1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በምዕራብ ጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች አሁን ጦርነቱ እንደቀጠለ ነዉ

ሰኞ፣ ጳጉሜን 1 2013

በስደት የቆዩና «ሳምሪ» የተባሉ የህወሓት ኃይሎች ከቅማንንት ተዋጊዎች ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ሽንፋና አካባቢው የከፈቱት ጦርነት በመንግስት ኃይሎች ቢቀለበስም አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ውጊያ መቀጠሉ ተመለከተ የቅማንንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቅዴፓ) ውንጀላው የተለመደ ነው ብሏል። 

Äthiopien  West Gondar und Metema
ምስል፦ DW/Alemenew Mekonnen

ከህወሓት ነፃ የወጡ አካባቢዎች ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እየተመለሱ ነዉ

This browser does not support the audio element.

 

 

በስደት የቆዩና «ሳምሪ» የተባሉ የህወሓት ኃይሎች ከቅማንንት ተዋጊዎች ጋር በመተባበር በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ሽንፋና አካባቢው የከፈቱት ጦርነት በመንግስት ኃይሎች ቢቀለበስም አሁንም በአንዳንድ አካባቢዎች ውጊያ መቀጠሉን የመንግስት ኃላፊዎችና የሽንፋ አካባቢ ነዋሪዎች ተናገሩ። የቅማንንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቅዴፓ) ውንጀላው የተለመደ ነው ብሏል። ከህወሓት ነፃ የወጡ ሌሎች አካባቢዎች ደግሞ ማህበራዊ አገልግሎት እና  ተቋማት ወደ ስራ እየገቡ ነውም ተብሏል።

በምዕራብ ጎንደር ዞን  መተማ ወረዳና የሽንፋ ከተማ አንዳንድ ነዋሪዎች “በበርካታ ግንባሮች ሽንፈት የገጠመው” ያሉት የህወሓት ኃይል ኃይሉን አሰባስቦ ሽንፋንና አካባቢውን የጦር አውድማና መሸጋገሪያ ለማድረግ ያደረገው ሙከራ አልተሳካም ብለዋል፡፡

አስተያየታቸውን ከሰጡን መካከል በሽንፋ ግንባር የሚገኙ ነዋሪ አንዱ ናቸው። ህወሓት ሳምሪ የተባለውንና የቅማንት ኃይልን አደራጅቶ ገብቷል ብለዋል፡፡

የሽንፋ ከተማ ቀበሌ አስተዳዳሪ አቶ በለጠ ዳምጤ ቡድኑ የሽንፋ ከተማንና አካባቢውን የጦር አውድማ በማድረግ ወደ ሌሎች የአማራ ክልል አካባቢዎች ለመሻገር ያደረገው ጥረት በተደረገው ውጊያ ከሽፏል ነው ያሉት፡፡

የምዕራብ ጎንደር ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደሳለኝ ጣሰው በበኩላቸው፣ ከነሐሴ 26/2013 ዓ ም ጀምሮ በአካባቢው ከ1ሺህ200 በላይ የጠላት ሉት ታጣቂ ከሱዳን እንደገባና በተወሰደ እርምጃ 175 ያህሉ ሲገደሉ ሌሎች በርካቶች ተማርከዋል ወይም ቆስለዋል ብለዋል፡፡

ቡድኑ ወደ ሱዳን እንደገና መውጣት የማይችልበት ሁኔታ እንዳለ የተናገሩት አቶ ደሳለኝ የመንግስት ኃይል እተከታተለ እያጠቃው እንደሆነም ተናግረዋል፡፡

የቅማንት ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (ቅዴፓ) ምክትል ሊቀመንበር አቶ አውግቸው ማለደ ስለቅማንንት የተባለው ስሞታ የተለመደ መሆኑን አመልክተው፣ “ሳምሪ ከቅማንት ጋር የሚያገናኘው ነገር የለም፣ የቅማንንት ማህበረሰብም ስለተባለው ነገር የሚያውቀው ነገር የለም ” ሲሉ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ ለ20 ቀናት ያህል በህወሓት ቁጥጥር ስር የነበረቸው የዋግኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ማዕከል ሰቆጣ ከባለፈው አርብ ጀምሮ ከቡድኑ ነፃመውጣት መቻሏንና ማህበራዊ ተቋማት ወደ መደበኛ ስራቸው እየተመለሱ መሆናቸውን የብሔረሰብ አስተዳደሩ ምክትል አስተዳዳሪ አቶ ተስፋዬ ገብሬ ለዶይቼ ቬለ ተናግረዋል፣ ሆኖም ህወሓት ጠቅልሎ ከብሔረሰብ አስተዳደሩ እንዳለቀቀም ጠቁመዋል፡፡

ቀደም ሲል በህወሓት ተይዘው የነበሩ የደቡብ ጎንደር  ዞን ከተሞችም ወደ መደበኛ እንቅስቃሴ እተመለሱ እንደሆነ የዞኑ አስተዳደር አመልክቷል፡፡

ዓለምነው መኮንን

አዜብ ታደሰ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW