1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ኦሮሚያ የፀጥታ ስጋት ባለባቸው አካባቢዎች የነዋሪዎች እንግልት

ሐሙስ፣ ጥቅምት 10 2015

ምዕራብ ኦሮሚያ እና በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች የፀጥታ ስጋት አይሎ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ግጭትና ጥቃት ነዋሪዎችን ማፈናቀል መቀጠሉ እየተገለጸ ነው፡፡ ምስራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ውስጥ እልባት አልባ ሆኖ የቀጠለው ግጭት የነዋሪዎች የእለት ተእለት ኑሮን ከባድ ማድረግ መቀጠሉንም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

IDPs from Horo guduru wollega
ምስል Seyoum Getu/DW

በጸጥታ ስጋት ውስጥ በሚገኙ የምዕራብ ኦሮሚያ ነዋሪዎች አቤቱታ

This browser does not support the audio element.

 

ምዕራብ ኦሮሚያ እና በተለያዩ የክልሉ አከባቢዎች የፀጥታ ስጋት አይሎ በሚስተዋልባቸው አካባቢዎች ግጭትና ጥቃት ነዋሪዎችን ማፈናቀል መቀጠሉ እየተገለጸ ነው፡፡ ምሥራቅ ወለጋ እና ሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ውስጥ እልባት አልባ ሆኖ የቀጠለው ግጭት የነዋሪዎች የእለት ተእለት ኑሮን ከባድ ማድረግ መቀጠሉንም ነዋሪዎች ተናግረዋል፡፡

በምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳ ባለፈው ሳምንት መጨረሻ ቅዳሜ ማታ የታጠቁ ኃይላት 24 ሰዎችን ገድለው  በንብረት ላይም ጉዳት ማድረሳቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች እና ባለስልጣናትን ዋቢ በማድረግ ዶይቼ ቬለ በሳምንቱ መጀመሪያ መዘገቡ ይታወሳል፡፡

በወረዳው ቦቃ በተባለች ቦታ በደረሰው ጥቃት በርካቶች የጥቃቱ ሰለባ መሆናቸው ይነገራል፡፡ እራሱን የኦሮሞ ነጻነት ጦር ብሎ የሚጠራውና መንግስት ሸነ ያለው እንዲሁም የአማራ ታጣቂዎች ተብለው በአከባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በተደጋጋሚ በነዚህ እና ሌሎችም ስፋራዎች ለሚደርስ ጥቃት በነዋሪዎች በተደጋጋሚ ይከሰሳሉ፡፡

ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸው እንዳይጠቀስ ጠይቀውን አስተያየታቸውን ለዶይቼ ቬለ የሰጡት የኪረሙ ወረዳ ሀሮ ቀበሌ ነዋሪ እንደሚሉት በዚህ ወረዳ የነዋሪዎች የእለት ተእለት ስጋቱ አሁንም አይሎ እንደቀጠለ ነው፡፡

በአከባቢው በኤሌክትሪክ እና በተለያዩ ማህበራዊ መገልገያዎች እጦት ተቸግረው የሚገኘው የአከባቢው ነዋሪ አሁንም ድረስ በታጣቂዎች በመከበብ የሰቀቀን ህይወት እንደሚመሩ ነው እኚው አስተያየት ሰጪ የሚገልጹት፡፡

ሌላው በርካቶች ከተፈናቀሉበት የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን አሙሩ ወረዳ አገምሳ ቀበሌ አስተያየታቸውን ያጋሩን ነዋሪ፤ “አሁን ታክቶናል፡፡ ከሳምንት ሳምንት የከፋ እንጂ ሲሻሻል አናይም፡፡ ይህ ሳምንት ደግሞ ስጋታችን አይሏል፡፡ አሁን ሰው እንደ በፊቱ እንኳ ርቀው መሄድ ብዙም አይደፈርም፡፡ ባለፈው ሳምንት ሶስት ወጣቶች እዚሁ አገምሳ ከተማ አጠገብ ከየት መጡ ሳይባል በታጣቂዎች ተገድለው ከ50 የማያንስ ከብቶች ተዘርፈዋል፡፡ ምግር በምትባል ቀበሌም ተመሳሳይ ዘረፋ ተሞክሮ እንደ ምንም ህዝብ ደርሶ አስጥሏል፡፡ ሌሊት አንተኛም፡፡ ቀንም አናርፍም፡፡ በብዙ አቅጣጫ ጥቃት ይከፈትብናል፡፡ ቡፋታ ጎልጃ በሚባል አቅጣጫም ማህበረሰቡ ሌሊት ኬላን ሲጠብቅ በታጠቁ አካላት ዘረፋ ተፈጽሟል፡፡ የተረጋጋ ሰላም ከራቀን ቆይቷል፡፡ በተለይም ሌሊት ሌሊት ሁሌም ተኩስ አለ፤ ግጭት ይፈጠራል ታክቶናል በቃ” ሲሉ የአከባቢው ማህበረሰብ ያለበትን ሰቆቃ አስረድተዋል፡፡የሆሮ ጉዱሩ ወለጋ ዞን ተፈናቃዮች አቤቱታ

አስተያየታቸውን አክለው ያብራሩት እኚው ነዋሪ ከተለያዩ የገጠር ቀበሌያት ነዋሪዎች ተፈናቅለው ወደ አገምሳ ከተማ መጥተዋል፡፡ “ከሆፊ ኢላሙ፣ ጦንቤ ዳንገብ፣ ሉማአ ዋሊ፣ ከጎቡ ቀጨሉ እስከ ሀሮ ጉዲና እንዲሁም ጃቦ ከሚባል አከባቢ ሰው ሁሉ ተፈናቅለው ይህን ከተማ ያለ አቅሟ አጨናንቀውአታል፡፡ ይሄ ስቃይ ከጀመረን ሁለት ዓመታት እየሞላ ነው፡፡ ከዚህ በፊት ጽንፈኛ የሆኑ ታጣቂዎች ነበር የሚያጠቁ፡፡ አሁን አሁን ግን ዘረፋን የለመደ ሁሉ ተነስቶ እያሰቃየን ይገኛል፡፡ መንግስት እንዲህ ስንሆን ሊመለከተን አይገባም፡፡ በመሃል የተሰቃየሁ ሰላማዊ ህዝብ ነው፡፡ ወዴት እንደምንሄድ ግራ ገብቶናል” በማለትም ውትወታቸውን ለመንግስት አሰምተዋል፡፡

ዶይቼ ቬለ ስለ ነዋሪዎቹ ስሞታ ከየአከባቢው የፀጥታ እና አስተዳደር ኃላፊዎች እና ከኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ቢሮ ምላሽ እና ተጨማሪ ማብራሪያዎችን ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ የሚገኘው ምስራቅ ወለጋ ዞን ኪረሙ ወረዳን ጨምሮ 13 በሚደርሱ ወረዳዎች ውስጥ ከዚህ ቀደም በነበረው የጸጥታ ችግር  ከ2 መቶ ሺ በላይ ዜጎች ተፈናቅለው መቆየታቸውን መረጃዎች ያሳያሉ፡፡

የኦሮሚያ ክልል አደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽን ባለፈው ሳምንት ለዶይቼ ቬለ ባጋራው መረጃ በቅርብ ጊዜው የሆሮ ጉዱሩ የተለያዩ ወረዳዎች ግጭት 61 ሺህ ያህል ነዋሪዎች ተፈናቅለው ለተለያዩ ቀውሶች መዳረጋቸውን አረጋግጧል፡፡ ሻምቡን ጨምሮ ወደ ተለያዩ የዞኑ አከባቢዎች በቂ የተባለውን የምግብና ምግብ ነክ የእርዳታ ቁሳቁሶች ከፌዴራል መንግስት ጋር በመሆን ወደ ስፍራው ለማዳረስ ጥረት እየተደረገ መሆኑንም የክልሉ ቡሳ ጎኖፋ ኃላፊ ሙስጠፋ ከድር ባለፈው ሳምንት ለዶይቼ ቬለ ተናግረው ነበር፡፡

በኦሮሚያ ክልል የወደሙ ተቋማትን መልሶ ለመገንባትና የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም የሚረዳ የ1.5 ቢሊዮን ብር ድጋፍ መደረጉን የከተማና መሠረተ ልማት ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡ ሚኒስትሯ ጫልቱ ሳኒ ከሌሎች ሀላፊዎች ጋራ በመሆን ድጋፉን ለኦሮሚያ ክልል ፕረዚዳንት ሽመልስ አብድሳ ትናንት ማስረከባቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል፡፡

ኢትዮጵያ አስከፊው የሰሜን ኢትዮጵያ የተራዘመ ጦርነት ውስጥ በምትገኝበት ባሁን ወቅት በተለይም በሰፊው አለመረጋጋት ይስተዋልበታል በሚባለው ምዕራብ ኦሮሚያ እና የክልሉ ሌሎች ውስን ስፍራዎች የነዋሪዎች ስቃይ እና እንግልት ትኩረት የተነፈገ ነው ይባልለታል፡፡

በምዕራብ ኦሮሚያ በተለያዩ ጊዜያት ለሚፈጠሩ ግጭቶች ተጠቂ ነዋሪዎቹ  “የአማራ ታጣቂዎች” ያሏቸውን እና መንግስት “ሸነ” ሲል በሽብርተኝነት የፈረጀውና እራሱን “የኦሮሞ ነጻነት ጦር” ብሎ የሚጠራውን ታጣቂ ቡድንን ተጠያቂ ያደርጋሉ፡፡

ስዩም ጌቱ

ታምራት ዲንሳ

ኂሩት መለሰ

 

 

 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW