በሞያሌ ከተማ በሰንደቅ ዓላማ ውዝግብ የታዳጊ ህይወት አለፈ
ሐሙስ፣ ጥቅምት 12 2019
በሞያሌ ከተማ በሰንደቅ ዓላማ ውዝግብ የ13 ዓመት ታዳጊ ህይወት ማለፉ
በኦሮሚያ ክልል ሞያሌ ከተማ ጥቅምት 08 ቀን 2019 ዓ.ም. በሰንደቃላማ በተነሳው ውዝግብ በተቀሰቀሰ ግጭት የሰው ህይወት ማለፉን የአይን እማኞች ለዶይቼ ቬለ ተናገሩ፡፡ በሶማሌ እና ኦሮሚያ ክልሎች አዋሳኝ ላይ በምትገኘው ሞያሌ “ያለ ቦታው ተሰቀለ” በተባለ ባንድራ ላይ ቅሬታ ያላቸው የአከባቢው ነዋሪዎች ያነሱትን ተቃውሞ ተከትሎ የአከባቢው የሁለቱ ክልሎች የጸጥታ ሃይሎች መሃል አለመግባባት ተፈጥሮ በመሃልም የ13 ዓመት ታዳጊ ህይወት በተተኮሰ ጥይት ማለፉ ነው የተሰማው፡፡ ቅዳሜ እለት በተፈጠረው በዚህ ውዝግብ ከሰኞ ጀምሮ እስከ ዛሬ እሮብ ለሶስት ተከታታይ ቀናት ውዝግቡ ቀጥሎ የከተማዋ የንግድ እንቅስቃና የትራንስፖርት አገልግሎት እክል አጋጥሞት መቆየቱንም ነዋሪዎቹ አስረድተዋል፡፡
በኦሮሚያ ክልል ቦረና ዞን ሞያሌ ከተማ አዲስ የሶማሌ ክልል አስተዳደር ሰንደቅ ዓላማ መሰቀሉን ተከትሎ በሶማሌ ክልል የጸጥታ ኃይሎች እና በኦሮሚያ የአካባቢው ሚሊሻዎች መካከል በተፈጠረው አለመግባባት ግጭት ተከስቶ እንደነበር ለዶይቼ ቬለ የተናገሩት የከተማዋ ነዋሪ የዓይን እማኝ፤ ውዝግብ የፈጠረው ክስተት መነሻን እንዲህ ገልጸዋል፡፡ “የአከባቢው የሶማሌ ጎሳ የሆኑት ገሪዎች ከዚህ በፊት የክልላቸው ባንድራ ተሰቅሎበት በማያውቅ ቦታ ላይ ባንድራ ሰቀሉ፡፡ ይህ ቦታ ሞያሌ 02 ቀበሌ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን ከዚህ በፊት በክልል-5 በኩል የይገባኛል ጥያቄ ተነስቶበት የማያውቅና ከዚህ በፊት ባንዲራቸውም ተሰቅሎበት የማያውቅ ቦታ ነው፡፡ በዚህ የአከባቢው ማህበረሰብ ቅሬታ ማሰማቱን ተከትሎ የአከባቢው ሁለቱ የፀጥታ አካላት መካከል አለመግባባት ይፈጠራል፤ በዚህ አጋጣሚ የአገር ሽማግሌዎችም ተጠርተው የፌዴራል የጸጥታ ሃይሎችም በመሃል ገብተው አቁሙ አሏቸው፡፡ በዚህም ነው ውጥረቱ የተረጋጋው” ብለዋል፡፡
ሌላው አስተያየት ሰጪ አከባቢው የአገር ሽማግሌ እንደነገሩን፤ “ነገሩ የተነሳው በሰንደቃላማ መሰቀል ምክንያት ነው፡፡ ይህ ባንዲራ የተሰቀለው በክልል አምስት በገሪ ጎሳዎች ነው፡፡ ይህ ባንዲራ የተሰቀለበት ቦታ ሞያሌ 02 ከዚህ በፊት ተሰቅሎበት በማይታወቅ ቦታ በመሆኑ አንሱ ተባሉ፡፡ ይህ ቦታ ግብር እራሱ ሲቆረጥ ወደ ክልል 04 ነው የሚከፈለው፡፡ በክልል አምስት በኩል ያሉ የጸጥታ አካላት በዚህ ፈቃደኛ ባለመሆናቸው በከተማዋ የአከባቢው የጸጥታ አካላት መካከል ውዝግብ ተፈጥሮ ነበር፡፡ አንዲት የ13 ኣመት ታዳጊ ባንዲራውን ለማውረድ ወደ ተሰቀለበት ቦታ ስትወጣ በተተኮሰባትም ጥይት ተገደለች” በማለት አስተያየታቸውን ሰጥተዋል፡፡
ከሰኞ ጀምሮ በዚህ ሦስት ቀናት ውጥረት ነግሶ ስጋቱ እንዳሌ ነው የሚሉት ሌላው አስተያየት ሰጪ የከተማዋ ነዋሪ በፊናቸው፤ “ከበቀደም ጀምሮ እስከዛሬ ድረስ በሁለቱም በኩል ያሉ ወጣቱ ድንጋይ ለመወራወር ውጥረት ፈጥረው ቆይተዋል፡፡ የሞያሌ ከተማ ከንቲባ ቢሮ ላይ ድንጋይ ተወርውሮ ጉዳት ደርሷል፡፡ ይሁንና በመሃል ግጭት እንዳይፈጠር የፌዴራል መንግስት የጸጥታ ሃይሎች መሃል ገብተው እስከዛሬም አቁሙ ብለው እየተከላከሉ ነው” ብለዋል፡፡
በውጥረቱ የተፈጠረው የንግድና ትራንስፖርት መቀዛቀዝ
በዚሁ በተፈጠረው ውጥረት ምክንያት የንግድ ከተማ በሆነችው የድንበር ከተማዋ ሞያሌ የንግድና የትራንስፖርት እንቅስቃሴው መስተጓጎሉን የገለጹልን የከተማዋ ነዋሪ የአይን እማኞች የተፈጠረው አለመረጋጋት እና የሰላም እጦት ስጋት እንደቀጠለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ “ዛሬም ከተማዋ ላይ የሚታየው የጸጥታ አካላት ነው እንጂ ሰው ምንም ነገር እየተገበያየ አይደለም፡፡ በዚህም በዚያም የታጠቁ አካላት ናቸው የሚታዩት እንጂ ንግዱ ተቀዛቅዟል ትራንስፖርትም የለም” ብለዋል፡፡
ዶይቼ ቬለ ነዋሪዎቹ ስላነሱት ስጋትና ክስተቱ ላይ ተጨማሪ መረጃ እና እልባቱን ለመጠየቅ ለሁለቱ ክልሎች የኮሚዩኒኬሽን ባለስልጣናት እንዲሁም ለሞያሌ ከተማ ከንቲባ ገልማ ኮሮጲቻ በመደወል ተጨማሪ መረጃ ለማግኘት ያደረገው ጥረት አልተሳካም። አስተያየት ሰጪዎቹ የከተማዋ ነዋሪዎች በሰጡን አስተያየት ግን ችግሩ በሁለቱም ወገኖች በኩል ተቀራርበው አፋጣኝ ውይይቶች ተደርጎ መፈታት ያለበት ነው፡፡ “ሁለቱም አመራሮች ፊትለፊት አውነት ተነጋግረው መፍታት አለባቸው፡፡ የሁለቱም ማህበረሰብ የአገር ሽማግሌዎች ዛላቂ መፍትሄ ላይ መነጋገር አለባቸው” ብለዋል፡፡
ሌላኛውም አስተያየት ሰጪ ቀጠሉ፤ “በሁለቱም በኩል ሽማግሌዎች እና አስተዳዳሪዎች አብረው ተቀምጠው ተወያይተው እልባት ማስቀመጥ አለባቸው፡፡ በዚህ ውጥረት ከተማዋ ምንም እንቅስቃሴዋ በመቆሙ የደሃ ልጅ በርሃብ እየተቸገረ ይገኛል” ሲሉ አስተያየታቸውን አክለዋል፡፡
ሥዩም ጌቱ
አዜብ ታደሰ
ኂሩት መለሰ