1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ

በምዕራብ ጎንደር የታጣቂዎች ምሽግ በኢትዮጵያ ኃይሎች ቁጥጥር ስር መግባቱ

ሐሙስ፣ ጥቅምት 3 2015

በአማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን መተማ ወረዳ «ታጣቂዎች ለሁለት ዓመታት መሽገውበት ነበር» የተባለን ቦታ የኢትዮጵያ ኃሎች ሰሞኑን በተደረገ ውጊያ ማስለቀቃቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች ተናገሩ። እማኞች ለዶቼ ቬሌ እንደገለጹት አብዛኘዎቹ ታጣቂዎች ተገድለዋል፤ ሌሎች ደግሞ ወደ ሱዳን ተሻግረዋል።

Äthiopien l Metema in der Amhara Region
ምስል፦ Alemnew Mekonnen

«ታጣቂዎቹ ተገድለዋል፤ የተረፉትም ሸሽተዋል»

This browser does not support the audio element.

በምዕራብ ጎንደር ዞን የታጣቁ ኃይሎች በተደጋጋሚ ወደ አካባቢው በመዝለቅ በግብርና ኢንቨስትመንት በተሰማሩ ባከሀብቶች ላይ ጥቃት በመክፈት አደጋዎችን ሲያደርሱ እንደነበር የአካባቢ አስተዳደሮች በተደጋጋሚ ሲገልፁ ቆይተዋል፡፡ ሰሞኑንም ሱዳንና ኢትዮጵያ በሚዋሰኑበት አካባቢ በመንግሥት ኃይሎችና በታጣቂዎች መካከል በተደረገ ውጊያ ታጣቂዎች ለሁለት ዓመታት ይዘዋቸው የነበረውን ጠንካራ ምሽጎች የመንግሥት ኃይሎች በወሰዱት የማጥቃት እርምጃ  ነፃ ማውጣታቸውን የአካባቢው ነዋሪዎች አመልክተዋል። የመተማ ወረዳ ነዋሪ እንዳሉት ከሱዳኗ ቲያ ከተባለች አካባቢ በቅርብ እርቀት ላይ የሚገኙና በታጣቂዎች ቁጥጥር ስር የነበሩ ምሽጎች አሁን በጥምር ጦሩ እጅ ገብተዋል።

«ቦታው የታወቀ ነው በሱዳን ድንበር ቲያ ነው የሚባለው ሶስት ምሽጎች ነበሩ ሶስቱንም ምሽጎች የጥምር ኃይሉ  ገብቶ እስከ ቀኑ ስድስት ሰኣት አካባቢ ነፃ አውጥቶ የድል ባለቤት ሆኗል።»

የመተማ ወረዳ አስተዳደር ጽህፈት ቤት ምስል፦ Alemnew Mekonnen

አሁን ቲያ በተባለው የኢትዮ ሱዳን አቅጣጫ «ጠላት» ያሉት አካል ተመትቶ መሞቱንና መበታተኑን ነው ነዋሪዎቹ የሚያስረዱት። በከፍተኛ ደረጃ በኮንክሪት ተሰርተው ነበሩ ምሽጎች ፈራርሰው ቤት ሠርተው የኖሩበት የነበረ ቦታ፣ እህል የሚፈጩበት ሁሉ በጥምር ኃይሉ ቁጥጥር ስር መዋሉን ነው ያስረዱት «ጠላት አሁን መሽጎ የተቀመጠበት ቦታ የለም» ሲሉ ነው አስተያየት ሰጪው ያብራሩት፡፡ ሁለቱ የበውቀት ተራራዎች፣ ሻረው (ዳኘው) ተራራ እና ቲያ ጥግ የነበረ (ማሪያም ተራራ) ሶስት ታላላቅ ምሽጎች መሰባበራቸውን አመልክተዋል፡፡በምዕራብ ጎንደር አንዳንድ አካባቢዎች አሁን ጦርነቱ እንደቀጠለ ነዉ

አስተያየት ሰጪዎቹ እንደሚሉት ታጣቂዎቹ በአካባቢው በስፋት የሚንቀሳቀሱት «የቅማንት ታጣቂ» እና «ጁንታ» ብለው የጠሯቸው ናቸው:: ኅብረተሰቡ በተገኘው ድል መደሰቱንና ነጻ የወጡ አካባቢዎችን ለማየት ወደ ቦታዎቹ እየሄደ ነው ብለዋል።

ታጣቂዎቹ ተጣምረው ውጊያ ሲያደርጉ አንደነበር ያስረዱት አንድ አስተያየት ሰጪ፣ ህይወታቸውን ያተረፉ ወደ ሱዳንና ኮርገና ወደተባለ አካባቢ እንደሸሹም ገልጠዋል።

በአማራ ክልል የመተማ ወረዳ፤ ጉዋንግ ወንዝምስል፦ Alemnew Mekonnen

«የመጡት እንግዴህ ጥምር ናቸው፣ የሳምሪ (የህወሓት ክንፍ)፣ የቅማንት ኃይል ነው በጋራ ሆነው የመጡት። በዚያ አካባቢ ላይ በተደጋጋሚ ነው ሙከራ የሚያደርጉት ያው አይሳካላቸውም … እሑድ የነበረው ደግሞ “ጥሩ ምት” ነው የተመቱት ከተመቱ በኋላ አብዛኛዎቹ የሳምሪ ቡድን አባላት ወደ ሱዳን ነው የሄዱት የቅማንት ኃይል ደግሞ ወደ ኮርገና ነው የሄዱት ስለዚህ የነበረው ሁኔታ ያንን ደጋግመው ቢሞክሩትም ያን ቦታ ለማስከፈት ነው ያ ከተከፈተላቸው ደግሞ ወደ መሐል የመግባት ፍላጎት ነው የነበራቸው፣ ግን ለጊዜው ተቀጭቷል።»

አንድ የምዕራብ ጎንደር ዞን የሥራ ኃላፊ ዝርዝር መረጃ ለመስጠት ፈቃደኛ ባይሆኑም በተደረገው ጦርነት ድል መገኘቱን ግን ተናግረዋል። ከታጣቂዎቹ በኩል አስተያየት ለማግኘት ያደረግሁት ጥረት አድራሻቸውን ማግኘት ባለመቻሌ አልተሳካም፡፡

ዓለምነው መኮንን

ሸዋዬ ለገሠ

ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW