1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ኦሮሚያ የቀጠለው የታጣቂዎች ጥቃት ግድያ ማባባሱ

ሰኞ፣ መስከረም 16 2015

ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የነዋሪዎችን ህይወት የቀጠፈውና በታጣቂዎች ተፈጸመ የተባለው ጥቃት ተባብሶ አሁን ደግሞ በዞኑ የአሙሩ ወረዳ እና በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ተስፋፍቶ ጉዳት ማድረሱ እየተነገረ ነው፡፡

Äthiopien | Wahlen | Oromia

በሆሮ ጉዱሩ ታጣቂዎች ባደረሱት ጥቃት ተጎጂዎች አወዛጋቢ አስተያየት ሰጥተዋል

This browser does not support the audio element.

በምእራብ ኦሮሚያ ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን እና በአከባቢው ወረዳዎች በቀጠለው የፀጥታ ችግር ነዋሪዎች አሁንም እያማረሩ ነው፡፡

ባለፈው ሳምንት በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ የነዋሪዎችን ህይወት የቀጠፈውና በታጣቂዎች ተፈጸመ የተባለው ጥቃት ተባብሶ አሁን ደግሞ በዞኑ የአሙሩ ወረዳ እና በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ተስፋፍቶ ጉዳት ማድረሱ እየተነገረ ነው፡፡

በትናንትናው እለትም መስከረም 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ከማለዳ ጀምሮ በአሙሩ ወረዳ ጎቡ ሲርባ ቀበሌ ታጣቂዎች በሲቪል ዞጎች ላይ አነጣጥሮ በጅምላው በወሰዱት ጥቃት እስካሁን ቢያንስ ከ40 ሰው በላይ መገደላቸውን የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ገልጸዋል፡፡

ጥቃቱን ባደረሱ የታጣቂዎቹ ማንነት ላይ ግን የአከባቢው ነዋሪዎች እየተወዛገቡ ነው፡፡

ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ሀሮ በተባለች ቀበሌ ነዋሪነታቸውን ያደረጉትና ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈቀዱ አስተያየት ሰጪ ትናንት ማለዳውን በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ ጎቡ በተባለች ስፍራ ንጹሃን ዜጎች ላይ አነጣጥሮ ተወስዷል ባሉት ጥቃት ቢያንስ 5 ሰዎች ተገድለው 10 ያህሉ ተጎድተዋል ይላሉ፡፡ እኚ አስተያየት ሰጪ ጥቃቱን ያደረሱ ታጣቂዎች ማንነት “ኦነግ ሸነ” ሲሉ ሲገልጹ፤ የጥቃቱ ሰለባዎች ደግሞ በአከባቢው ለዘመናት የኖሩ የአማራ ብሔር ተወላጆች መሆናቸውን በስም ጠቅሰው አብራርተዋል፡፡

የትናንት ማለዳው ጥቃት የተፈጸመበት ጎቡ ሲርባ የተባለች ቀበሌ በቅርቡ ነሓሴ 23 እና 24 ቀን 2014 ዓ.ም. ታጣቂዎች ከ60 በላይ ንጹሃን ዜጎችን ከገደሉበት አሙሩ ወረዳ አገምሳ ከተማ 10 ኪ.ሜ. ገደማ ብቻ እንደምትርቅ በአከባቢው ነዋሪዎች ይነገራል፡፡ ይህ አካባቢ ከኪረሙ ወረዳ ጋር የሚዋሰንና ሀሮ ከተባለች ቀበሌም ከ10 ኪ.ሜ. ባልበለጠ ርቀት ላይ ነው ሚገኘው፡፡

ስለ ትናንት ጠዋቱ የጎቡ ጥቃት በአሙሩ ወረዳ በኩል የአከባቢው ነዋሪ መሆናቸውን ገልጸው አየሁ ያሉትን ያጋሩን ነዋሪ ደግሞ ቀደም ብለው ስለክስተቱ ከነገሩን የኪረሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ ነዋሪ የተለየ አስተያየት ነው ያጋሩን፡፡ ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ከመግለጽ የተቆጠቡት እኚህም ነዋሪ፤ የጥቃቱን አድራሾች የአማራ ብሔር ታጣቂዎች ሲሉ ነው የገለጹት፡፡ ትናንት ከማለዳው 3፡00 ጀምሮ እስከ አመሻሽ 11፡30 ዘልቋል ባሉት የጎቡ ጥቃትም የ90 ዓመት አዛውንት ጭምር የሚገኙበት በትንሽ ግምት ከ35 በላይ ሰላማዊ ዜጎች ተገድለዋል ነው የሚሉት፡፡

“በዚህ እኛ አከባቢ በሁሉም አቅጣጫ መንግስት የሰጠን ትኩረት በቂ ነው ብዬ አላምንም፡፡ ከ500 በላይ የአማራ ታጣቂዎች ናቸው እየወጉን የሚገኙት፡፡ በአከባቢያችን ዓመታት ወደ ማስቆጠር እየሄደ ያለው የሰላም እጦት አርሶ አደር እና ቤተሰቦቹን ለስቃይ የዳረገ እየሆነ ነው የመጣው፡፡ ከከዚህ ቀደሙ በባሰ ሁኔታ ትናት የተፈጸመው አስከፊ ድርጊት ለመግለጽም ስሜት የሚፈታተን ሆኗል፡፡” ያሉን እኚህ አስተያየት ሰጪ፤ መሮጥ የሚችል ሸሽቶ አዛውንቶች እና ህጻናት በሚኖሩበት ቤታቸው መሞታቸውን አንስተዋል፡፡

በአሙሩ ወረዳ ከዚህ በፊት የዜጎች መፈናቀል ከደረሰባቸው 13 ቀበሌያት በተጨማሪ ይህ የጎቡ ሲርባ በወረዳው ነዋሪዎች የተፈናቀሉበት 14ኛ ቀበሌ መሆኑ ነው የሚገለጸው፡፡ የአከባቢው ነዋሪ የአይን እማኙ አክለው በሰጡን ማብራሪያ “አሁን በዚያው በቀበሌው ሆኘ ነው የማውራህ፡፡ ይሄው አሁን 35 ሰዎች ቀብረን አሁንም ጥቃቱ ባለመቋረጡ ሌሎች አስከሬን ማንሳት አልቻልንም፡፡ የሟቾች ቁጥር 80 ሊደርስ እንደሚችል ይገመታል፡፡ ከ500 የማያንስ የቀንድ ከብትም ተዘርፏል፡፡ መንግስት ባለበት አገር ይህ መሆኑ ባልተገባ ነበር፡፡ አስከፊ ችግር ውስጥ ነን” ሲሉ የችግሩን አስከፊነት አብራርተዋል፡፡

የተወሳሰበው ግጭት ነዋሪዎቹን በሚያወዛግብበት በዚህ አከባቢ በኪረሙ ወረዳ “ጠላት” ባሉት ታጣቂ መከበባቸውና በአከባቢው የከፋ የጸጥታ ችግር መኖሩን የሚገልጹት የሀሮ ቀበሌው አስተያየት ሰጪ ግን በቂ የፌዴራል ወይል የክልል የጸጥታ ኃይል በአከባቢው ባለመኖራቸው እንቅስቃሴያቸው ተገድቦ እንደሚገኝ ነው ያስረዱት፡፡

እኚው ነዋሪ መንግስት ከበባውን ሰብሮላቸው ታማሚን ለማሳከምና ሌሎች እንቅስቃሴዎችን ማድረግ እንዲችሉም ጥሪያቸውን ያሰማሉ፡፡

የአሙሩ ወረዳ ጎቡ ሲርባ ቀበሌው አስተያየት ሰጪው የትናንቱን ጥቃት አስመልክተው በሰጡን አስተያየት ጥቃት አድራሽ ታጣቂዎች ከ40 በላይ የግለሰቦች ቤት እና እንደ ትምህርት ቤት ያሉ የህዝብ ተቋማትንም ጭማር ማውደማቸውን ያነሳሉ፡፡ የጥቃቱ ሰለባዎች ሰላማዊ የአከባቢው ነዋሪዎች መሆናቸውንም ይሞግታሉ፡፡

“ይህ የትናንት ጥቃት በብሬንና መተረየስ በመሰሉ ከባድ መሳሪያዎች የታገዘ ነው፡፡  የኪረሙና አሙሩ ወረዳ አስተዳደሮች ብሎም በየደረጃው ያሉ የመንግስት አካላት እንዲደርሱልን ነው ጥሪ የምናቀርበው፡፡ እኛጋ እየሞቱ ያሉት እኮ ታጣቂዎች ሳይሆኑ በአከባቢው የተከበሩ ንጹሃን ሽማግሌዎች ጭምር ነው፡፡” የኤን እማኙ ቀጥለዋል፡፡ “እየተቃጠለ ያለው የነዋሪዎች ቤት የኦነግ ሸነ ነው ወይ?” ሲሉም ጠይቀዋል፡፡ “እየተጠቃን ያለነው ንጹሃን ነን፡፡ አሁን ካንተ ጋር በምናወራበት ሰዓት ወልቂጤ ከሚባል አከባቢ በኩል ሌላ አዲስ ጥቃት ተከፍቶ ሟቾች እያነሳን መቅበር እንኳ አቋርጠናል፡፡” ሲሉም አስተያየታቸውን ደምድመዋል፡፡

በሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን በተለይም በአሙሩ እና ጃርደጋ ጃርቴ ወረዳዎች እንዲሁም በነዚህ ወረዳዎች አጎራባች ላይ በምትገኘው ኪረሙ ወረዳ ዓመቱን በሙሉ ከፀጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ስማቸው በተደጋጋሚ ሲነሳ ከርሟል፡፡ አሁን ስለሰፋው የነዋሪዎች የፀጥታ ስጋት እና የተወዛገቡበት የግጭቱ ክስተትን በተመለከተ ከገለልተኛ አካል ማጣራት አልተቻለም፡፡

በዚሁ ላይ የወረዳውና የዞኑ አመራሮች የሆኑ የአከባቢው ባለስልጣናት አስተያየት ለማካተት በተደጋጋሚ ያደረግነው ጥረትም እስካሁን አልተሳካም፡፡

ሰሞኑን በጃርደጋ ጃርቴ ወረዳ ታጣቂዎች በወረዳው ከተማ 01 ቀበሌ አከባቢ ከፍተዋል የተባለው ጥቃት ስላስከተለው ጉዳት ለማጣራት ወደ አከባቢው ነዋሪዎች ብንደውልም የቴሌኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት በአከባቢው በመቋረጡ ጥረታችን አልሰመረም፡፡

የፌዴራል መንግስት ኮሚዩኒኬሽን አገልግሎት ሚኒስቴር ቅዳሜ መስከረም 14 ቀን 2014 ዓ.ም. ባወጣው መግለጫ ግን መንግስት ከህብረተሰቡ ጋር ተቀናጅቶ በአከባቢው “ሸነ” ያሏቸው ታጣቂዎች ላይ ወታደራዊ እርምጃ መውሰዱን ተከትሎ ታጣቂዎቹ በጃርደጋ ጃርቴ ንጹኃን ላይ ያነጣጠረ የግድያ እርምጃ መውሰዳቸውን አመልክቷል፡፡ የመንግስት ኮሚዩኒኬሽን መግለጫው መንግስት አከባቢውን “አሸባሪ” ካሏቸው ኃይላት ለማጽዳት እየሰራ መሆኑን ቢገልጽም፤ በጥቃቱ በንጹሃን ላይ የደረሰ ዝርዝር መረጃ ከመስጠት ግን ተቆጥቧል፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW