1. ወደ ይዘቱ ዝለል
  2. ወደ ዋናዉ ገፅ ዝለል
  3. ወደ ተጨማሪ የDW ድረ-ገፅ ዝለል

ምርጫን ተከትሎ በሞዛምቢክ የቀሰቀሰው ተቃውሞ

ቅዳሜ፣ ጥቅምት 30 2017

በደቡብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ሞዛምቢክ የመጀመሪያው የመድበለ ፓርቲ ምርጫ ከተካሄደ ከጎርጎሪያኑ 1994 ዓ/ም ጀምሮ እያንዳንዱ የምርጫ ውጤት በተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን በገለልተኛ ተንታኞችም ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ አወዛጋቢ ነው። ዘንድሮም በሀገሪቱ በጥቅምት ወር አዲሱ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ቻፖ ከተመረጡ ወዲህ፤የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እየተባባሰ ነው።

Mosambik Maputo Proteste gegen Regierung
ምስል Siphiwe Sibeko/REUTERS

ምርጫን ተከትሎ በሞዛምቢክ የቀሰቀሰው ተቃውሞ

This browser does not support the audio element.

ሞዛምቢክ በጥቅምት ወር አዲሱ ፕሬዝዳንት ዳንኤል ቻፖ ከተመረጡ ወዲህ፤ በደቡብ አፍሪቃዊቷ ሀገር ፤የተቀሰቀሰው አለመረጋጋት እየተባባሰ ነው ። ያለፈው ሀሙስ በዋና ከተማይቱ ማፑቶ ጎዳናዎች ላይ ተቃዋሚዎች ያስተባበሯቸው ታላላቅ ሰልፎች ተካሂደዋል። ታዛቢዎች ብጥብጥ እና ግርግር እየጨመረ ይመጣል ብለው ይሰጋሉ።
በደቡብ አፍሪካ በሮዛ ሉክሰምበርግ ፋውንዴሽን  ተንታኝ የሆኑት ሞዛምቢካዊው ፍሬድሰን ጊለንጌ እንደሚሉት በሀገሪቱ ላለፉት በርካታ አመታት በነበረዉ አፋኝ አገዛዝ ሳቢያ  ሁከትን መጠቀም  ብቸኛው መንገድ እየሆነ የመጣ ይመስላል። .
«አገዛዙ ሰዎች ከሰላማዊ ሰልፍ ለማስቆም የሃይል እርምጃ ለመውሰድ እየሞከረ ነው።እስካሁን ይህ አልሰራም፣ ሰዎች አሁንም በመንገድ ላይ ናቸው።... አንዱ ችግር ሰዎች ስለለውጥ መንግስት እንዲያናግራቸው የሚጠብቁ መሆናቸው ነው። ነገርግን መነጋገር አልቻሉም። ነገር ግን በቋሚነት መነጋገርየሚፈልገው የሞዛምቢክ መንግስት ሳይሆን ህዝብ ብቻ ነው። አምናለሁ፣ መንግስት ሰልፉን ለማስቆም ብጥብጥ ይጨምራል።»ብለዋል።

የመንግስት ተቃውሞዎችን ችላ ማለት

ፍሬድሰን ጊለንጌ እንደሚገልፁት ሞዛምቢካውያን ስለሚመኙት ለውጥ ለመወያየት መንግሥት ፈቃደኛ ባለመሆኑ  ለተቃውሞ እውቅና እየሰጠ ነው። 
የመጀመሪያው የመድበለ ፓርቲ ምርጫ  ከተካሄደ ከጎርጎሪያኑ 1994 ዓ/ም ጀምሮ በሞዛምቢክ  እያንዳንዱ የምርጫ ውጤት በተቃዋሚዎች ብቻ ሳይሆን በገለልተኛ ተንታኞችም ሳይቀር በከፍተኛ ሁኔታ አወዛጋቢ ነው።
ባለፉት 30 ዓመታት ውስጥ አንድም የምርጫ ውጤት በሀገሪቱ ተአማኒ ሆኖ አልታየም የሚሉት ጌሌንጌ፤ ጎልቶ የወጣው የምርጫ ማጭበርበር እና የገዥው ፓርቲ ፍሪሊሞ/ FRELIMO/ ቀጣይነት ያለው ታማኝነት ማጣት፤ በምርጫ እና የፍትህ አካላት ላይ ተደጋጋሚ ውንጀላዎች እንዲጨምሩ ያደርጋል። ከምርጫው በኋላ ተደጋጋሚ ግጭቶችን ጨምሮ በመላ አገሪቱ አለመረጋጋት እንዲፈጠር ምክንያት ሆኗል።
በዚህ አመት የሞዛምቢካውያን  የቁጣ ስሜት ከዋና ከተማዋ ማፑቶ ተሻግሮ  በበርካታ የሀገሪቱ ክፍል ታይቷል። የምርጫው ውጤት በጥቅምት 24  ቀን ይፋ ከሆነ ወዲህ  ከባድ ተቃውሞዎች ተቀስቅሰዋል።ተቃዋሚዎች ውጤቱን በመቃወም የጥቅምት 9ኙን ምርጫ በማጭበርበር  ገዥውን ፓርቲ/FRELIMO/  ከሰዋል።

በሞዛምቢክ ፕሬዚዳንታዊ ምርጫ ዕጩ የነበሩት ቫንሲዮ የሞንድላን ጠበቃ እና ቃል አቀባይ ባልታወቁ ታጣቂዎች በጥይት ተገድለውባቸዋል።ምስል Alfredo Zungia/AFP

የተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቬንሢዮ ሞንድላን ደጋፊዎቸ ቅሬታቸውን ለህገ-መንግሥታዊ ፍርድ ቤት ያቀረቡ ሲሆን የሀገሪቱ የምርጫ ኮሚሽን የምርጫ ውጤቱን ይፋ ካደረገ በኋላ ወዲያውኑ ለተቃውሞ ወደ  አደባባይ ወጥተዋል።
የ50 ዓመቱ ሞንድላን የግል  እጩ ሆነው ቢወዳደሩም፣ ከ20% በላይ ድምጽ ያገኘው የሞዛምቢክ ልማት ብሩህ ተስፋ ፓርቲ ድጋፍ አግኝተዋል።
እንደ  ምርጫ ኮሚሽኑ የፍሬሊሞ እጩ ዳንኤል ቻፖ ከ70% በላይ ድምጽ በማግኘት ፕሬዚዳንታዊ ምርጫውን አሸንፈዋል። የሞዛምቢክ ዋና ተቃዋሚ ፓርቲ ሬናሞ እጩ ተወዳዳሪው ከ6 በመቶ ያነሰ ድምጽ በማግኘት  ሶስተኛ ደረጃን ይዞ አጠናቋል።

የሞዛምቢክ ጨቋኝ አገዛዝ በተቃዋሚዎች ግድያ መከሰስ

ፍሪሊሞ  ፓርቲም ለተቃውሞ ሰልፎቹ ተገቢ መልስ መስጠት ባይችልም፣ ፖሊስ ሰልፎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።  የተቃዋሚ ፓርቲ መሪው የሞንድላን ጠበቃ እና ቃል አቀባይም ባልታወቁ ታጣቂዎች በጥይት ተገድለዋል። ይህም በሰልፈኞቹ ላይ ተጨማሪ ቁጣ እና ብጥብጥ እንዲጨምር አድርጓል። ግድያው ከተፈፀመ በኃላም በእሳቸው ላይ የፖሊስ ዛቻ እና ማስፈራሪያ  ስለበረታባቸው ከህዝብ እይታ መሰወራቸው ተገልጿል። በመገናኛ ብዙሃን ዘገባ መሰረት የሀገሪቱ ፖሊሶች ሞንድላን በደቡብ አፍሪካ ተደብቀዋል ብሎ ያምናሉ።ያም ሆኖ ተንታኙ ጊለንጌ በተቃዋሚ ፓርቲው መሪ  ደህንነት ላይ ስጋት አላቸው። 
«በሞዛምቢክ በማይስማሙባቸው የፖለቲካ እና የማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሃሳባቸውን በመግለጻቸው ብቻ ነፃ ጋዜጠኞች፣ የህዝብ አስተያየት ሰጪዎች፣ ምሁራን፣ ተሟጋቾች እና ሌሎች በርካታ ሰዎች ሲገደሉ አይተናል። ሞንድላን ሞዛምቢክ ውስጥ ቢሆን ሊገደል የሚችልበት ግልፅ አደጋ አለ ማለት እችላለው።»ብለዋል።ሲሉ ለDW ተናግረዋል።

በሞዛምክ ለተቀቀሰው ተቃውሞ ፍሪሊሞ ፓርቲም ለተቃውሞ ሰልፎቹ ተገቢ መልስ መስጠት ባለመቻሉ፤ ፖሊስ ሰልፎቹን ለመበተን አስለቃሽ ጭስ ተኩሷል።  ምስል Alfredo Zungia/AFP

በስዊዘርላንድ ባዝል ዩኒቨርሲቲ ሞዛምቢካዊው የማህበረሰብ ጥናት ባለሙያ  ኤሊሲዮ ማካሞ በበኩላቸው ከሀገር መውጣት ለተቃዋሚዎች ጥሩ ውሳኔ ነው ይላሉ።ማካሞ አያይዘውም ስለ ተቃውሞው ስፋት ሲናገሩ  "ከዚህ በፊት በሞዛምቢክ እንደዚህ ያለ ተቃውሞ አልተከሰተም" ይላሉ።
«ሰልፎቹ ጨዋታ ቀያሪዎች ናቸው፣ ከዚህ በፊት በሞዛምቢክ ውስጥ እንደዚህ ያለ  ነገር አልተፈጠረም። ወጣቶች ፍርሃት የላቸውም። እናም ትርክቱን መቀየር ችለዋል። አሁን መንግስት ትኩረቱ በማጭበርበር ላይ ነው። እናም የፍሬልሞ ድል በማጭበርበር ብቻ ተቀባይነት ሊኖረው የሚችል  አይመስለኝም።»በማለት ገልፀዋል።

የሀሰተኛ መረጃን ማሰራጨት 

ከተቀሰቀሰው ተቃውሞ ጎንለጎን በአካባቢው  በርካታ የሀሰት ዜናዎች እየተሰራጩ ነው  የሚሉት ባለሙያው፤  በበይነመረብ የሚደረጉ የማጭበርበሪያ ሙከራዎች በሙሉ ከመንግስት ባይሆኑም፤ አንዳንዶቹ ግን በቀጥታ “ከFRELIMO ፓርቲ ጋር የተገናኙ ናቸው።ብለዋል።  እነዚህም ከተቃዋሚዎች የሚመጡ ትርክቶችን ለመመከት ስልታዊ በሆነ መንገድ የተነደፉ መሆናቸውን ገልፀዋል ። 
በሌላ በኩል ምርጫን ተከትሎ ሞዛምቢክ ውስጥ መንግስት ተፅእኖውን ለማስቀጠል  በኢንተርኔት አገልግሎት ላይ ከፍተኛ ገደቦችን ማድረግ  የተለመደ  ዘዴ መሆኑን ባለሙያው ገልፀዋል።
ለዚህም « የኢንተርኔት ኩባንያዎች የኢንተርኔት አገልግሎትን ለመሰረዝ ወይም ለመገደብ ከፖሊስ እና ከፍትህ ባለስልጣናት መመሪያ ተቀብለዋል» ብለው ያምናሉል።
ሞንድላን የምርጫ ውጤትን በመቃወም የሚደረገው ተቃውሞ እስከሚቀጥለው ሳምንት ድረስ  ደጋፊዎቹን በተቻለው መጠን በማህበራዊ ሚዲያ ላይ ሲማፀኑ ቆይተዋል።ሞንድላን ባለፈው አርብ  በፌስቡክ ገጻቸው በቀጥታ ባደረረጉት  ንግግር፤ ወደ ማፑቶ ለመመለስ እና ተቃውሞውን ለመቀላቀል ሁሉም ቅድመ ሁኔታዎች እንደተመቻቸላቸው አረጋግጠው ደጋፊዎቻቸው ትግሉን አጠናክረው እንዲቀጥሉ ነግረዋቸዋል።
በዚህ ሁኔታ በሞዛምቢክ የቀጠለው አፈና እና ተቃውሞ ተንታኞች በቅርብ ሁኔታው ይቀየራል ብለው አያስቡም።ይህም ሀገሪቱን ለከፋ ቃውስ ይዳርጋል የሚል ስጋት አሳድሯል።


ፀሐይ ጫኔ
ነጋሽ መሐመድ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ የ DW ታላቅ ዘገባ

የ DW ታላቅ ዘገባ

ቀጣዩን ክፍል ዝለለዉ ተጨማሪ መረጃ ከ DW

ተጨማሪ መረጃ ከ DW