በምዕራብ ጎንደር ዞን አብዛኛዎቹ ከተሞች ኤሌክትሪክ ተቋርጧል
ሰኞ፣ ግንቦት 25 2017
ባለፈው ግንቦት 22 ቀን 2017 ዓ.ም. በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ “መቃ” በተባለ ቦታ በጣለ ከባድ ዝናብ ምክንያት 230 ኪሎ ቮልት ተሸካሚ 6የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በመውደቃቸው ወደ ሱዳን የሚጓዘውን የኤሌክትሪክ ኃይል ጨምሮ በምዕራብ ጎንደር ዞን በሚገኙ በአብዛኛዎቹ ከተሞች ኃይል መቋረጡን የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት አስታውቋል፡፡
በአገልግሎቱ የምዕራብ ጎንደር ዞን የስርጭት፣ ኔትወርክና መሠረተ ልማት ቡድን አስተባባሪ አቶ ላቅ አያልነህ ለዶይቼ ቬሌ እንደተናገሩት በነበረው ከበድ ዝናብ ምክንያት ወደ ሱዳን የሚሄደው መስመር ጭምር ተጎድቷል፤ በምዕራብ ጎንደር የሚገኙ በርካታ ከተሞች ኃይል ተቋርጦባቸዋል፣ የጥገና ሥራዎች በባለሙያዎች እየተሰሩ እንደሆነም ተናግረዋል፡፡
ወደ ሱዳን የተዘረጋው መስመር ጉዳት ደርሶበታል
ወደ ሱዳንኤሌክትሪክየሚያስተላልፈው መስመር መሰሶ መውደቁን የተናገሩት አቶ ላቀ የመስመር ፍተሻ እየተደረገ በመሆኑ በጉዳዩ ዙሪያ ዝርዝር መረጃ እንደሌላቸው አመልክተዋል፡፡
የምዕራብ ጎንደር ዞን የመንግሥት ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች መምሪያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ቢሆነኝ በበኩላቸው በጉዳቱ በርካታ ከተሞች ኃይል እንደተቋረጠባቸው ጠቁመው፣ የመልሶ ጥገናው ሥራ እየተሰራ ነው ብለዋል፡፡“ኮኪት፣ ገንዳ ውሀ፣ አውላላ፣ አዳኝአገር ጫፎ፣ ገለጎ ሽንፋ፣ የተባሉ አካባቢዎች ኃይል ተቋርጦባቸዋል፡፡” ብለዋል፡፡
የሽንፋ ከተማ ነዋሪ አካባቢው ቆላማ በመሆኑ ኃይል መቋረጡም በብዙ ከተሞች በውሀ አቅርቦት ላይ ችግር መፍጠሩን አስረድተዋል፡፡
“ኃይል በመቋረጡ በሥራ ላይ ተፅዕኖ ፈጥሯል” ነዋሪዎቹ
ከገንዳ ውሀ በ18 ኪሎሜትር ርቀት ላይ ጉዳት መድረሱን የተናገሩት የመቃ ቀበሌ ነዋሪ በመስመሩ ብልሽት ምክንያት ባንኮች፣ ፀጉር ቤቶች፣ ዳቦ ቤቶች አገልገሎት እየሰጡ አይደለም ነው ያሉት፡፡
የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በይፋዊ የፌስ ቡክ ገፁ እንዳመለከተው፣ ግንቦት 22/2017 ዓም ነፋስ ቀላቅሎ የጣለ ከባድ ዝናብ መቃ በተባለ ቦታ ላይ ባል 230 ኪሎ ቮልት ኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎችን በመጉዳቱ በኃይል አቅርቦት ላይ ጉዳት ደርሷል ነው ያለው፣ በዚህም ምክንያት በምዕራብ ጎንደር ዞን ገንዳ ውሀ፣ መተማ ዮሐንስ ገለጎና አካባቢው ኃይል ተቋርጧል ብሏል፡፡
ከከረምቱ ጋር ተያይዞ በበርካታ አካባቢዎች የኤሌክትሪክ መቋረጥ በየእለት የቀን ተቀን ሥራቸው ላይ ጫና እያሳደረ እንደሆነ የተለያየ አካባቢ ነዋሪዎች የገልፃሉ፡፡
ዓለምነው መኮንን
ኂሩት መለሰ
ሸዋዬ ለገሠ