1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምስራቅ ወለጋ ጉትን ከተማና አካባቢው የጸጥታ ችግር

ረቡዕ፣ ኅዳር 21 2015

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ጉትን ከተማና አካባቢው በተከሰተ የፀጥታ ችግር የሰው ሕይወት መጥፋቱ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ቀዬአቸውን መልቀቃቸው ተገለጠ። የጉትን አጎራባች በሆነው በኪረሙ ወረዳም ትናንት ከጠዋት 2፡00 ሰዓት ገደማ አንስቶ በነበረው ከፍተኛ ተኩስ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ሰው መጎዳቱንና ቤቶችም መቃጠላቸውን ከስፍራው ለመረዳት ተችሏል።

Äthiopien Vertriebene aus Wollega in Bahir Dar angekommen | Hauptstadt der Amhara-Region
ምስል Alemnew Mekonnen/DW

ግድያ እና ማፈናቀሉ ቀጥሏል

This browser does not support the audio element.

በኦሮሚያ ክልል ምስራቅ ወለጋ ጉትን በሚባል ከተማና አካባቢው በተከሰተ የፀጥታ ችግር የተነሳ ሕይወት መጥፋቱ እና በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች ቀዬአቸውን መልቀቃቸው ተገለጠ። አንድ የሕግ ባለሞያና የልዩ ኃይል አባላትን ጨምሮ የ11 ሰዎች ሕይወት ማለፉንም ነዋሪዎች ተናግረዋል። የጉትን አጎራባች በሆነው በኪረሙ ወረዳም ትናንት ከጠዋት 2፡00 ሰዓት ገደማ አንስቶ በነበረው ከፍተኛ ተኩስ ቁጥሩ በውል ያልታወቀ ሰው መጎዳቱንና ቤቶችም መቃጠላቸውን ከስፍራው ለመረዳት ተችሏል። በጉዳዩ ላይ ከምስራቅ ወለጋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ እና ከክልሉ ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት ማብራሪያ ለማግኘት የተደረገው ጥረት ስልክ ባለመነሳቱ አልተሳካም። 

በሰላም እጦት ምክንያት በወለጋ ዞኖች ከ7 መቶ ሺ በላይ ሕዝብ ከቤት ንብረቱ ተፈናቅሎ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚገኝ የተባበሩት መንግስታት የሰብአዊ ጉዳዩች ማስተባበሪያ ጽ/ቤት (UNOCHA) በቅርቡ ባወጣው ዘገባው አመልክቷል። ከጥቅምት ወር መጀመሪያ አንስቶ ከአራት ጊዜ በላይ ጥቃቶች የደረሱባት የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳና ጉትን ከተማ አሁንም በአካባቢው በሚስተዋለው የሰላም መደፍረስና በስጋት ምክንያት ወደ ሌላ ከተማ እየሸሹ እንደሚገኙ አስተያየታቸውን የሰጡን ነዋሪዎች ጠቁመዋል። በጉትን ከባለፈው ሳምንት አርብ ኅዳር 16 ቀን፣ 2015 ዓ.ም ጀምሮ በሺ የሚቆጠሩ ነዋሪዎች ከቤት ንብረታቸው መፈናቀላቸውን አብራርተዋል። በአካባቢው ለሚደረሱት ጉዳቶች በሸኔ ስም የሚንቀሳቀሱ ኃይሎችን ተጠያቂ አድርገዋል።
እልባት ያላገኘው የምስራቅ ወለጋው ኪረሙ ወረዳ አለመረጋጋት

የወለጋ ተፈናቃዮች በባሕር ዳር ከተማምስል Alemnew Mekonnen/DW

ከ52ሺ በላይ የተፈናቀሉ ሰዎች የሚገኙባት የምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ በትናትናው ዕለት ጠዋት በጀመረ ተኩስ በሰውና ንብረት ላይ ጉዳት መድረሱ ተገልጿል። በወረዳው ከተማ የንግድና መኖሪያ ቤቶች መውደማቸውን እንዲሁም ጀነረተሮችና የተለያዩ ቁሳቁሶች መዘረፋቸውን ነዋሪዎች ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል። በትናንቱ ግጭት አምስት የፀጥታ ኃይሎች ሕይወት ማለፉን አንድ ነዋሪ የነገሩን ሲሆን፤ ሌላው ነዋሪ ደግሞ የልዩ ኃይልን ጨምሮ 11 ሰዎች ሕይወት ማለፉን ማየታቸውን አብራርተዋል።

«ከጠዋት ጀምሮ ቤት እያቃጠሉ ነው፡፡ የታጠቁ ጽንፈኛ ኃይሎች ናቸው ወደ ከተማ ገብተው ተኩስ የከፈቱት፡፡ ታጣቂዎቹ ለሁለተኛ ጊዜ ነው ወደ ከተማው ገብተው ጥቃት ያደረሱት ልዩ ኃይልን ጨምሮ 11 ሰዎች ሞተዋል፡፡ የተወሰኑ ልዩ ኃይሎች ነበሩ ነገር ግን ከአቅማቸው በላይ ነው፡፡ በወረዳው ውስጥ ከሚገኙት 19 ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ የተፈናቀሉ ሰዎች በወረዳው ከተማ ነው ተጠልለው የሚገኙት።»

የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ተፈናቃዮች በሻምቡ ዩኒቨርሲቲምስል Seyoum Getu/DW

የተፈናቃዮች ሮሮ ከኪረሙ ወረዳ

ስለ ጉዳዩ የሚያውቁት ካለ ማብራሪያ እንዲሰጡን የጠየቅናቸው በኢትዮጵያ ሰብአዊ መብቶች ኮሚሽን የኦሮሚያን ጉዳይ እየተከታተሉ የሚገኙት አቶ ኢማድ አብዱልፈታ ተቋሙ ጉዳዩን እየተከታተለ እንደሚገኝና በቅርብ በዝርዝር መረጃ ይፋ እንደሚያደርግ ተናግረዋል፡፡ ኪረሙ ወረዳ በተደጋጋሚ ጥቃት የደረሰባት ከተማ ስትሆን፤ በወረዳዋ የሚኖሩ የአማራ እና የአሮሞ ተወላጆች በሚደርሱት ጉዳቶች የሸኔ ታጣቂዎችና ጽንፈኛ ፋኖ ያሉትን ቡድን ይወነጅላሉ። በአካባቢው በማኅበረሰቡ ላይ የሚደርሱት ጥቃቶች ለማስቆም የተወሰደ ርምጃ አለመኖሩን የጥቃቱ ሰለባ የሆኑ ነዋሪዎች ይናገራሉ።

ነጋሣ ደሳለኝ

ማንተጋፍቶት ስለሺ

እሸቴ በቀለ
 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW