1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

በምዕራብ ወለጋ ዞን ሕንዳዊ እና ጃፓናዊን ጨምሮ አምስት ሰዎች ተገደሉ

ማክሰኞ፣ መጋቢት 10 2011

በምዕራብ ወለጋ ዞን ከነጆ ከተማ አቅራቢያ ያልታወቁ ታጣቂዎች አንድ ሕንዳዊ እና አንድ ጃፓናዊን ጨምሮ አምስት ሰዎች ገደሉ። ሟቾች ይጓዙበት የነበረ ፒክ አፕ ደብል ጋቢና ተሽከርካሪ በጥይት ከመታ በኋላ በእሳት ጋይቷል። 

Karte Ethiopia und Eritrea ENG

ዛሬ ማለዳ ከነጆ አምስት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ከማለዳው 1 ሰዓት ከ15 ደቂቃ ላይ በተፈጸመው ጥቃት ከተገደሉ መካከል ሥራ አስኪያጅ እና የጂኦሎጂ ባለሙያን ጨምሮ ሶስት የአንድ ኩባንያ ተቀጣሪ ኢትዮጵያውያን ይገኙበታል። 

በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ከነጆ ከተማ በስተምዕራብ አቅጣጫ በተፈጸመው ጥቃት ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች አስከሬኖች ወደ ነጆ ሆስፒታል መወሰዳቸውን የከተማው የኮምዩንኬሽን ቢሮ ባለሙያ አቶ ቶሌራ ሱኪ እና በምርመራ ላይ የተሳተፉ የጸጥታ አስከባሪ ለDW አረጋግጠዋል። 

ከኦሮሚያ ክልል ወደ ነጆ የተላከ የጸጥታ አስከባሪ ኃይል አባል "የሬሳውን መልክ መለየት አትችልም። የእነሱ ጓደኞች የቱጋ እንደተቀመጡ፤ በዚህ ቦታ የተቀመጠው እከሌ ነው ሲሉን ነው ከዚያ ሬሳውን ያወጣንው። ሬሳውን አውጥተን ሆስፒታል አስገብተናል። ሬሳው እከሌ ብለህ መለየት የማትችልበት ደረጃ ላይ ነው ያለው" ሲሉ ለDW ተናግረዋል።

የነጆ ከተማ ነዋሪዎች ማለዳ የጥይት ተኩስ መሰማቱን አረጋግጠዋል። አቶ ቶሌራ "እሩምታ ነበረ። አንድ ጊዜ 12 ጥይት ተተኩሷል። ሌላ ጊዜ ደግሞ 15 ጥይት ተተኩሷል" ሲሉ ተናግረዋል። "ተኩሱን እኛም ሰምተናል" የሚሉት የጸጥታ አስከባሪ ከጥቃቱ ያመለጡ ሌሎች መንገደኞች መረጃውን በአካባቢው ለሚገኘው የፌድራል ፖሊስ እና የመከላከያ ሰራዊት ማድረሳቸውን ገልጸዋል። 

የጸጥታ አስከባሪው "ሌላ መኪና ከኋላ ተከትሎ የሚሔድ ነበር። አጠገቡ ሲደርስ በጥይት እንደተመታ እና ሰዎቹ መመታታቸው ሲያይ ሹፌሩ ረግጦ አለፈ እና ወደ እኛ ደወለ። በዚህን ጊዜ እነሱ [ጥቃት ፈፃሚዎች] እሳት ለኩሰውበት ነው የሔዱት። መኪናው እየተቃጠለ ነው" ሲሉ አክለዋል።   

የጸጥታ አስከባሪዎች ከሥፍራው ሲደርሱ "ወደ 56 የሚሆኑ የክላሽ ጥይቶች" ማግኘታቸውን ገልጸዋል። የተሽከርካሪው አካል በጥይት መመታቱን መስታዎቶችም መርገፋቸውን ጸጥታ አስከባሪዎች ታዝበዋል። 

እስካሁን የጥቃቱ ፈፃሚ ማንነት አልታወቀም። የአካባቢው ነዋሪዎች "ተኩስ ሰምተናል፤ ማንነታቸውን አናውቅም። እከሌ ነው ብለን መግለጽ አንችልም" የሚል ምላሽ ለጸጥታ አስከባሪዎች ሰጥተዋል።

እሸቴ በቀለ

አዜብ ታደሰ 

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW