በምዕራብ ጎንደር ዞን የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሶሶች በተደጋጋሚ ይሰረቃሉ
ማክሰኞ፣ ነሐሴ 13 2017
በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞንየኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ምሶዎች በመሠረቃቸዉ ምክንያት አብዛኛዎቹ የዞኑ ከተሞች ኃይል ከተቋረጠባቸው ከ10 ቀናት በላይ ማስቆጠሩን ነዋሪዎች ተናገሩ። የኤሌክትሪክ ኃያል በዉጤቱም “ኔት ወርክ” በመቋረጡ ባንኮች አግልግሎት ማቆማቸዉን ባለሙያዎች አስታዉቀወል። የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ጥገና መጀመሩን አመልክቷል፡፡
መፍትሔ ያጣው የኃይል ተሸካሚ ምሰሶዎች ዝርፊያ
ሰሞኑን በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን ጭልጋ ወረዳ አካባቢ በሁልት ባለ 230ሺህ ቮልት ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ተሸካሚ ብረቶች ላይ በተፈፀመ ስርቆት የአካባቢው ከተሞች ኃይል እንደተቋረጠባቸው የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኤሌክትሪክ ኃይል አመልክቷል፡፡
“230ሺህ ቮልት ኃይል ተሸካሚ 2 ምሰሶዎች ስርቆት ተፈፅሟል” የሰሜን ምዕራብ ሪጅን ኤሌክትሪክ ኃይል
በመተማ ዮሐንስ የአንድ ባንክ ባለሙያ የኃይል መቋረጡ “የኔት ወርክ” አገልግሎቱም እንዲቋረጥ በማድረጉ ባንካቸው አገልግሎት ምስጠት ማቆሙን ጠቁመው፣ አገልግሎቱ እንዲመለስ ኢትዮ ቴሌ ኮም “የኔት ወርክ” አገልግሎት ጀኔሬተር በመጠቀም እንዲያስጀምር ጥያቄ ማቅረባቸውን ተናግረዋል፡፡
በምዕራብ ጎንደር ዞን አንድ የቋራ ወረዳ ነዋሪም መብራት በአካባቢው ከተቋረጠ ቀናት ባማስቆጠሩ ከኤሌክትሪክ ኃይል ጋ በተያያዘ አግልግሎት የሚሰጡ ሁሉም ተቋማት ሥራ ማቆማቸውን አስረድተዋል፡፡
“በኃይል መቋረጡ ባንኮች ሥራ አቁመዋል” የባንክ ባለሙያ
የሽንፋ ከተማ ነዋሪ የሆኑ ሌላ አስተያየት ሰጪ እንዲሁ ከኃይል መቋረጡ ጋር ተያይዞ በርካታ ሥራዎች መቆማቸውን ተናግረዋል፣ በተለይ አካባቢው ሞቃታማ በመሆኑ የማቀዝቀዣ ማሳሪያዎች በማቆማቸው ህብረተሰቡ ተቸግሯል ነው ያሉት፣ ብዙ ባንኮች እየሰሩ አይደለም ያሉት እኚህ አስተያየት ስጪ ጀኔሬተር በመጠቀም ኃይል የሚያገኙትም ቢሆን የነዳጅ ወጪውን አልቻሉትም ብለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል የሰሜን ምዕራብ ሪጅን የከፍተኛ መስመር ጥገና ኃላፊ አቶ በላይነህ ልጃለም ነሐሴ 2/2017 ዓም በጭልጋ ወረዳ ከፍተኛ የኤሌክትሪክ መስመር ላይ ስርቆት በመፈፀሙ በምዕራብ ጎንደር ዞን ያሉ ከተሞች ኃይል እንደተቋረተባቸው ተናግረዋል፣ ሆኖም የጥገና ሥራው መጀመሩን ለዶይቼ ቬሌ አመልክተዋል፡፡
“መስመሩ ቢጠገንም አሁንም ከስጋት ነፃ አይደለም” አስተያየት ስጪ
መስመሩ ጥገና ቢደረግለትም በአካባቢው ተደጋጋሚ የኤሌክትሪክ መስመሮችና ብረቶች ስርቆት የሚፈፀምበት በመሆኑ አሁንም ጠበቅ ያለ ጥበቃና ለህብረተሰቡ የግንዛቤ ማስጨበጥ ሥራ ካልተሰራ ችግሩ በቀጣይም ሊከሰት እንደሚችል ኃላፊው ሥጋታቸውን ተናግረዋል፡፡
ግንቦት 22/2017 ዓም በምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ “መቃ” በተባለ ቦታ 230 ሺህ ኪሎ ቮልት ተሸካሚ 6 የኤሌክትሪክ ምሰሶዎች በተመሳሳይ ጉዳት ደርሶባቸው በዞኑ በሚገኙ አብዛኛዎቹ ከተሞች ለቅናት ኃይል ተቋርጦ እንደነበር የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት በወቅቱ አስታውቆ ነበር፡፡
ዓለምነው መኮንን
ነጋሽ መሐመድ
ልደት አበበ