1. ወደ ይዘቱ እለፍ
  2. ወደ ዋናዉ ገጽ እለፍ
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ እለፍ
ውዝግቦችሶማሊያ

በሞቃዲሾ እስር ቤት ላይ ጥቃት የፈጸሙ የአልሸባብ አባላት በሙሉ መገደላቸውን ሶማሊያ ገለጸች

እሑድ፣ መስከረም 25 2018

በሞቃዲሾ ጎድካ ጂልኮው እስር ቤት ላይ ትላንት ጥቃት የፈጸሙ ሰባት የአል-ሸባብ አባላት መገደላቸውን የሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ። ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው አል-ሸባብ የታሰሩ አባላቱን እንዳስፈታ ገልጿል። የሶማሊያ ብሔራዊ የመረጃና ደሕንነት ኤጀንሲ የሚያስተዳድረው እስር ቤት የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ለፍርድ ከመቅረባቸው በፊት የሚቆዩበት ነው።

የአል ሸባብ አባላት የጦር መሣሪያ ይዘው ይታያሉ
በሞቃዲሾ በሚገኘው ጎድካ ጂልኮው እስር ቤት ላይ ትላንት ቅዳሜ ለተፈጸመው ጥቃት ኃላፊነቱን የወሰደው አል-ሸባብ በእስር ላይ የነበሩ አባላቱን እንዳስፈታ አስታውቋል። ምስል፦ picture alliance/AP Photo/M. Sheikh Nor

በሞቃዲሾ በሚገኘው ጎድካ ጂልኮው እስር ቤት ላይ ትላንት ቅዳሜ ጥቃት የፈጸሙ ሰባት የአል-ሸባብ አባላት መገደላቸውን የሶማሊያ መንግሥት አስታወቀ። ከሶማሊያ ፕሬዝዳንታዊ ጽህፈት ቤት አቅራቢያ የሚገኘው እስር ቤት አብዛኛውን ጊዜ የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ለፍርድ ከመቅረባቸው በፊት የሚቆዩበት ነው።

የሶማሊያ ብሔራዊ የመረጃ እና ደሕንነት ኤጀንሲ (NISA) የሚያስተዳድረው እስር ቤት በሞቃዲሾ ከፍተኛ ጥበቃ ከሚደረግላቸው መካከል ይገኝበታል። 

የአል-ሸባብ ታጣቂዎች ትላንት ቅዳሜ ከሰዓት በኋላ በእስር ቤቱ ላይ ጥቃት ሲከፍቱ ከፍተኛ ፍንዳታ እና ለሰዓታት የዘለቀ የተኩስ ልውውጥ እንደተሰማ የዐይን እማኞች ለፈረንሳይ ዜና አገልግሎት እና ለአሶሼትድ ፕሬስ ተናግረዋል።

ለጥቃቱ ኃላፊነቱን የወሰደው አል-ሸባብ በእስር ላይ የነበሩ አባላቱን እንዳስፈታ አስታውቋል። የሶማሊያ ሀገር ውስጥ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ እሁድ ባወጣው መግለጫ “የጸጥታ ኃይሎች የተሳተፉትን ሁሉንም ሰባት ታጣቂዎች ተኩሰው በመግደል ጥቃቱን ማቆም ተሳክቶላቸዋል” ብሏል። ይሁንና በተፈጸመው ጥቃት የተገደሉ እስረኞችም ይሁኑ የጸጥታ አስከባሪዎች ስለመኖራቸው ያለው ነገር የለም።

ጥቃቱ የተፈጸመው በሞቃዲሾ ጎዳናዎች እና ከፍተኛ ጥበቃ በሚደረግላቸው ተቋማት ደጃፍ ለደሕንነት የተቀመጡ ግዙፍ የኮንክሪት መገደቢያዎች መነሳታቸውን የሶማሊያ መንግሥት ባሳወቀ በሰዓታት ልዩነት ውስጥ ነበር። 

ሶማሊያ ነባራዊ ሁኔታ ውጥረት ቢበረታበትም ፕሬዝደንት ሐሰን ሼህ መሐመድ በዚህ ዓመት ሀገሪቱ ቀጥተኛ ምርጫ እንድታካሒድ ግፊት በማድረግ ላይ ናቸው። ፕሬዝደንቱ በምርጫ ምክንያት በተፈጠረ አለመግባባት በሶማሊያ ብሔራዊ ጦር እና ክልላዊ ኃይሎች መካከል ግጭት የተቀሰቀሰባትን የጁባላንድ ግዛት ዛሬ እሁድ ጎብኝተዋል። 

ላለፉት 25 ዓመታት ከአል-ሸባብ ጋር ግጭት ውስጥ የቆየችው የሶማሊያ የጸጥታ ሁኔታ በዚህ ዓመት መልሶ የማሽቆልቆል አዝማሚያ አሳይቷል። ታጣቂ ቡድኑ በዚህ ዓመት አነስተኛ ከተሞች እና መንደሮች በመቆጣጠር በጎርጎሮሳዊው አቆጣጠር ከ2022 እስከ 2023 በተወሰደ ወታደራዊ እርምጃ የተፈጠረውን ለውጥ እየቀለበሰ እንደሚገኝ የፈረንሳይ ዜና አገልግሎት ዘግቧል። 

አርታዒ ታምራት ዲንሳ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል እለፈው ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW