡፡ በሰው ህይወት እና ንብረት ላይ የደረሰውን የጉዳት መጠን እየተጣራ ነው፡፡ ከብት መዝረፍና መንዳት አልፎ አልፎ ይስተዋል ነበር፡፡ አሁን ግን በተደራጀና በተጠናከረ መልኩ ጉዳት መድረሱን መረጃ ደርሶናል፡፡ " 

በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ እና በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ አሙሩ የተባሉ ወረዳዎች ውስጥ ለረጅም ጊዜ በቆየው የጸጥታ ችግር ሳቢያ የሰው ህይወት መጥፋትን ጨምሮ ከ63ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው ቆይተዋል፡፡ በኪረሙ ወረዳ አጎራባች በሆነው አሙሩ ወረዳ በተመሳሳይ ባለፈው ሳምንት ረቡዕ እና ሐሙስ በታጣቂዎች በደረሰው ጥቃት ወደ አምስት ሰዎች ህይወት ማለፉ ተዘግበዋል፡፡

ነጋሳ ደሳለኝ

አዜብ ታደሰ

ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW